1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፦ ሚያዚያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም.

Hirut Melesseማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2016

የሚያዚያ 15 ቀን 2016 ዓም አርዕስተ ዜና የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙ ከተሞች በተነሳው ግጭት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ መብለጡን የተመድ አስታወቀ። ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ጅቡቲ የባህር ዳርቻ ላይ ሰጥማ 16 ሰዎች መሞታቸውን 28 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት እንዳልታወቀ IOM ዛሬ አስታወቀ። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪቺ ሱናክ ብሪታንያ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ከመላክ የሚያግዳቸው እንደሌለ አስታወቁ። ስደተኞች በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ብሪታንያ እንዳይመጡ የሚከለክል ሕግ የብሪታንያ ፓርላማ ካጸደቀ በኋላ ነው ሱናክ ይህን ያሉት።

https://p.dw.com/p/4f6cF

 

ናይሮቢ   በአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

 

የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙ ከተሞች በተነሳው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ እንደሚበልጥ የተመድ አስታወቀ። ድርጅቱ ትናንት ማምሻውን የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጠቅሶ እንዳስታወቀው በአላማጣ ከተማ እና በራያ አላማጣ ዛታ እንዲሁም ኦልፋ በተካሄደው ግጭት ሰበብ የተፈናቀሉት ቁጥር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከ50 ሺህ በላይ ሆኗል።  በሕይወት ለመቆየት መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ህጻናት የሚገኙባቸው የነዚህ ተፈናቃዮቹ ሰብዓዊ ይዞታም አሳሳቢ ነው ብሏል። ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መካከል በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ የጃፓን የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ኤምባሲዎች ችግሩ በውይይት እንዲፈታና ለሰላማዊ ሰዎችም ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ ክልል መንግስት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ «ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል» ሲል ከሶ አካባቢውን ለቆ ካልወጣ ህዝቡን ከጥቃት ለመከላከልና ክልሉንም ከጥፋት ለማዳን ይገደዳል ሲል አስታውቆ ነበር። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጀኔራል ታደሰ ወረደ  ደግሞ «በኃይል የተያዙ የትግራይ አካባቢዎች» ያሏቸውን ቦታዎች በኃይል ለማስመለስ እንደማይፈልጉ ሆኖም ችግሮቹ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመነጋገርና በመግባባት የሚፈቱ እንደሚሆን ባለፈው ሳምንት ገልፀዋል።

 

 

ባህርዳር    የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ዋለ

 

በአማራ ክልል የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተው እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉን የሰሜን ጎንደር አስተዳደር አስታወቀ። አስተዳደሩ እንዳለው ቃጠሎው ያስከተለው ጉዳት መጠን ገና አልታወቀም ፡፡የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቢምረው ካሳ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ሚያዝያ 10/2016 ዓ ም ከምሽቱ 3 ሰዓት ባልታወቀ ምክንያት በፓርኩ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በህዝቡ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

« ሚያዚያ 10 ከምሽቱ ሦስት ነው የተነሳው።የአካባቢው ማኅበረሰብ ፣የጋይድ ማኅበር ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን መዋቅር ውስጥ በማስገባት ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ አመራርና የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተነስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ ርብርብ አድርገው ለማጥፋት ጥረት አድርገዋል። ቦታው ጓሳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጠፍቷል ስትለው በውስጥ ረመጥ ቆይቶ ንፋስ ሲመጣ የሚነሳበት እድል ነበር። ግን በቁጥጥራችን ስር አውለነዋል።»

 አቶ ቢምረው በድርጊቱ የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች መያዛቸውንም ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ በሕግ አግባብ ምርመራ ተደርጎ ጉዳዩ የሚጣራ መሆኑን፤ ቃጠሎው ያደረሰው የጉዳት መጠንም ተጣርቶ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ከዛሬ 5 ዓመት በፊት ፓርኩ ተመሳሳይ የእሳት አደጋ ደርሶባት በህዝቡና በተባባሪ አካላት መጥፋቱን ዓለምነው መኮንን ከባህርዳር በላከው ዘገባ አስታውሷል።  የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በጎርጎሮሳዊው በ1978 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።

 

ናይሮቢ      ጅቡቲ መርከብ ሰጥማ 16 ፍልሰተኞች ሞቱ 28 የደረሱበት አልታወቀም

 

ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ጅቡቲ የባህር ዳርቻ ላይ ሰጥማ 16 ሰዎች መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) ዛሬ አስታወቀ።  ድርጅቱ እንዳለው 28 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም። IOM የሟቾቹንም ሆነ የጠፉትን ሰዎች ዜግነት አልጠቀሰም። የሰጠመችው ጀልባ ህጻናትን ጨምሮ 77 ስደተኞችን አሳፍራ እንደነበር IOM በኤክስ ገጹ አስታውቋል። በዚሁ መስመር ከሁለት ሳምንት በፊት 60 ስደተኞችን ጭና ትጓዝ የነበረች ጀልባ ከጅቡቲ በስተሰሜን ምስራቅ በሚገኝ ስፍራ ላይ ሰጥማ የ38 ኢትዮጵያውያን ሕይወት ማለፉን ሌሎች 6 ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን ድርጅቱ አስታውቆ ነበር። ኢትዮጵያውያን በብዛት በዚህ መስመር በጀልባ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመሰደድ ሲሞክሩ ተመሳሳይ አደጋ ያጋጥማቸዋል። በተያያዘ ዜና ከፈረንሳይዋ ካሌ ደሴት ወደ ብሪታንያ ለመሻገር ሲሞክሩ አምስት ስደተኞች ባሕር ላይ በደረሰ አደጋ መሞታቸው ተሰምቷል። ሟቾቹን ጨምሮ ከመቶ በላይ ስደተኞችን ጭና የነበረች መርከብ ካገጠማት አደጋ በኋላ የፈረንሳይ የባሕር ኃይል መርከቦች በስፍራው ደርሰው ተሳፋሪዎቹን ለማውጣት መቻላቸው ነው የተገለጸው።

 

ለንደን   ብሪታንያ ተገን ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ መላክ የሚያስችላት ሕግ አጸደቀች

 

የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪቺ ሱናክ ብሪታንያ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ከመላክ የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ አስታወቁ።ሱናክ ይህን ያሉት የብሪታንያ ፓርላማ ስደተኞች በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ብሪታንያ እንዳይመጡ የሚከለክል ሕግ ትናንት ለሊት ካጸደቀ በኋላ ነው።በቅርብ ዓመታት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአፍሪቃ ፣መካከለኛው ምሥራቅና የእስያ ስደተኞች በሀገራቸው በሚደርሱባቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት በሰዎች አሻጋሪዎች በኩል በትናንሽ ጀልባዎች የእንግሊዝ ቻናልን በማቋረጥ ወደ ብሪታንያ ገብተዋል።   ባለፉት ሁለት ዓመታት ብሪታንያ ፍልሰቱን ለማስቆም ከመካከላቸው አንዳንዶቹን ከሀገርዋ የማባረር ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች።  ሕጉ በመጽደቅ መንግሥት ተገን ጠያቂዎችን ከዚህ ቀደም አቅዶ ወዳልተሳካለት ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዝግጅቱን ይጀምራል። ሱናክ ትናንት እንደተናገሩት ከ10 እስከ 12 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ የሩዋንዳ በረራዎች ይጀመራሉ። 500 ሰራተኞች፣ ተገን ጠያቂዎቹን አጅበው ለመውሰድ ተዘጋጅተዋል። ፍርድ ቤቶችም አቤቱታዎችን ለማስተናገድ እየጠበቁ ነው ብለዋል። ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ማባረርን  ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲቃወሙት ቆይተዋል። ተችዎች እቅዱን ኢሰብዓዊ እርምጃ ይሉታል።

 

በርሊን   አንድ የአውሮጳ ፓርላማ አባል ረዳት ለቻይና በመሰለል ተጠርጥሮ ታሰረ

 

አንድ በአውሮጳ ፓርላማ የቀኝ ጽንፈኛው የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ አባል ረዳት ለቻይና በመሰለል ተጠርጥረው ታሰሩ። አቃቤ ሕግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ  ጂያን ጂ ሲል የጠቀሳቸው የፓርላማ አባል ረዳት ፣የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ስለሚወያይባቸው ጉዳዮች ለቻይና የስለላ ተቋም መረጃ በማስተላለፍ ተጠርጥረው መያዛቸውን አስታውቋል። ባለፈው ሰኔ በተካሄደ ምርጫ የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ አባል የሆኑት ማክሲሚልያን ክራህ የተባሉት የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲው የፓርላማ አባል ከረዳታቸው አንዱ በስለላ ተጠርጥረው መያዛቸውን ከመገናኛ ብዙሀን መስማታቸውን ተናግረው መሰለላቸው ከተረጋገጠ ከርሳቸው ጋር መስራት አቆማለሁ ብለዋል። ከቅርብ ወራት ወዲህ የምዕራብ አውሮጳ ሀገራት  ቻይና ተካሂዳለች የሚባለው ስለላ ትኩረታቸውን ስቧል። ሰኞ እለት ሶስት የጀርመን ዜጎች ወታደራዊ መተግበሪያዎች ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች ለቻይና አሳልፎ በመስጠት ተጠርጥረው ታስረዋል። በዚሁ እለት ብሪታንያ ውስጥ ሁለት ሰዎች ለቻይና በመሰለል ተከሰዋል።ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ፣  የፓርላማ አባላትን ጨምሮ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ቻይና በሳይበር ስለላ ታካሂዳለች ሲሉ ወንጅለው ነበር። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ቻይና በአውሮጳ ስለላ ታካሂዳለች መባሉን ቻይናን ለማዋረድና ለመጫን ታስቦ የሚደረግ ሲሉ አጣጥለውታል።

 

ብራሰልስ      የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ የሰዎችን ጉልበት በመበዝ የሚሰሩ ምርቶችን አገደ

የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ የሰዎችን ጉልበት በመበዝ የሚሰሩ እቃዎችን ሽያጭ ፣ የወጪና የገቢ ንግድ በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት አገደ። ፓርላማው ገደቡን የጣለው በተለይ በቻይናዋ ግዛት ሺንጃንግ አሳሳቢ በሚባለው የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ መነሻነት ነው። ዩናይትድ ስቴትስም ከሶስት ዓመት በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምበታል ከሚባለው ሺንጃንግ በሚመጡ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ እገዳ ጥላለች።   አንድ እቃ የሰዎችን ጉልበት በመበዝ የተመረተ መሆኑ ከተረጋገጠ በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ገበያ መሸጥ አይቻልም። እገዳ የተጣለባቸው ምርቶችንም ለመያዝ በኅብረቱ ድንበሮች ቁጥጥር ይካሄዳል።ቻይና በበኩልዋ ዋነኛ የጥጥ አምራች በሆነችው ሺንጃንግ ግዛት የመብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ መባሉን አስተባብላለች።

 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።