1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቲት 18 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ታትሟል ሰኞ፣ የካቲት 18 2016የመጨረሻ ማሻሻያ ሰኞ፣ የካቲት 18 2016

በእንግሊዝ የካራባዎ ዋንጫን ቸልሲ በጉዳት በርካታ ታዳጊዎችን ለማሰለፍ ለተገደደው ሊቨርፑል አሳልፎ ሰጥቷል ። በቱኒዝያ በተከናወነው የአፍሪቃ አገር አቋራች አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ የ2ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች ። ስለ ድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እድሳትና ይዞታ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ።

https://p.dw.com/p/4ctut
ሊቨርፑል የካራባዎ ዋንጫን አነሳ
ሊቨርፑል ቸልሲን በፍጻሜው 1 ለ0 አሸንፎ የካራባዎ ዋንጫን አነሳምስል Hannah Mckay/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ የካራባዎ ዋንጫን ቸልሲ በጉዳት በርካታ ታዳጊዎችን ለማሰለፍ ለተገደደው ሊቨርፑል አሳልፎ ሰጥቷል ። በቱኒዝያ በተከናወነው የአፍሪቃ አገር አቋራች አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ የ2ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቀቀች ። እደሳ በተደረገለት የድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ሁለተኛው ቡድን የኡጋንዳ ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ቡድንን 1 ለ0 አሸንፏል ። ስለ ጨዋታው እና ስታዲየሙ ይዞታ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ።

አትሌቲክስ

ሰሜን አፍሪቃዊቷ ቱኒዝያ ውስጥ ትናንት እሁድ የካቲት 17 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛው የአፍሪቃ አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ በሁለተኝነት የሚዳሊያ ሰንጠረዥ በመያዝ አጠናቀቀች ። በፉክክሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዐሥራ ሁለት ሃገራት መካፈላቸው ተገልጧል ። ኢትዮጵያ በወጣት ሴት 6 ኪ.ሜ.፣ በወጣት ወንድ 8 ኪ.ሜ.፣ በአዋቂ ሴትና ወንድ 10 ኪ.ሜ፤ እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ በአጠቃላይ በ28 አትሌቶች መካፈሏ ተዘግቧል ።

በዚህ ፉክክርም፦ኢትዮጵያ በግል እና በቡድን ሁለት የወርቅ፣ አምስት የብር እና ሦስት የነሐስ በድምሩ ዐሥር ሜዳሊያዎችን አግኝታለች ። በዚህም መሠረት፦ ከመላው አፍሪቃ ተሳታፊዎች አራት የወርቅ፤ ሦስት የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችው ከኬንያን በመከተል የሁለተኝነት ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች ። የካቲት 11 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በውድድሩ አስተናጋጇ ቱኒዝያን ጨምሮ፦ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ኬንያ፣ አንጎላ፣ ሲሼልስ፣ ላይቤሪያ፣ ኮንጎ፣ ኬፕ ቬርዴ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ኢትዮጵያ ተሳትፈዋል ። የኬንያ ቡድን  ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ፉክክር ብቻ ሲቀረው በጠቅላላው ውድድር የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመጠቅለል ዘንድሮም የበላይነቱን አስጠብቋል ። ኬንያ እና ኢትዮጵያ ከአንድ ወር ግድም በኋላ ቤልግሬድ ሠርቢያ ውስጥ በሚዘጋጀው የዓለም አገር አቋራጭ ፉክክር ላይ ከወዲሁ ግምት ተሰጥቷቸዋል ። 

ከፍ ብላ የምትሮጥ ሴት አትሌት
ከፍ ብላ የምትሮጥ ሴት አትሌት ምስል Michael DeYoung/Bildagentur-online/Blend Images/picture alliance

ከዚህ ባሻገር፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ስኮትላንድ ግላስጎው ውስጥ በሚካሄደው በ19ኛው የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር ውጤት ለማስመዝገብ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከወዲሁ ልምምዱን እያከናወነ መሆኑ ተገልጧል ። 130 ሃገራት በሚሳተፉበት የስኮትላንዱ ፉክክር ከፊታችን ዐርብ እስከ እሁድን ድረስ በ26 ዘርፎች ውድድሮች ይከናወናሉ ።

እግር ኳስ

የጥር 20 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ የድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም እድሳት የምረቃ ስነስርዓት በማስመልከት ትናንት በኢትዮጵያ ሁለተኛ ብሔራዊ ቡድን እና በዩጋንዳ ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች  መካከል በተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ኢትዮጵያ 1 ለ0 አሸንፋለች ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚው የኡጋንዳ ቡድንን ያሸነፈው ቢንያም ዐይተን 69ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ነው ። የስታዲየሙ እድሳት መመረቅ የኢትዮጵያ ስታዲየሞች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያካሂዱ በካፍ ተጥሎ ለነበረው እገዳ ምን አንደምታ አለው? ውድድሩስ በካፍ አለያም በፊፋ ዕውቅና አለው? የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ስለድሬዳዋው ስታዲየም በዓለም አቀፍ ገምጋሚዎች ውሳኔ ባይሰጥበት ተስፋ እንዳለው ገልጧል ። 

የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ
የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ምስል privat

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ዛሬ ማታ ዌስትሀም ዩናይትድ ብሬንትፎርድን ያስተናግዳል ። ብሬንትፎርድ ባለፈው ጨዋታ በሊቨርፑል ከደረሰበት የ4 ለ1 ብርቱ ሽንፈት ገና አላገገመም ። ዎልቭስ ሼፊልድ ዩናይትድን ትናንት 1 ለ0 አሸንፏል ። ቅዳሜ ዕለት አርሰናል ተጋጣሚው ኒውካስልት 4 ለ1 አንኮታኩቷል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ፉልሀምን አስተናግዶ የ2 ለ1 ሽንፈት ደርሶበታል ።   ኤቨርተን ከብራይተን ጋ አንድ እኩል ወጥቶ ነጥብ ተጋርቷል ። ክሪስታል ፓላስ በርንሌይን 3 ለ0፤ አስቶን ቪላ ኖቲንግሀም ፎረስትን 4 ለ2 አሸንፈዋል ።  ማንቸስተር ሲቲ በትግል በርመስን 1 ለ0 ማሸነፍ ችሏል ። 

የጥር 13 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ በደረጃ ሰንጠረዡ ማንቸስተር ሲቲ 59 ነጥብ ይዞ 2ኛ ነው ።  አርሰናል በ58 ሦስተኛ፣ አስቶን ቪላ 52 ነጥንብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ሊቨርፑል በ60 ነጥብ ይመራል ። ቸልሲ በ35 ነጥቡ 11ኛ ደረጃ ላይ ነው ።

ሊቨርፑል የካራባዎ ዋንጫን አነሳ

እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የተከፈለባቸው ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችን ያሰለፈው ቸልሲ በካራባዎ ዋንጫ አዳጊዎችን ካሰለፈው ሊቨርፑል ጋ ትናንት ገጥሞ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። በርካታ ወሳኝ ተጨዋቾቹን በጉዳት ያጣው ሊቨርፑል ገና ከአካዳሚ ብቅ ያሉ በርካታ አዳጊዎችንም አሸንፎ ለዋንጫ ድል መብቃቱ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል ። ሊቨርፑል ግብ አዳኞቹ ሞሐመድ ሣላኅ፣ ዲዬጎ ጆታ እና ዳርዊን ኑኔዝን ጨምሮ በርካታ ወሳኝ ተጨዋቾች በጉዳት መሰለፍ አልቻሉም ።

በካራባዎ ዋንጫ ሽንፈት የቸልሲ ተጨዋቾች አንገት ደፍተዋል
ሊቨርፑል የካራባዎ ዋንጫን ሲያነሳ የቸልሲ ተጨዋቾች አንገት ደፍተዋልምስል Hannah Mckay/REUTERS

ጀርመናዊው አሰልጣኝ ምንም እንኳን ልድም ያላቸው ተጨዋቾቻቸው ቢጎዱባቸውም አዳዲሶቹን ከቀድሞዎቹ ጋ በማጣመር ደፋር ሙከራቸው ስኬት ተጎናጽፈዋል ። አሰልጣኙ በእርግጥም ለዋንጫው ቋምጠው ከመጨነቅ ይልቅ በአዳጊ ተጨዋቾች ብቃት ሲደሰቱ እና ሲዝናን በገጽታቸው ማየት ይቻል ነበር ። በስተመጨረሻም በጨዋታ ወቅት የነበራቸውን ደስታ ዋንጫ በማንሳት እና ሜዳሊያ በማጥለቅም አጣጥመዋል ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባለፈው ውድድር አቻ የተለያየው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት በሆፈንሀይም ሽንፈትን አስተናግዷል ።  ዶርትሙንድ በሜዳው ሲግናል ኤዱና ፓርክ 3 ለ2 ነው የተሸነፈው ።  በዚህም መሠረት በ41 ነጥቡ ተወስኖ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ ይገኛል ። የጥር 6 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

አውግስቡርግ ትናንት ፍራይቡርንግን አስተናግዶ 2 ለ1 ሸንቷል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና ቮልፍውቡርግ ሁለት እኩል ተለያይተዋል ። ባለፈው ዐርብ ማይንትስን 2 ለ1 የረታው ባዬር ሌቨርኩሰን በ61ነጥቡ በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነት ተኮፍሷል ። ባዬርን ሙይንሽን ከትናንት በስትያ ላይፕትሲሽን 2 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 53 አድርሷል ። ከኮሎኝ ጋ አንድ እኩል የተለያየው ሽቱትጋርት በ47 ነጥቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ላይፕትሲሽ 40 ነጥብ ይዞ ዶርትሙንድን ይከተላል ። 17 ነጥብ ያለው ያለው ኮሎኝ 16ኛ ወራጅ ቀጠናው ጠርዝ ላይ ሰፍሯል ። ማይንትስ እና ዳርምሽታድት በ15 እና 13 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛሉ ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ