1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 20 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 20 2016

በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች አስደማሚ በሆነ መልኩ ቀጥለዋል ። በ10 ተጨዋቾች የተወሰነው የኤኳቶሪያል ጊኒ በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች ለጊኒ እጅ መስጠቱ ብዙዎችን አስቆጭቷል ። ግብጽ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ተሸኝታለች ። ውድድሮቹ ቀጥለዋል ።

https://p.dw.com/p/4bnT1
የአይቮሪኮስት ደጋፊ በአፍሪቃ ዋንጫ
በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ወቅት የአይቮሪኮስት ደጋፊምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች አስደማሚ በሆነ መልኩ ቀጥለዋል ። በ10 ተጨዋቾች የተወሰነው የኤኳቶሪያል ጊኒ በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች ለጊኒ እጅ መስጠቱ ብዙዎችን አስቆጭቷል ። ግብጽ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ተሸኝታለች ። አስተናጋጇ አይቮሪ ኮስት ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ ዛሬ ማታ ከሴኔጋል ጋ ትፋለማለች ። በሳምንቱ መጨረሺያ ላይ ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፋቸውን ያረጋገጡት፦ ናይጄሪያ፤ አንጎላ፤ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ጊኒ ናቸው ።   በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ኖርዊች ሲቲን 5 ለ2 ድል ያደረገው ሊቨርፑል አሰልጣኝ ቡድኑን ሊለቁ መሆናቸው በሳምንቱ መጨረሺያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል። ምናልባትም ወደ ባርሴሎና ሊያቀኑ ይችላሉ ተብሏል ። የአትሌቲክስ እና ሌሎች የስፖርት ዘገባዎችንም አካተናል ።

አትሌቲክስ

በጃፓን የኦሳካ ማራቶን በሴቶች የትናንት ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወርቅነሽ ኤዴሳ (2:18:51)አሸናፊ ሆናለች ። በግማሽ ማራቶን የኦሳካ ፉክክር ደግሞ ደስታ ቡርቃ (1:08:20)ሁለተኛ ወጥታለች ። አሸናፊዋ የጃፓኗ ሯጭ ዩካ አንዶ (1:08:18) ናት ።

ስፔን ውስጥ በተከናወነው የሴቪያ ግማሽ ማራቶን የሴቶች ሩጫ ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዓለምጸሐይ ዘሪሁን (1:07:59)አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሆናለች ። ሌላኛዋ የሀገሯ ልጅ አበራሽ ሽልማ (1:08:02) ሁለተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች ።

በታይላንድ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ በወንድም በሴትም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል ። በወንዶች ፉክክር ደረሰ ፈቃዱ (32:18)፤ በሴቶች ደግሞ ዓለምቸሐይ አድባሩ(34:52)ናቸው ያሸነፉት ።

በስፔን ኤቢዛ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ የሴቶች ፉክክር ደግሞ፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ልቅና አምባው (30:57)የ2ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች ። አሸናፊዋ ኬኒያዊቷ ሚሪያም ቼቤት (30:40)ናት ። 

የኦሎምፒክ ችቦ
የኦሎምፒክ ችቦ፤ የጃፓን ኦሎምፒክ እንደጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 ። ፎቶ ከማኅደርምስል BEN STANSALL/AFP/Getty Images

በሌሎች የአትሌቲክስ መረጃዎች፦ የኢትዮጵያ ፓሪስ ኦሎምፒክ 2024 ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ማካሄዱ ተገልጧል ። በዚህም መሰረት የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የሀገር ውስጥ የችቦ ቅብብሎሽ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ መኪያሄዱ ተዘግቧል ። የወንጪ ታላቁ ሩጫ ውድድርም በሳምንቱ መገባደጂያ ተከናውኗል ።

እግር ኳስ

ትናንት ልብ አንጠልጣይ በነበረው የፍጹም ቅጣት ምት መለያ፦ ግብጽ በኮንጎ ዴሞክራሲያዉዊ ሪፐብሊክ ከአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ተሰናብታለች ። መደበኛ ጨዋታው አንድ እኩል ቢጠናቀቀም አንድ ተጨዋች በቀይ ካርድ የተሰናበተባት ግብጽ በፍጹም ቅጣት ምቱ መለያ 8 ለ7 ተሸንፋለች ። በዚህም መሰረት በሩብ ፍጻሜው የኮንጎ ዴሞክራሲያዉዊ ሪፐብሊክ ከጊኒ ጋ የፊታችን ዐርብ ትጋጠማለች ።

የጥር 13 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ጊኒ ሌላኛው በቀይ ካርድ አንድ ተጨዋቿ የተሰናበተባት ኤኳቶሪያል ጊኒን በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች 1 ለ0 አሸንፋ ነው ለሩብ ፍጻሜ የበቃችው ። መደበኛ 90 ደቂቃውንም ሆነ ጭማሪውን 8 ደቂቃ ቀጥ አድርገው የያዙት ኤኳቶሪያል ጊኒዎች የማታ ማታ እጅ ሰጥተዋል ። ምናልባትም ግብ ጠባቂው ግብ የሆነችውን ኳስ ለግቶ ለጊኒ ተጨዋቾች ከመዳረጉ ይልቅ ለቡድኑ ተጨዋቾች ቢያደርስ ጨዋታው ያለምንም ግብ ተጠናቆ ወደ ጭማሪው ደቂቃ ይሻገሩ ነበር ። ያኔ ደግሞ የሚፈጠረው ሌላ ሊሆን ይችልም ነበር ። እናም ግብ ጠባቂው እንዲያ በርካታ ኳሶችን አጨናግፎ በስተመጨረሻ የሠራው ስህተት ከተከላካዮች ድክመት ጋ ተደምሮ ቡድኑን አሳዛኝ ተሸናፊ አድርጎታል ።

የቱኒዝያ ተጨዋቾች ሜዳ ላይ ተዘርግተው ሐዘናቸውን ሲገልጡ
ነደቡብ አፍሪቃ ተሸንፈው ከምድብ ማጣሪያው የተባረሩትት የቱኒዝያ ተጨዋቾች ሜዳ ላይ ተዘርግተው ሐዘናቸውን ሲገልጡምስል Themba Hadebe/AP Photo/picture alliance

ቅዳሜ ዕለት ናሚቢያን 3 ለ0 ድባቅ የመታው አንጎላ፤ ካሜሩንን 2 ለ0 ካሰናበተው ናይጄሪያ ጋ በሩብ ፍጻሜው ዐርብ ዕለት ይጋጠማል ። አንጎላ እና ናሚቢያ በቅዳሜው ግጥሚያ አንድ አንድ ተጨዋቾቻቸው በቀይ ካርድ ተሰናብተውባቸዋል ።  የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቹ ዛሬም ቀጥለው፦ በአስደማሚ ሁኔታ የተጠበቁ ቡድኖችን አሰናብተው በድንቅ ሁኔታ እዚህ የደረሱት ኬፕ ቬርዴ እና ሞሪታንያ ይጋጠማሉ ። ከምሽቱ ሦስት ሰአት ደግሞ  አስተናጋጇ አይቮሪኮስት ከሴኔጋል ጋ የሞት ሽረት ፍልሚያ ታደርጋለች ።  ነገ በሚኖሩ ሁለት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ቀሪ የሩብ ፍጻሜ አላፊ ሁለት ቡድኖች ይለያሉ ። በነገው ዕለት ማሊ ከቡርኪናፋሶ እንዲሁም ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪቃ ይጋጠማሉ ። ዘንድሮ የአረብኛ ተናጋሪ የአፍሪቃ ጠንካራ ሃገራት በምድብ ግጥሚያዎች መሰናበታቸው በርካቶችን አስገርሟል ። እስካሁን አልጄሪያ፤ ቱኒዝያ እና ግብጽ የምድብ ማጣሪያውን ሳያልፉ ተሰናብተዋል ። 

የአፍሪቃ እግር ኳስ በአጓጊነቱ ቀጥሏል

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የፊታችን ረቡዕ ሳምንት ይጠናቀቃሉ ። የቅዳሜ ሳምንት የደረጃ፤ እንዲሁም በነጋታው እሁድ የዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ ።

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች፦ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ትናንት ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፋ የግብ ልዩነት ድል አድርገዋል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በኤፍ ኤ ካፕ የትናንቱ ግጥሚያ ኒውፖርት ካውንቲን 4 ለ2 ድል ያደረገው አጥቂው ራሽፎርድ በሌለበት ነበር ። ማርኩስ ራሽፎርድ በትናንትናው አራተኛ ዙር ጨዋታ ያልተሰለፈው ዐርብ ዕለት እንዳመመው እና መሳተፍ እንደማይችል ከተናገረ በኋላ መሆኑ ተገልጧል ። ሆኖም አጥቂው ሐሙስ ዕለት ቤልፋስት የምሽት ጭፈራ ቤት ውስጥ መታየቱ እና ዐርብ ዕለትም በልምምድ ቦታ አለመገኘቱ ተዘግቧል ። ምናልባትም ቡድኑ የስነምግባር ርምጃ ሊወስድበት ሳይችል አይቀርም ። ለዚያም ይመስላል   የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ፦ «እንግዲህ አመመኝ ብሎ ዐሳውቋል» ያሉት ። «ቀሪው የውስጥ ጉዳይ ነው ። ለእኔ ተዉት ። ለእኛው ተዉት» ሲሉም ያከሉት ።

የጥር 6 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ኳስ መረብ ላይ አርፋ
ኳስ መረብ ላይ አርፋምስል Aijaz Rahi/AP/picture alliance

ትናንት በነበሩ የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች፦ ሳውዝ ሐምፕተን ከዋትፎርድ ጋ አንድ እኩል ተለያይቷል ።  ኒውካስል ፉልሀምን እንዲሁም ዎልቨርሐምፕተን ዌስት ብሮሚችን 2 ለ0 አሸንፈዋል።  ደጋፊዎች ተጣልተው በተከሰተው ግርግር ግን ጨዋታው ለ38 ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር ።  በዛሬው ዕለት በሚኖር የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ደግሞ ብላክበርን ከውሬክስሀም ጋ ይጫወታል ።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዶሚኒካን ሪፐብሊክ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን በዚሁ ሳምንት ያከናውናል ። ቡድኑ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ለሚኖረው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ዝግጅት እንዲሆነው በሚል ቅዳሜ ዕለት የአቋም መለኪያ አድርጓል ። ብሔራዊ ቡድኑ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ከሆነው መቻል ሴቶች የእግር ኳስ ቡድን ጋ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጋጥሞ አንድ እኩል ተለያይቷል ። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪቃ አቻው ጋ ሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታውን እሁድ ጥር 26 ቀን፣ 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ያደርጋል ተብሏል ።  የማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታው ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የካቲት 2 እንደሚከናወን ተገልጧል ።

ኤፍ ኤ ካፕ አራተኛ ዙር ግጥሚያ 

ለአሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ድጋፍ
አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በሊቨርፑል ደጋፊዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ናቸው ምስል Propaganda Photo/IMAGO

የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በቃኝ አሉ ። ዐርብ ዕለት ደጋፊዎቻቸውን ያስደነገጠው ውሳኔያቸውን በተመለከተ ዬርገን ክሎፕ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጠዋል ። ሊቨርፑልን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ማሰልጠን የጀመሩት ዬርገን ክሎፕ በቡድኑ ገና ተጨማሪ የ2 ዓመት ውል ነበራቸው ። ቢሆንም በቃኝ ብለዋል ።

«ቡድኑን የዉድድሩ ዘመን ሲያበቅ እለቅቃለሁ። ይህ ዜና ለአብዛኞቹ ወዳጆቻችን አስደንጋጭ እንደሆን ዐዉቃለሁ። ጉልበቴ እያለቀ ነው። ይህን ደግሞ አንድ ቀን በይፋ ወጥቼ መናገር እንዳለብኝ ዐዉቃለሁ። ሥራውን ደጋግሜ መሥራት እንደማልችል ዐውቃለሁ። በዚህ ቡድን ዉስጥ ሁሉን ነገር እወዳለሁ። ሥራችን ሁሉ እወዳለሁ ግን ሥራዬን ደግሜ ማራዘም መቀጠል አልችልም። ለቡድኑ ከፍተኛ ፍቅር አለኝ። ለቡድኑ ማድረግ የምችለዉ አሁን ትንሽ ነገር እዉነት ብቻ ነዉ። እዉነቱ ደግሞ ይህ ነዉ። »  የታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የአሰልጣኞች ዝውውር

የቀድሞው የሊቨርፑል ተጨዋች ዣቪ አሎንሶ የእሳቸውን ቦታ ይተካል እየተባለ ነው።   በሌላ ዜና፦ የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የ18 ወራት ውል ቢቀራቸውም የባርሴሎና አሰልጣኝ ለመሆን ዳር ዳር እያሉ መሆናቸውን ጋዜጦች ዘግበዋል።  ዜናውን አሰelxaNu «ፍጹም ሐሰት» ሲሉ ዛሬ አጣጥለዋል ። የባርሴሎና አሰልጣኝ ዣቪ ሔርናንዴዝ በውድድር ዘመኑ መገባደጃ ቡድኑን ትቶ እንደሚሄድ ተነግሯል ። ዣቪን በመተካት የባርሴሎና አሰልጣኝ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱ ሌሎች አሰልጣኞ መካከል በሊቨርፑል ቆይታቸው እንደበቃቸው የገለጡት ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕም ይገኙበታል ። ባርሴሎና  ሌሎች የጀርመን አሰልጣኞች ላይም ዐይኑን የጣለ ይመስላል ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የአሁኑ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን እንዲሁም የቀድሞ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክም የባርሴሎና አሰልጣኝ ሊሆኑ ይችላሉ ተብልለው ግምት ተሰጥቷቸዋል ። 

የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ
የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2019 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ቡድናቸው ድል አድርጎምስል Actionplus/picture alliance

የአውሮጳ ቡድኖች ውጤቶች

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ነገ ዳግም ይጀምራል ። ኖቲንግሀም ፎረስት ከአርሰናል፤ ሉቶን ታወን ከብራይተን፤ ፉልሀም ከኤቨርተን እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከሼፊልድዩናይትድ ይጋጠማሉ ።

የታኅሣሥ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ትናንት ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቦሁምን 3 ለ1 እንዲሁም ዑኒዮን ቤርሊን ዳርምሽታድትን 1 ለ0 አሸንፈዋል ። ቅዳሜ በነበሩ ግጥሚያዎች ደግሞ፦ ባዬር ሌቨርኩሰን ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ዜሮ ለዜሮ፤ ሆፈንሀይም ከሐይደንሀይም እንዲሁም ቮልፍስቡርግ ከኮሎኝ አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ቬርደር ብሬመን ፍራይቡርግን 3 ለ1 ሲረታ፤ አውግስቡርግ በባዬርን ሙይንሽን 3 ለ2 ተሸንፏል ። ላይፕትሲሽ በሽቱትጋርት የ5 ለ2 ሽንፈት ደርሶበታል ።

በስፔን ላሊጋ፦ ሴቪያ ከኦሳሱና አንድ እኩል ሲወጣ፤ አትሌቲኮ ክለብ ከካዲዝ ጋ ያለምንም ግብ ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል ። ሴልታቪጎ በሜዳው ከጂሮና ጋ ተጋጥሞ 1 ለ 0 ሲረታ፤  አትሌቲኮ ማድሪድ ቫሌንሺያን 2 ለ 0 አሸንፏል ።

በጣሊያን ሴሪአ ደግሞ፦ ላትሲዮ ናፖሊን አስተናግዶ ያለምንም ግብ ቬሮና ከፍሮዚኖኔ ጋ አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ኢንተር ሚላን ፊዮሬንቲናን፤ ሞንትሳ ሳሱዎሎን 1 ለ0 አሸንፈዋል ። ጄኖዋ ሌቼን 2 ለ1 ድል አድርጓል ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ