1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁሉን ሰው ሊያጋጥም የሚችለው የአጥንት መሳሳት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016

የአጥንት መሳሳት ችግር በሁሉም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል እንደሆነ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ችግሩ በሚያጋጥሙ አደጋዎች አጥንት በቀላሉ እንዲሰበር ያደርጋል። አጥንት ጥንካሬ የሚረዳ ነገር ይኖር ይሆን?

https://p.dw.com/p/4erDn
ፎቶ ከማኅደር
የአጥንት መሳሳት ችግር ሁሉኑም ሊያጋጥም የሚችል እንደሆነ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ፎቶ ከማኅደርምስል Imago/Zuma/Sumatran Orangutan Conservation

ሁሉን ሰው ሊያጋጥም የሚችለው የአጥንት መሳሳት

 

የአጥንት መሳሳት መንስኤ

ከአድማጭ የተላከልንን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በድጋሚ ስለአጥንት መሳሳት የጤና ችግር መንስኤ የጠየቅናቸው በዘርፉ ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ ሃኪምነት ያገለገሉት ዶክተር ውብታየ እንደገለጹልን የአጥንት መሳሳት ችግር የዕድሜው ሁኔታ ሊለያይ ቢችልም ሁሉንም ሰው ሊያጋጥም የሚችል ነው። እሳቸው እንደሚሉትም ለአጥንት መሳሳት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሆርሞኖች ወይም ንጥረ ነገሮች በሂደት የሚያደርጉት ለውጥ አንዱ ነውና ምናልባትም ዋነኛው ነው።

 ችግሩ በዕድሜ ሂደት በሴቶች ላይ ቀድሞ የሚከሰት ሲሆን ወንዶችም የአጥንት መሳሳት ተጋላጭ ናቸው። ጠያቂያችን የእናትዎን ዕድሜ አልገለጹም፤ ቢታወቅ ኖሮ ለማብራሪያው የተሻለ እንደሚሆን ነው የተረዳነው። እንዲያም ሆኖ ለአጥንት መሳሳት የሚታወቁም የማይታወቁም ምክንያቶች መኖራቸውን ባለሙያው ይገልጻሉ። አጥንት እንዲሳሳ የሚያደርጉ ምክንያቶች ከሰውነት ውስጥ ያሉ ሂደቶች ብቻም አይደሉም ይላሉ ዶክተር ውብታዬ። ውጫዊ ምክንያቶች ማለትም አልክሆል መጠጥ ማዘውተር፤ እንዲሁም ትንባሆ ማጨስ የመሳሰሉ መንስኤዎች አሉ።

ይህም ብቻም አይደለም ተጓዳኝ ህመም እንደ ስኳር፣ ኩላሊት፤ ሪህ እና የመሰሳሰሉ የጤና ችግሮች መኖር፤ ለእነሱም ሲባል የሚወሰዱ መድኃኒቶች ተጽዕኖ እንደሚኖራቸውም አብራርተዋል። በተጨማሪ፤ ከመጠን ያለፈ ውፍረትና በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግም እንዲሁ መንስኤዎች እንደሆኑ ነው ባለሙያው የተናገሩት።

ፎቶ ከማኅደር ፤ የጉልበት መገጣጠሚያ
በየቀኑ በእግር መንቀሳቀስ ለአጥንት ጥንካሬ እንደሚጠቅም ዶክተር ውብታዬ ዱሬሳ ተክሌ መክረዋል። ፎቶ ከማኅደር ፤ የጉልበት መገጣጠሚያ ምስል picture-alliance / OKAPIA KG, Germany

የአጥንት መሳሳት ችግርን ለማወቅ የሚደረገው

አስቀድሞ የአጥንት መሳሳቱ ችግር እንዳለና በምን ያህል መጠን እንደሆነ ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ከታወቀ በኋላ በሀኪም ትዕዛዝ መሠረት አስፈላጊውን መድኃኒት መውሰድ ሊያግዝ እንደሚችል የገለጹት ዶክተር ውብታዬ፤ መድኃኒቱ ግን ለሕይወት ዘመን የሚወሰድ መሆኑንም አመልክተዋል። ምርመራዎችን ሳያደርጉ ሊወሰዱ የሚችሉ መድኃኒቶችን በተመለከተም የቫይታሚን ዲ ንጥረ ነገር ያለባቸውን የምግብ ተጨማሪዎችን መጠቀም እንደሚመከርም ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን የተሻለ የሚሆነውና የሚመከረው ግን በሀኪም ተመርምሮ የሚታዘዘው መድኃኒት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሀኪም ምክር

የአጥንት መሳሳት ችግር በአብዛኛው ከዕድሜ መጨመር ጋር የሚገናኝ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በወጣትነትም ሊያጋጥም እንደሚችልም ነው ዶክተር ውብታዬ መለከቱት። ጠያቂያችን እናትዎ ያጋጠማቸው የአጥንት መሳሳት ከተጠቀሱት መንስኤዎች በአንዱ ወይም በሌላው ሊሆን እንደሚችል በመገመት ሀኪም ቤት በመሄድ ተገቢውን ምርመራ እንዲያደርጉ መክረዋል። አጥንት እንዲጠነክር ደግሞ በየቀኑ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ እንደሚረዳም ጠቁመዋል። ካልሲየም የሚገኝባቸውን እንደ ወተት እና የወተት ተዋጽኦ ያሉ ምግቦችን መመገብ፤ ክብደት መቀነስ አስፈላጊ መሆኑንም የዘርፉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ አክለው ገልጸዋል። አድማጫችንን ለተሳትፏቸው እንዲሁም ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡንን ዶክተር ውብታየን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ