የአጥንት መሳሳት ችግር እና መፍትሄው
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 11 2013አጥንት ከሰውነት ክፍል ጠንካራው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ጥንካሬውን ሊያጣ እንደሚችል የአጥንት ህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። አጥንት ጥንካሬውን ጤናማ በሆነ መልኩ ጠብቆ እንዲዘልቅ በአመጋገብም ሆነ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ መርዳት እንደሚያስፈልግም ይመከራል። ከዕድሜ መግፋት ጋር በተገናኘ የአጥንት ጥንካሬ ማጣት ወይም መሳሳት እንደሚያጋጥም ቢታመንም ችግሩ በወጣትነት ዕድሜ ሲያጋጥም መንስኤውን ለማወቅ ሊደረጉ የሚገባቸው ምርመራዎች እንዳሉ የዘርፉ ሀኪሞች ይመክራሉ።
«የአጥንት መሳሳት ታምሜ ነው፤ ዕድሜዬ 26 ነው፤ የዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር ነኝ ሥራ መሥራት አልቻልኩም፤ እባካችሁ አጭር መፍትሄ ብታመላክቱኝ?» የሚለው መልእክት ከአድማጫችን ሩሃማ ነው በኢሜይል አድራሻችን የደረሰን። የዩኒቨርሲቲ መምህርት መሆኗን የገለጸችልን እና በወጣትነት የዕድሜ ክልል የምትገኘው ጠያቂያችን፤ ጥያቄያዋን ከዓመታት በፊት ስለአጥንት ጤንነት ያቀረብነውን መሰናዶ ከድረገጻችን በመውሰድ አያይዛዋለች። መምህርት ሩሃማ ስለምትከታተይን በቅድሚያ እናመሰግናለን። ጥያቄሽን በምሥራቅ ጀርመን ድሬዝደን ከተማ አጥንት እና መገጣጠሚያ ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን በሚመለከት የሕክምና ዘርፍ ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ ሃኪምነት በማገልገል ላይ ለሚገኙት ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ፤ አቅርበናል። ዶክተር ውብታየን ለመሆኑ የአጥንት መሳሳት ምንድነው አልናቸው።
«የአጥንት መሳሳት ኦስቲዮፖሮሲስ እንለዋለን ፤ ይኽም ማለት የአጥንት ጥንካሬው መለስለስ ነው። ምክንያቱም አጥንታችን በየቀኑ ይገነባል፤ በአንድ በኩል ደግሞ የተገነባው ይፈርሳል። ግን በብዛት የሚበልጠው መገንባቱ ነው። መገንባቱ ሚዛኑን ጠብቆ ከሆነ የአጥንት ጥንካሬውን አያጣም። የአጥንት ዴንሲቲው ነው ዋናው። ዴንሲቲው ማለት የአጥንቱ አሠራሩ ጠበቅ ያለ ሲሆን፤ በአንድ በኩል እየተገነባ በአንድ በኩል ሲፈርስ የአጥንታችን ጥንካሬው ጤናማ ይሆናል። የማፍረሱ ሂደት ሲያይል በዚያን ጊዜ ነው የአጥንት መለስለስ የሚመጣው።»
አጥንት ከሰውነት ክፍላችን ጠንካራ የሚባለው መሆኑ ነው የዘርፉ ምሁራን የሚገልጹት። ለመሆኑ የአጥንት መለስለስ በምን ምክንያት ይመጣል? ችግሩ በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ ሊከሰት እንደሚችል በማስገንዘብ ባለሙያው በርከት ምክንያቶቹን ይዘረዝራሉ። የአጥንት መሳሳትን ሊያስከትሉ ከሚችሉ ምክንያቶች ዕድሜ አንዱ ነው። ጥያቄው የተላከልን ግን በወጣትነት የዕድሜ ክልል ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ መምህርት ነው። በወጣትነት ይኽ ችግር ሲያጋጥም መንስኤ ሊሆን የሚችለው ምን ይሆን ብለናል ለአጥንት ህክምና ከፍተኛ ባለሙያው።
ወደ ህክምናው ለመድረስ ግን በመጀመሪያ የአጥንት መሳሳት እንዲከሰት ምክንያት የሆነውን እንከን በደም ምርመራም ሆነ ተያያዥ ይኽን ችግር መለየት በሚያስችሉ ምርመራዎች ተለይቶ መረጋገጥ እንደሚኖርበት ነው ዶክተር ውብታየ አጽንኦት የሰጡት። የቫይታሚን ዲ እና የካልሺየም እጥረት፤ እንዲሁም የእንቅርት በሽታ ለዚህ አይነተኛ መንስኤዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም በዋናነት አሳስበዋል። የአጥንት መሳሳት ችግሩ መጠነኛ ከሆነ በምግብ ማለትም ቫይታሚን ዲ ያላቸውን በመመገብ፣ በካልሺየም የበለጸጉትንም በማዘውተር፤ በዚያም ላይ እንቅስቃሴን አዘውትሮ በማድረግ ጥንካሬውን ማሻሻል እንደሚቻልም የአጥንት እና መገጣጠሚያ ህክምና ባለሙያው መክረዋል። በ26 ዓመት የአጥንት መሳሳት ችግር መከሰቱ የተለመደ አይደለም ያሉት ዶክተር ውብታየ የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግ ቀስ በቀስ መጀመር እንደሚገባም ይመክራሉ።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ