1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 13 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 13 2016

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት የሚከናወነው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያዎች ያልተጠበቁ ውጤቶችን እያስተናገደ 3ኛ ዙር ላይ ደርሷል ። በቡንደስሊጋው ባዬርን ሙይንሽን ሽንፈት ሲገጥመው በፕሬሚየር ሊጉ ደግሞ ሊቨርፑል በአስተማማኝ መልኩ ድል አድርጓል ። ኢትዮጵያውያን በአትሌቲክስ ድል ተቀዳጅተዋል ።

https://p.dw.com/p/4bY7J
የአፍሪቃ እግር ኳስ ግጥሚያ በአይቮሪኮስት
የአፍሪቃ እግር ኳስ ግጥሚያ በአይቮሪኮስት፤ የመክፈቻው ስነስርዓት ደማቅ ነበር ምስል Weam Mostafa/BackpagePix/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት የሚከናወነው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ ያልተጠበቁ ውጤቶችን እያስተናገደ 3ኛ ዙር ላይ ደርሷል ። ከ24ቱ ቡድኖች 3ኛ ዙር ግጥሚያ ሳያደርጉ ወደ ቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሁለት ቡድኖች ኬፕ ቬርዴ እና ሴኔጋል ናቸው ። በቡንደስሊጋው ባዬርን ሙይንሽን ሽንፈት ሲገጥመው በፕሬሚየር ሊጉ ደግሞ ሊቨርፑል በአስተማማኝ መልኩ ድል አድርጓል ። ኢትዮጵያውያን በአትሌቲክስ ድል ተቀዳጅተዋል ። 

የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ

በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የምድብ ግጥሚያ ትናንት ደቡብ አፍሪቃ ናሚቢያን 4 ለ0 ድል አድርጋለች ። ደጋፊዎች ደቡብ አፍሪቃ አምስተኛ ግብ እንድታስቆጥር በእጅ ምልክት እየሰጡ ሲያበረታቱ ነበር ። በእርግጥም በአራት ግብ ብቻ የረኩ ያልመሰሉት ደቡብ አፍሪቃ ተጨዋቾች አምስተኛ ሊሆን የሚችል ኳስ መክኖባቸዋል ። ከምሥራቅ አፍሪቃ ዘንድሮ ብቸኛ ሆና ያለፈችው ታንዛኒያ የማሸነፍ እድሏን በባከነ ሰአት ከእጇ አስወጥታለች ። ዛምቢያ በ88ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ግብ ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል ።

ማሸነፍ ሲገባት የማታ ማታ ድሏን አሳልፋ የሰጠችው ታንዛኒያ በ1 ነጥብ ብቻ ተወስናለች ። ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋ ረቡዕ የመጨረሻ ግጥሚያዋን ታከናውናለች ። በምድቧ ዛምቢያ በ2 ነጥብ ይከተላል ። የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ተመሳሳይ 2 ነጥብ ይዞ 2ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ሞሮኮ በ4 ነጥብ 1ኛ ነች ። 

የአፍሪቃ እግር ኳስ ግጥሚያ ደጋፊዎች
የአፍሪቃ እግር ኳስ ግጥሚያ ደጋፊዎች ሞሮኮ ከኮንጎ ጋ ሲጫወትምስል Sia Kambou/AFP

ከዛሬ ግጥሚያዎች መካከል፦ ጊኒ ቢሳዎ ከናይጄሪያ እንዲሁም አሰተናጋጇ አይቮሪኮስት ከኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጓቸው ይገኙበታል ። ሞዛምቢክ ከጋና እንዲሁም ኬፕቬርዴ ከግብጽ ጋ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም ዛሬ የሚጠበቁ ናቸው ። በነገው እለት ደግሞ፦ ጋምቢያ ከካሜሩን፤ ጊኒ ከሴኔጋል፤ ሞሪታንያ ከአልጄሪያ እንዲሁም አንጎላ ከቡርኪናፋሶ ጋ ይጋጠማሉ ። ረቡዕ ዕለት ናሚቢያ ከማሊ፤ ደቡብ አፍሪቃ ከቱኒዝያ፤ ዛምቢያ ከሞሮኮ እንዲሁም ታንዛኒያ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋ ተጋጥመው የምድብ ግጥሚያዎች ይጠናቀቃሉ ። ከቅዳሜ ጀምሮም የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።

ዝክረ-ቤከንባወር

በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ ገናና ከነበሩ ጥቂት ተጫዋቾች መካከል፦ «ንጉሠ ነገሥት» የሚል ስያሜን የተቀዳጀው የ78 ዓመቱ ፍራንስ ቤከን ባወር ዝክር ባለፈው ሳምንት ተከናውኗል ። ፍራንስ ቤከን ባወር በወጣትነት ዘመኑ ለ18 ዓመታት ተሰልፎ በተጫወተበት ባዬርን ሙይንሽን አሬና ስታዲዬም ነበር ዝክሩ ዐርብ እለት የተከናወነለት ። በዝክር ስነስርዓቱ ላይ ከፍራንስ ቤከን ባወር ቤተሰቦች በተጨማሪ ታዋቂ ስፖርተኞች እና ፖለቲከኞችም ተገኝተዋል ። የጀርመን ርእሰ-ብሔር ፍራንክ-ቫልተር ሽታየንማየር በዝክሩ ላይ ስለ ቤከንባወር ሲናገሩ፦ «ታላቁ ጀርመን» ሲሉ አወድሰውታል ። «የሀገራችን ተወዳጁ መልእክተኛ» ሲሉም አክለዋል ። 

ንጉሠ ነገሥት» የሚል ስያሜን የተቀዳጀው ፍራንስ ቤከንባወር
በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ ገናና ከነበሩ ጥቂት ተጫዋቾች መካከል፦ «ንጉሠ ነገሥት» የሚል ስያሜን የተቀዳጀው ፍራንስ ቤከንባወርምስል Matthias Schrader/AP/picture alliance

«የተከበራችሁ ሐዘንተኞች፤ እኔ በዓለም ዙሪያ የምር ብዙ ተጉዣለሁ እናም በደረስኩበት ሁሉ በየትኛውም ክፍለ-ዓለም ፍራንስ ቤከንባወር ታዋቂ ነው በተፈጥሮ ከታደለው የዲፕሎማሲ ችሎታ የሀገራችን ተወዳጁ መልእክተኛ ሆኗል ቤከንባወር ለሀገራችን በቀና መንገድ ያበረከተውን፤ በዓለም ዙሪያ ተቀባይነት እንዲኖረን ያደረገውን ማንም ቢሆን በትክክል መገመት አይችልም ለሀገራችን የሚገባውን አበርክቷል »  

ሙይንሽን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ግዙፉ ስታዲየም ቁጥራቸው 30.000 የሚደርስ የፍራንስ ቤከንባወር አድናቂዎች መታደማቸውም ታውቋል ። በዝክር ሥነ ስርዓቱ ላይ የባዬር ሙይንሽን እግር ኳስ ቡድን ፕሬዚደንት ሔርበርት ሐይነር ፍራንስ ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበር ተናግረዋል ።

«ፍራንስ ለሁሉም ከልቡ ወዳጅ ነበር ሁኔታም ከእግር ኳሱ ጎን ለጎን ለየት ያለ ሰብእና አላብሶታል   ዛሬ እዚህ በርካታ ሰዎች በመሰባሰባቸው ደስ ሊለው እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ ትንሽም ቢሆን ሳይደንቀው የሚቀርም አይመስለኝም ምን?‘ ብሎ ሊጠይቅም ይችል ይሆናል ብቻ ሁላችሁም እዚህ በእኔ ምክንያት እንዳይሆን የተሰባሰባችሁት? ግን እኮ አስፈላጊ አልነበረምሊልም ይችላል ስለራሱ ብዙ ማለት የሚመቸው አይነት አይደለም »

የፍራንስ ቤከንባወር ወዳጅ እና ለረዥም ጊዜ አብሮ የተጫወተው የባዬር ሙይንሽን የክብር ፕሬዚደንት ዑሊ ሆኔስ ስለታታሪነቱ መስክሯል ።

«ምንም ነገር ይሥራ ምን ሁሌም የሚላት ነገር አለች፦አይሆንም የማይሆን ነገርማ አላደርግምይል ነበር የባዬርን ሙይንሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሳለ ይሁን ፕሬዚደንት፤ የብሔራዊ ቡድኑ ይሁን የባዬርን ሙይንሽን አሰልጣኝ የነበረ ጊዜ ሁሌም የሚላት ነገር ነበረች፦በፍጹም፤ ይህንእማ አላደርግም ግን ደግሞ ካደረገ፤ በርካታ ልዩ ችሎታዎች እንደነበረው ሰው በሚደንቅ ሁኔታ ጥንቅቅ ባለ መልኩ፤ በትጋት ነበር የሚከውነው። »

በፍራንስ ቤከንባወር ዝክር ስነስርዓት ላይ ታዳሚያን
በፍራንስ ቤከንባወር ዝክር ስነስርዓት ላይ ከፍራንስ ቤከን ባወር ቤተሰቦች በተጨማሪ ታዋቂ ስፖርተኞች እና ፖለቲከኞችም ተገኝተዋል ። ምስል Christian Charisius/dpa/picture alliance

በዝክር ሥነ ስርዓቱ ላይ ከታደሙ ታዋቂ ፖለቲከኞች መካከል የጀርመን መራኄ-መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ፤ የነጻ ባዬርን ግዛት ጠቅላይ ሚንሥትር  ማርኩስ ዞይደር ይገኙበታል ። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማን፤ ጀርመንን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ለዓለም ዋንጫ ያበቁት አሰልጣኝ ዮአሒም ሎይቭ፤ የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እግር ኳስ ኃላፊ ሩዲ ፎይለርም ታድመዋል ። የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ሴፌሪንም በዝክሩ ላይ ለመታደም ሙይንሽን ድረስ ተጉዘዋል ።

የጥር 6 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ እሁድ ዕለት ከቬርደር ብሬመን ጋ ለነበረው የቡንደስሊጋ ግጥሚያ ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩት የባዬርን ሙይንሽን ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖዬር እንዲሁም አጥቂዎቹ ሔሪ ኬን እና ቶማስ ሙይለርም በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል ።

ቡንደስሊጋ

በቡንደስሊጋው ግጥሚያ ባዬር ሙይንሽን ትናንት በሜዳው አሊያንስ አሬና ከቬርደር ብሬመን ጋ በነበረው ግጥሚያም ለፍራንስ ቤከንባወር የመታሰቢያ አበባ ጉንጉን በስታዲየሙ መግቢያ ላይ በረዥም ምንጣፍ አኑሯል ። መሀል ሜዳ ላይም የፍራንስ ቤከንባወርን 5 ቁጥር መለያ ለብሶ የተነሳውን ቆየት ያለ ፎቶግራፍ በማድረግ ዙሪያውን በርካታ የአበባ ጉንጉኖች አኑሯል ።

በቡንደስሊጋው የእግር ኳስ ግጥሚያ ግን  ባዬርን ሙይንሽን በሜዳው  በቬርደር ብሬመን የ1 ለ0 ሽንፈት ደርሶበታል ። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅም በሜዳው አውግስቡርግን አስተናግዶ 2 ለ1 እጅ ሰጥቷል ። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ ላይፕትሲሽ በሜዳው ተጫውቶ በባዬርን ሌቨርኩሰን የ3 ለ2 ሽንፈት ደርሶበታል ። በዚህ ድሉም ባዬርን ሌቨርኩሰን በቡንደስሊጋው ነጥቡን 48 አድርሶ በመሪነቱ ገስግሷል ።  ባዬርን ሙይንሽን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ41 ነጥብ ይከተላል ። ቅዳሜ ዕለት ወደ ቦሁም አቅንቶ 1 ለ0 የተሸነፈው ሽቱትጋርት 34 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ላይፕትሲሽ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድም ተመሳሳይይ 33 ነጥብ ሰብስበው በግብ ክፍያ ልዩነት 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል ። ኮሎኝ ከትናንት በስትያ በቦሩስያ ዶርትሙንድ የ4 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ገጠሞታል ። ኮሎኝ ተመሳሳይ 11 ነጥብ ባላቸው ማይንትስ እና ዳርምሽታድታ መሀል 17ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ በወራጅ ቃጣናው ይቃትታል ። 

 ለፍራንስ ቤከንባወር የመታሰቢያ አበባ ጉንጉን
ለፍራንስ ቤከንባወር የመታሰቢያ አበባ ጉንጉን በስታዲየሙ መግቢያ ላይ በረዥም ምንጣፍ አኑሯል ። መሀል ሜዳ ላይም የፍራንስ ቤከንባወርን 5 ቁጥር መለያ ለብሶ የተነሳውን ቆየት ያለ ፎቶግራፍ በማድረግ ዙሪያውን በርካታ የአበባ ጉንጉኖች አኑሯል ።ምስል LEONHARD SIMON/REUTERS

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት በርመስን በገዛ ሜዳው 4 ለ0 ያንኮታኮተው ሊቨርፑል 48 ነጥብ ይዞ በመሪነት ግስጋሴው ቀጥሏል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ እንዲሁም ቅዳሜ ዕለት ክሪስታል ፓላስን 5 ለ0 ድባቅ የመታው አርሰናል እና አስቶን ቪላ በግብ ክፍያ ተለያይተው በ43 ነጥብ ይከተላሉ ።

የታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ ዐርብ እለት አንድ እኩል የተለያዩት ሉቶን ታወን እና በርንሌይ እንዲሁም ትናንት ከዌስትሀም ጋ ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ የተጋራው ሼፊልድ ዩናይትድ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ። ዛሬ ማታ ብራይተን ዎልቭስን ያስተናግዳል ።

ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ለጥቂት ሳያልፍ ቀርቷል ።  በዓለም ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሺያ ዙር የመልሱን ጨዋታ ትናንት (እሁድ ጥር 12 ቀን፣ 2016 ዓ.ም) በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አከናውኖ ሞሮኮን 1 ለ0 ቢያሸንፍም፤ በደርሶ መልስ የ2 ለ1 የሞሮኮ ድል ግን ለዓለም ዋንጫ ጫፍ ደርሶ ሳያልፍ ቀርቷል ።

አትሌቶች ሲሮጡ
አትሌቶች ሲሮጡ ። ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረኮች በአትሌቲክስ ድል ተቀዳጅተዋል ። ምስል Charlie Neibergall/AP/picture alliance

አትሌቲክስ

የታኅሣሥ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ በስፔን ሳንታ ፖሎ  በተከናወነ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊያኑ በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ በመሆን ሜዳሊያ አግኝተዋል።  ። በወንዶች አንድአምላክ በልሁ  (59:59) አንደኛ በውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ፤ ብረሃኑ ወንድሙ (1:01:12) የሁለተኛ ደረጃ ይዞ የብር ሜዳሊያ ተሸልሟል ። በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር፦ ዘውዲቱ አደራው  አንደኛ (1:07:59) በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ  ስታጠልቅ፤  ትዕግስት አያሌው  (1:09:17) በሦስተኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልማለች ። በሙምባይ ታታ ማራቶንም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች አሸንፊ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌፌሬሽን ዘግቧል ። በወንዶች ውድድር ለሚ ብርሃኑ (2:07:50)፣ ሐይማኖት አለው (2:09:03)እና ምትኩ ጣፋ (2:09:58) ከ1ኛ እስከ 3ኝ በውጣት አሸናፊ ሆነዋል ። በሴቶች ፉክክር ከ1ኛ እስከ 8ኛ ድረስ ኢትዮጵያውያቱ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል ። በዚህ ውድድር አበራሽ ምንሰው (2:26:06) 1ኛ ወጥታለች ። ሙሉ ሐብት ጽጌ (2:26:51) 2ኛ፤ መድኂን ደጀኔ(2:27:34) 3ኛ ደረጃ አግኝተዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ነጋሽ መሐመድ