1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Shewaye Legesseሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2016

የሰላም ሚኒስትር ደኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ በዛሬ ዕለት የፀረሰላም ኃይሎችን በመደገፍና ጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው። ታንዛኒያ ውስጥ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ155 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ። እስያ ውስጥ ደግሞ በሙቀት ማዕበል ሰዎች እየሞቱ ነው። ቱርክና ግሪክ ከሰሃራ በመጣ አቧራ አየራቸው ታፍኗል። በማዕከላዊ ናይጀሪያ ከባድ ዝናብ በእስር ቤት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ 120 የሚሆኑ እስረኞች ማምለጣቸው ተሰማ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም የወባ በሽታ ስርጭት በእጅጉ መስፋፋቱ እና የሚያደርሰው ጉዳትም እየከፋ መምጣቱ ተገለጸ።

https://p.dw.com/p/4fC8H

አዲስ አበባ፤ አቶ ታዬ ደንደዓ ክስ ተመሰረተባቸው

የሰላም ሚኒስትር ደኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ በዛሬ ዕለት ክስ እንደተመሰረተባቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አስታወቁ። እንደዘገባው አቶ ታዬ ፀረሰላም ኃይሎችን በመደገፍና ጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተባቸው። ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገ-መንግሥትና ሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከተው ችሎት ነው። ዘገባው አክሎም የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ክሶችን ማቅረቡን አመልክቷል።  

ተከሳሹ በአራት ጠበቆቻቸው ተወክለው ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንደተነበበላቸው፤ በጠበቆቻቸው በኩልም የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው ጥያቄ መቅረቡም ተገልጿል። ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የዋስትና ጥያቄያቸውን ሊያስከለክሉ የሚችሉ ነጥቦችን ጠቅሶ ተከራክሯል። ፍርድ ቤቱ ዋስትናን በሚመለከት መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱንም ዘገባው አመልክቷል።

 

ዳሬሰላም፤ ታንዛኒያ ውስጥ በጎርፍ አደጋ 155 ሞቱ

ታንዛኒያ ውስጥ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ155 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ አስታወቁ። ኤሊኞ የተሰኘው የአየር ጠባይ ክስተት ባስከተለው ኃይለኛ ዝናብ እና የመሬት መንሸራተት በሀገሪቱ በርካታ ግዛቶች ቤቶች፤ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ሰብል መጎዳቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ካሲም ማጃሊዋ ለፓርላማው ተናግረዋል። ማጃሊዋ እንደተናገሩት ኃይለኛ ንፋስ ያገዘው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት በበርካታ የታንዛንያ ግዛቶች ከባድ ጉዳት አድርሷል። በዚህም ሕይወት መጥፋቱን፣ ከ51 ሺህ በላይ ቤተሰቦች እና 200 ሺህ ሕዝብ ለችግር መዳረጉንም ገልጸዋል። 236 ሰዎች መጎዳታቸውን፤ መንገዶች፤ ድልድዮች እና የባቡር ሃዲዶች ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውንም ዘርዝረዋል። ኤሊኞ የተሰኘው የአየር ጠባይ ክስተት በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በተጎዱ የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የፈረንሳይ የዜና ወኪል በላከው ዜና ጠቅሷል።

 

ካኖ፤ ከናይጀሪያ እስር ቤት 119 እስረኞች ማምለጣቸው

ማዕከላዊ ናይጀሪያ ውስጥ ከባድ ዝናብ በአንድ እስር ቤት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ 120 የሚሆኑ እስረኞች ማምለጣቸው ተሰማ። ትናንት ረቡዕ ዕለት ለሰዓታት የወረደው ዝናብ በዋና ከተማ አቡጃ አቅራቢያ የሚገኘውን እስር ቤት ሕንጻና አጥሩን ማፈራረሱ ነው የተገለጸው። አጋጣሚውን በመጠቀምም እስረኞቹ ሲያመልጡ የእስር ቤቱ ሠራተኞች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር አስሩን መያዝ እንደቻሉ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። የጠፉትን ፍለጋም መቀጠሉን አመልክቷል። የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ኅብረተሰቡ ያመለጡትን እስረኞች በማፈላለግ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል። የእስር ቤቱ ቃል አቀባይ አዳሙ ዱዛ፤ በቅኝ ግዛት ዘመን የተገነባ ነው ያሉት ያረጀው የእስር ቤቱ ይዞታ ለተፈጠረው ችግር መንስኤ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

 

አዲስ አበባ፤ ዓለም አቀፍ የወባ መከላከል ቀን

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም የወባ በሽታ ስርጭት በእጅጉ መስፋፋቱ እና የሚያደርሰው ጉዳትም እየከፋ መምጣቱ ተገለጸ። ዛሬ የሚታሰበውን ዓለም አቀፍ የወባ መከላከል ቀንን በማስመልከት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የአየር ንብረት መለወጥ እና የግጭቶች መስፋፋት ለወረርሽኙ ስርጭት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አመልክቷል።  የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የተጠቀሰው ሁኔታ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ ሚኒስትር ዴኤታው የወባ በሽታን የሚያመጡ ትንኞች ለመከላከያ ከሚረጨው ኬሚካል ጋር እየተላመዱ መምጣት ሌላው ለወባ ስርጭት መባባስ ዓይነተኛ ሚና መጫወቱ ንም ነው ያመለከቱት። ከቆዳ ስፋቷ 75 በመቶ የሚሆነው ለወባ ትንኞች መራቢያነት አመቺ እንደሆነ በሚነገርባት ኢትዮጵያ 69 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በዚህ አካባቢ እንደሚኖር የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በአሁኑ ወቅት ለወባ ስርጭት መባባስ በሽታው ጠፍቷል የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ አደገኛ መሆኑንም አስረድቷል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወረርሽኙን በአደገኛ ሁኔታ መስፋፋት አስመልክቶም ለቀጣይ ሦስት ወራት የሚቆይ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ያስችለኛል ያለውን ዘመቻ ማወጁን መግለጫውን የተከታተለው ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ በላከው ዜና ጠቅሷል።

 

ዋሽንግተን፤ 18 ሃገራት ሃማስ ታጋቾችን እንዲለቅ ጠየቁ

18 ሃገራት ሃማስ በእጁ የሚገኙ ታጋቾችን እንዲለቅ ጥሪ አቀረቡ። ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ፤ ፈረንሳይን ጨምሮ 18ቱ ሃገራት በጋራ ባቀረቡት ጥሪ ባለፈው መስከረም 26 ቀን ሃማስ ያገታቸውን ወገኖች እንዲለቅ ጠይቀዋል። ከ200 ቀናት በላይ በሃማስ ይዞታ ጋዛ ውስጥ ከሚገኙ ታጋቾች የየሃገራቱ ዜጎችም እንደሚገኙበት አመልክተዋል። ታጋቾቹ እንዲለቀቁም በመካሄድ ላይ ያለውን የድርድር ጥረት እንደሚደግፉም ሃገራቱ በመግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። መግለጫው አክሎም ድርድሩ የታጋቾቹን መለቀቅ፣ በጋዛም አስቸኳይ እና ለረዥም ጊዜ የተጠበቀው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ፤ አስፈላጊው ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ እንዲሁም ግጭት እንዲቆም በሚለው ላይ ማተኮሩን አመልክቷል። በተጠቀሰው ቀን በሃማስ ከታገቱት 240 ሰዎች፤ 129 የሚሆኑት ሳይሞቱ እንዳልቀረ በእስራኤል በኩል ግምት መኖሩን ዘገባዎች ያሳያሉ።  

 

ሞስኮ፤ ሩሲያ የዩክሬን የረዥም ርቀት የጦር መሣሪያ ማግኘት

ሩሲያ ዩክሬን የትኛውንም ዓይነት የረዥም ርቀት የጦር መሣሪያ ብትታጠቅ የግጭቱ ውጤት ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንደማይኖር አስታወቀች። ከክሬምሊን ይህ አስተያየት የተሰጠው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዩክሬን በአህጽሮተ ቃል ATACMS የተሰኘውን ሚሳኤል በስውር የመላኩና መሣሪያውን በያዝነው ወር ከታሰበበት ስፍራ መድረሱን ከተሰማ በኋላ ነው። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ ስለጉዳዩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በግጭቱ በቀጥታ እየተሳተፈች መሆኑን በማመልከት ለዩክሬን የሚደረገው ወታደራዊ እርዳታ የሚያመጣው ለውጥ የለም ነው ያሉት።

«ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ግጭት በቀጥታ እየተሳተፈች ነው። እስካሁን ሲያቀርቡ የነበረውን የጦር መሣሪያ ዓይነትና ስልት ወደማሳደጉ እየሄዱ ነው።» ይህ በወታደራዊ ልዩ ዘመቻው ውጤት ላይ የሚያመጣው መሠራዊ ለውጥ አይኖርም። ግባችንን እናሳካለን። ሆኖም ግን ይህ ለዩክሬን ለራሷ ተጨማሪ ችግር ይፈጥራል።»

የተጠቀሰው ATACMS የተሰኘው ሚሳኤል እስከ 300 ሜትር ርቀት ተወንጭፎ ኢላማውን ሊመታ የሚችል መሣሪያ እንደሆነ ነው የተገለጸው። የተባለው ሚሳኤል ለዩክሬን መሰጠቱን የመከላከያው ዘርፍ ቃል አቀባይ ማረጋገጣቸውንም  አዣንስ ፍራንስ ፕረስ በዜናው ጠቅሷል።   

 

ባንኮክ፤ ታይላንድ ውስጥ በሙቀት ማዕበል 30 ሰዎች ሞቱ

በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ታይላንድ ውስጥ በሙቀት ማዕበል ቢያንስ 30 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ የሀገሪቱ መንግሥት ዛሬ አስታወቀ። በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚሊየኖች የሚገመቱ ሰዎች ባለተለመደ መልኩ ሞቃት በሆነው የአየር ጠባይ ለችግር መጋለጣቸው ተገልጿል። በአካባቢው በዚህ ሳምንት በታየው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ፊሊፒንስ ውስጥ ትምህርት ቤቶች ተዘግበዋል። ሕንድ ውስጥ ምርጫ ቅስቀሳ  በማድረግ ላይ የነበሩ ሚኒስትር ቀልባቸውን ስተው መውደቃቸው ነው የተገለጸው። ሌላው ቀርቶ ሞቃቱ የአየር ሁኔታ ተራራማ በምትባለው ኔፓል ሳይቀር የጤና ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን የሙቀቱ መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ በመነገሩ ሀኪም ቤቶች በዛሬው ዕለት በተጠንቀቅ እንዲጠባቀቁ ታዘዋል። ተመራማሪዎች የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው የሙቀት ማዕበል ረዥም ጊዜ እንዲቆይ እና ተደጋግሞ እንዲከሰት እያደረገው መሆኑን ይናገራሉ።

 

ኢስታንቡል፤ ከሰሀራ የተነሳ አቧራ ቱርክን ማዳረሱ

ከሰሀራ የተነሳ አቧራ ቱርክን ማዳረሱ ተሰማ። የሀገሪቱ የሜትሪዮሎጂ አገልግሎት አየሩን በሞላው አቧራ ምክንያት የጤና እክል ሊያጋጥም እንደሚችል እና በመጓጓዣዎች ላይም አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል። በተለይም የመተንፈሻ አካላት የጤና ችግር ያለባቸው ወገኖች ከቤት እንዳይወጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። አንካራን ጨምሮ አሽከርካሪዎች አቧራው እይታን እንደሚያውክ በማስተዋል እንቅስቃሴያቸው መገደቡን የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ ዘግቧል። የአቧራው ደመና በኢስታንቡል እና ኢዝሚር ከተሞችም አየሩን መበከሉ ነው የተገለጸው። በዚህም ምክንያት በአንዳንድ ከተሞች ትምህርት ቤቶች እንደሚዘጉ፤ የመጓጓዣ እንቅስቃሴም ሊቋረጥ እንደሚችል ተነግሯል። በተመሳሳይ የየደቡባዊ ግሪክ ሰማይም በዚሁ አቧራ መታፈኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።