1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የተሳታፊ ልየታ ሊጀምር ነ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 2015

"በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉ" ሲል ገልጾ የነበረው የምክክር ኮሚሽኑ በመጪው 2016 ዓ. ም አጋማሽ ጥር ዋናውን ጉባኤ ለማካሄድ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ዛሬ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4VUw8
የኢትዮጵያ ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ፅሕፈት ቤት።ኮሚሽኑ የአዲስ አበባ ተሳታፊዎችን ይለያል
የኢትዮጵያ ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ፅሕፈት ቤት።ኮሚሽኑ የአዲስ አበባ ተሳታፊዎችን ይለያልምስል Solomon Muchie/DW

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የተሳታፊ ልየታ ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2016 ዓ.ም አጋማሽ ጥር ላይ ዋናውን የምክክር ጉባኤ ለማከናወን ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለፀ። 
ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ከዚህ በፊት በክልሎች ሲያደርግ የነበረውን የተሳታፊ ልየታ ሥራ በቀጣይ ቀናት በአዲስ አበባ በ119 ወረዳዎች እንደሚጀምር አስታውቋል ።
ለዚሁ ሥራ "እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ" የተባሉ አካላትን መለየታቸውንም ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ሥላሴ ዛሬ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልፀዋል።
"እነዚህም የኢትዮጵያ  ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ  ዕድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የወረዳ አስተዳደር ናቸው" ብለዋል።

የተባባሪ አባላት ገለልተኝነት

ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው የሽግግር ፍትሕ እና የኮሚሽኑ ሥራ የሚጋጭ አለመሆኑን ከቀረበለት ጥያቄ በመነሳት ምላሽ ሰጥቷል። በተሳታፊ ሥራው ልየታ ውስጥ አደረጃጀት የሌላቸው የተባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተፈናቃዮችም እንደሚሳተፋ ተነግሯል። የእነዚህን አካላት ገለልተኝነት በተመለከተ እንዲሁም ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኃላፊነት ለሌሎች እያጋራ ስለመሆን አለመሆኑ የተጠየቁት ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ተከታዩን መልሰዋል።
"ይህንን ሥራ ለመወጣት በህብረተሰቤ ዘንድ እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ አካላትን ይህንን ሥራ እንዲያግዙን አድርገናል። ተባባሪ አካላት ማለት እምነት የሚጣልባቸው፣ በማህበረሰበ ዘንድ ታማኝ ናቸው ተብሎ የሚታሰቡትን ነው" 

ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ
ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ከዚህ በፊት በክልሎች ሲያደርግ የነበረውን የተሳታፊ ልየታ ሥራ በቀጣይ ቀናት በአዲስ አበባ በ119 ወረዳዎች እንደሚጀምር አስታውቋል ።ምስል Solomon Muchie/DW

ጦርነት እና የኮሚስኑ ስኬት

በመግለጫው ኢትዮጵያ በጦርነት እየታመሰች የእናንተ ሥራ በስኬት ይጠናቀቃል፣ ተገቢውን ሂደትስ ያልፋል ወይ ብሎ ማመን እንዴት ይቻላል ? ተብሎም ጥያቄ ቀርቦ ነበር። የኮሚሽኑ የበላይ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ ተቋማቸው የግጭቶች መፍትሔ ፈላጊ አካል ለመሆን ይልቁንም ለዚሁ ስኬት እየጣረ መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተሳታፊዎች ልየታ ሥራ ላይ መሠረታዊ የሚባል ባይሆንም መጠነኛ የአሰራር ማሻሻያ ስለመደረጉ ተገልጿል።

ደም አፋሳሽ ውግያዎች ለስራው ዕንቅፋት ስለመሆናቸው

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ. ም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ "የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረንጴዛ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ" ሲል አስቸኳይ ያለውን ሀገራዊ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
"በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉ" ሲል ገልጾ የነበረው የምክክር ኮሚሽኑ በመጪው 2016 ዓ. ም አጋማሽ ጥር ዋናውን ጉባኤ ለማካሄድ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ዛሬ አስታውቋል። 

ኮሚሽኑ እስካሀን በአምስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊዎች ልየታ ሥራ አከናውኛለሁ ብሏል።

ሰለሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ማንተጋፍቶት ስለሺ