1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ - ፎዝያ ጀማል

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2016

የ25 ዓመት ፎዝያ ጀማል ሳዉዲአረብያ ስትኖር አምስት ዓመት ሆኗታል። የማዳም ቤት ገጣሚ ነኝ፤ የደሴ ልጅ ወሎዬ ስትል ራስዋን ታስተዋዉቃለች። በቲክቶክ የመጽሐፍት አንባብያንና ገጣምያን መድረክ ላይ ግጥሞችዋን በማቅረብም ትታወቃለች። በቅርቡ ቲክታክ ላይ በነበረ የሥነ-ግጥም ዉድድርም አሸናፊ ሆናለች። የግጥም መድብሏ በቅርቡአንባብያን እጅ ይደርሳል።

https://p.dw.com/p/4fC3b
የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ
የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ ምስል Privat

የማዳም ቤትዋ ገጣሚ፤ ፎዝያ ጀማል በሳዉዲ አረብያ

የማዳም ቤትዋ ገጣሚ

የ 25 ዓመት ወጣት ነኝ ፤ ሳዉዲአረብያ ስኖር አምስት ዓመት ሆኖኛል። የማዳም ቤት ገጣሚ ነኝ ስትል የነገረችን ፎዝያ ጀማል ትባላለች። በኤሞ እና ቲክቶክ የመጽሐፍት አንባብያን እና ገጣምያን መድረክ ላይ ግጥሞችዋን በማቅረብ ትታወቃለች። በቅርቡ ቲክታክ ላይ በነበረ የሥነ ግጥም ዉድድርም አሸናፊ ሆናለች። ፎዝያ የ 20 ዓመት ሳለች ነዉ፤ ራሴን ላሻሽል ስትል ከደሴ ወደ ሳዉዲ አረብያ ያቀናችዉ።

«ግጥምን ለመጀመርያ ጊዜ በድምፅ ያቀረብኩት ኢሞ በሚባለዉ ማኅበራዊ መገናኛ ላይ ነዉ። ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ የማደንቃት ገጣሚ ስለሆነች። መጀመርያ የስዋን ግጥሞች በማንበብ ነዉ ወደ ማኅበራዊ መገናና በድምጬ የወጣሁት። ግጥም መጻፍ የጀመርኩት ግን እዛዉ ኢትዮጵያ እያለሁ ነዉ። ተማሪ እያለሁኝ ሚዲያ ክለብ ላይ ግጥም እየጻፍኩ አነብ ነበር። የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ነኝ ግን በግጥሜ ዉስጥ ሁለቱን ሃይማኖቶች ለማዛመድ እሞክራለሁ። ብዙ ጊዜ ስለማርያም እጽፋለሁ። ጸሐፊ ስትሆኚ ሁሉንም ነገር ታያለሽ። ሴት ሆነሽ ስደት ላይ ሆነሽ ደግሞ ትንሽ ይከብዳል።  ማዳም ቤት ሰራተኛ ሆኖ ከስራ ጋር ሥነ-ግጥም ልጻፍ ማለት ይከብዳል። እኔ ብዙ ጊዜ ግጥሞቼን የምጽፈዉ ከስራ በኃላ ለሊት ለመኝታ ወደ አልጋዬ ስሄድ ነዉ። ቲክታክ ላይ ሥነ ግጥሞቼንም የማቀርበዉ እንዲሁ ነዉ። ግጥሞቼን የሰሞ የሥነ ጽሑፍ አዋቂዎች እዝያዉ ቲክቶክ ላይ ምክረ ሃሳብ ይሰጡኛል ። ይህን እንዲህ ብታደርጊዉ እያሉ ብዙ የተሻሻልኩት በቲክቶኩ ዓለም ነዉ።»

የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ - ፎዝያ ጀማል
የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ - ፎዝያ ጀማል ምስል Privat

የማዳም ቤትዋ ገጣሚ ፎዝያ ጀማል ቀን በስራ ለሊት የመኝታዋን ጊዜ ግጥም በመጻፍ ፤ ደሞም በማኅበራዊ መገናኛ በተለይ ደግሞ በቲክ ታክ ሥነ ግጥሞችዋን በማቅረብ ታዋቂነትን አትርፋለች። ፎዝያን እንደገጣሚ ለየት የሚያደርጋት፤ ሥለ ድንግል ማርያም በመጻፍዋ  ነዉ የሚሏት አያሌ ናቸዉ። ፎዝያ በበኩልዋ የተወለድኩት ወሎ ያደኩት ደሴ፤ ወለዬ ነኛ መልስዋ ነዉ። 

«ሥነ ግጥምን መቻሌ አልያም መዉደዴ ያደኩበት ሁኔታ ይመስለኛል። ማለቴ ወሎ ላይ ተወልዶ ማደግ፤ እስላሙም ክርስትያኑም በአንድ ሆኖ ነዉ የሚያድገዉ፤ የመጣሁበት መንገድ ይመስለኛል። ለምሳሌ እኔ መስጅድ ስሄድ፤ የኔ ጓደኞች ባለ ማህተቦቹ ነጠላ አጣፍተዉ ወደ ቤተ ክርስትያን ሲሄዱ እንገናኛለን። ከቤተክርስትያን ልንቀበላቸዉ የምንሄድበት አጋጣሚም አለ። ከሁሉ በላይ ደግሞ እኔ ማርያምን በጣም ነዉ የምወዳት። ስለስዋ እጽፋለሁ።»

ኢትዮጵያዉያት ሰራተኞች በሳዉዲ 

በአረቡ ዓለም ስላሉ ሴት ሰራተኞች፤ የማዳም ቤት ሰራተኛ የማዳም ቤት ሲባል ይሰማል በሳዉዲ አረብያ ለኢትዮጵያዉያን ኑሮ እንዴት ይሆን? ገጣሚ ፎዝያ ጀማል፤ ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች ከባድ መሆኑን ተናግራለች። በተለይ ለማዳም ቤት ሰራተኞች ላለቻቸዉ ሴቶች ክብር አለኝ ብላለች። ምክንያቱም በማዳም ቤት ስራ ከፍተኛ ጥንካሪን ስለሚጠይቅ ነዉ ስትል ወጣትዋ ገጣሚ ፎዝያ ተናግራለች። በሳዉዲ የሚኖሩ ወንዶች በሹፊርነት አልያም በበረሃማዉ ገጠር እርሻ ላይ አልያም በግ ግመል እንደሚጠብቁ ተናግራለች።

የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ - ፎዝያ ጀማል
የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ - ፎዝያ ጀማል ምስል Privat

በቅርቡ በሳዉዲ አረብያ የነበሩ በሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ተመልሰዋል። አብዛኞቹ ለበርካታ ወራቶች አልያም ዓመታት እስር ቤት የነበሩ ናቸዉ ። በሳዉዲ አረብያ እስር ቤቶች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትእንደሚካሄድ ይነገራል፤ ወደ ዓረቡ አለም የሚሰደዱ ኢትዮጵያዉያን በመንገድ ጉዞዋቸዉ ብዙ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። በርካታ ወጣት ኢትዮጵያዉያን ሞተዋል። ገጣሚ ፎዝያ እንደተናገረችዉ አሁንም ኢትዮጵያዉያን ወደ ሳዉዲ ይመጣሉ።

ገጣሚ ፎዝያ ጀማል ስላካፈለችን ታሪክ እና ልምዷ፤ በዶቼ ቬለ ስም እናመሰግናለን። የገጣሚ ፎዝያ ጀማል አይነት በርካታ እህቶች በተለይ ደግሞ በአረቡ ዓለም የሚኖሩ እና ልምዳቸዉን ሊያካፍሉን የሚፈልጉ ካሉ፤ በፌስቡክ ዋትስ አፕ አልያም ድረ-ገጻችን ላይ መልክታችሁን አስቀምጡልን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ