1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016

https://p.dw.com/p/4erGD

የኢትዮጵያ መንግስት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ ብሪታንያ እና ሰሜን አየር ላንድ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያውያን ተረጂዎች የሚውል ዓለማቀፍ የገንዘብ ማሰባሰብ መርኃ ግብር ጄኔቫ ስዊዘርላንድ ውስጥ እያካሄዱ ነው።

በተያዘው የጎርጎረሳዉያኑ 2024  ለኢትዮጵያዊያን ተረጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ዛሬ በመርኃ ግብሩ ላይ በድጋሚ አስታውቋል። ነገር ግን ሰብአዊ እርዳታውን ለማድረስ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ  እስካሁን ከለጋሾች ማሰባሰብ የቻለው፣ ከ5 በመቶ በታች እንደሆነ ዓለማቀፉ ድርጅት ገልጿል።

በዛሬው የጄኔቫው መርሃ ግብር ከለጋሾች ለመሰብሰብ የታቀደው፣ በጣም አስቸኳይ ለሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች የሚውል 1 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ነዉ የተመለከተው።

በኢትዮጵያ 4.5 ሚሊዮን የውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ ከአንድ ቀን በኋላ በከፋ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ላለች ሱዳን የሰብአዊ ዕርዳታ ይደርስ ዘንድ የሚያስፈልገውን 2.1 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ተመሳሳይ መርኃ ግብር ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዟል።

 

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጠላት የሆኑ ሐይሎች ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ነው ሲሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሱ።

የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል በተያዙ የትግራይ ግዛቶች፥ እየታየ ያለው ክስተት በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር አልያም በህወሓት፥ ወይም ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በይፋዊ ማሕበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ ክስተቱ ሁለቱ ወገኖች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እያደረጉት ያለውን አወንታዊ ግንኙነት ለማደናቀፍ የሚፈልጉ "የስምምነቱ ጠላቶች" የፈጠሩት ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ህወሓት ለአራተኛ ዙር በህዝባችን ላይ ግጭት ቀስቅሷል ሲል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ «አብን» ከስሷል። አብን በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ ህወሓት «ከትናንቱ ታሪካዊ ስህተቱ የማይማር» በማለት ብርቱ ነቀፋ የሰነዘረው። የአብን መግለጫ የተሰማው፣ የህወሓት ኃይሎች በራያ አላማጣ አካባቢ «አንዳንድ ቦታዎችን እየተቆጣጠሩ ነው» የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ  ነው።

አብን፤ «በህወሓት ችግር የአማራና የትግራይ ህዝቦች ፣ መላ ሀገሪቱ እና ቀጠናው ችግር ውስጥ እየወደቀ በመሆኑ ይህ በአስቸኳይ እንዲቆም» ሲል  ጠይቋል። በተለይ የፌዴራሉ እና የአማራ ክልል መንግስታት «በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘውን ወረራ» ያለውን « በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አበክረን እንጠይቃለን» ም ፤ ብሏል።

 

ሞኑን በራያ አላማጣ ወረዳ አንዳንድ አካባቢዎች ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በ10ሺህ የሚቆጠሩ የአላማጣና ኮረም ነዋሪዎች ወደ ቆቦና ሰቆጣ መፈናቀላቸውን ተናገሩ።
አንድ ከአላማጣ ከተማ ትናንት ወደ ቆቦ እንደተፈናቀሉ የነገሩን ተፈናቃይ እንዴት ናችሁ ያለን አካል የለም፣ በየበረንዳውና በየመንገዱ ተበትነናል ብለዋል። በመንገድ ላይ ከየት እንደተተኮሰ በማይታወቅ ጥይት ተመትተው የሞቱ ሠዎች እንዳሉም አመልክተዋል።
«ትናንት የተፈጠረው፣ የመማር ማስተማርና ሌሎችም የቢሮ ስራዎች ነበሩ፣በኋላ ላይ ግን ህዝቡ እንዳለ ተደናገረ ቤቱን ጥሎ ወጣ፣ ወደ ቆቦ ነው ሰው የሄደው፣ ወዴት ናችሁ? የት ናችሁ? ያለን እንኳ የለም፣ ወደ ወገናቸው ሲመጡ ከየት እንደተተኮሰ ባታወቅም ተተኩሶባቸው የተገደሉ ተፈናቃዮችም ነበሩ»
እንደ አስተያየት ሰጪው 10ሺህ ያክል ሰዎች ከአላማጣ ቆቦ ገብተዋል። እንደዚሁም ከኮረም ከተማ የሚፈናቀሉ ሠዎች ሰቆጣ ከተማ መግባታቸውን ትናንት ከቦታው የደረሱ ተፈናቃይ ተናግረዋል። የፀጥታ አካላት አባላት ተፈናቃዮችን አትሂዱ እያሉ ሲመልሷቸው መመልከታቸውንም ለዶቼ ቬለተናግረዋል።
« ሰው እየወጣ ነው፤ አላማጣም ወጥቷል ፤ ከኮረምም እየወጣ ነው ፤ ያው እኔ ራሱ ወጥቻለሁ ሰቆጣ ነው ያለሁት ፤ ትናንት ነው የወጣሁት እኔ በዚህ በአሸንጌ በኩል መጥተዋል። ግን ፌዴራል ፖሊሶች ተመለሱ እያሉ ነው።»
የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ሊቀመንበርና የዓላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ „ምንም እንኳ የትግራይ ተዋጊዎች ከተሞችን መቆጣጠር ባይችሉም በየተራሮች አሉ” ብለዋል። ህብረተሰቡም ያለውን ሥጋት በመፍራት እየተፈናቀለ እንደሆነ ለባህር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን አረጋግጠዋል። የምሽቱ ዜና መጽሔታችን በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ዘገባ ይዟል።
 

የእስራኤል ወታደሮች ደቡባዊ የጋዛ ሰርጥን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ 1 ሺ ቶን የሚመዝኑ ያልፈነዱ ቦምቦች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ማግኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጥኤማውያን ስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ። የቦምቦቹ መገኘት በሰርጡ በተረጋጋ ሁኔታ እርዳታ ለማድረስ ብርቱ ተግዳሮት ሳያስከትል እንደማይቀር አስግቷል።

 የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ እንዳለው የእስራኤል ወታደሮች ዋነኛዋን ካን ዬኑስ ማዕከላዊ የከተማ ክፍል ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ በተደረገ አሰሳ ቦምቦቹ ተገኝተዋል። በአካባቢው በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ምግብ እና መጠለያን ጨምሮ ለህይወት አድን መሰረታዊ አቅርቦቶች በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ ድርጅቱ አሳስቧል።

የመንግስታቱ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መረጃ የጋዛ ሰርጥን ከፈንጂዎች ለማጽዳት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንደሚያስፈልግ እና ምናልባትም ረዥም ዓመታት ሊወስ,ድ ይችላል  ። በጋዛ ሰርጥ ከስ,ድስት ወራት በላይ ባስቆጠረው የእስራኤል ሃማስ ጦርነት አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች የሆኑ 33,843 ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል። እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እያደረሰች ያለው ጥቃት አሁንም ድረስ አላባራም።

 

በሱዳን ሰላማዊ ዜጎችን ሳይለዩ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች «የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች» ሊሆኑ እንደሚችሉ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አስጠነቀቁ ። በሱዳን ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት አንድ ዓመት ማስቆጠሩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ዋና ጸሐፊ ጉተሬሽ ጦርነቱ ከሁለት ተፋላሚዎች ባሻገር በሱዳን ህዝብ ላይ እየተካሄደ ነው » ብለዋል።

በጦርነቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያንን ለእልቂት በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅላል ያሉት ጉተሬሽ ሰላማዊ ሰዎችን ሳይነጥል የሚደረግ ጦርነት ንጹሃንን ከመግደል፣ ማቁሰል እና ማፈናቀል ባሻገር ህዝቡ በሽብር ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል ብለዋል። ይህ ደግሞ «የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል ነው» በማለት ጉተሬሽ ገልጸዋል።

ከሱዳን የህዝብ ቁጥር አንድ አራተኛውን በሚሸፍነው በምዕራብ ዳርፉር ኤል ፋሽር ዳግም ባገረሸው እና ብሄርን መሰረት ያደረገው ግጭት እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ዋና ጸሐፊው ለጋዜጠኞች በሰጡት በዚሁ መግለጫቸው ጠቅሰዋል። የዳርፉሩ አዲስ ግጭት ወደ ከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይሸጋገርም አስግቷል።  ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃያሎች አር ኤስ ኤፍ የሚደገፉ ሚሊዮኖች ከከተማዋ በስተምዕራብ የሚገኙ መንደሮችን ማቃጠላቸውን ተከትሎ ለበርካታ ሰዎች ዳግም መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

 

የአውሮጳ ህብረት በኢራን የድሮን ቴክኖሎጂ ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ እንዲጣል ፍላጎቷ መሆኑን ጀርመን አስታወቀች። ጀርመን የህብረቱን አዲስ ማዕቀብ ይጣል ጥያቄ ያቀረበችው ኢራን ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት በእስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ነው።

በኢራን የድሮን ቴክኖሎጂ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ለተራዘመ ጊዜ እንዲጣል ከፈረንሳይ እና ከሌሎች የህብረቱ አቻዎቻቸው ጋር መነጋገራቸውን  የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አናሌና ቤርቦክ ተናግረዋል። ቤርቦክ እስራኤልን ለመጎብኘት ከመነሳታቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ማዕቀቡን የመጣል እርምጃ በጋ እንደሚወስዱ ተስፋቸውን አጋርተዋል።

 ይህ በእንዳለ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ዛሬ ወደ እስራኤል አቅንተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ከኢራን ጥቃት በኋላ በእስራኤል እና ኢራን መካከል የሰፈነው ውጥረት እንዳይባባስ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ሮይተርስ ዘግቧል። ኢራን በእስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት መሰንዘሯን ቀድመው ካወገወገዙ ሃገራት ጀርመን አንዷ ናት ።

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ