1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሳሰቢያ እና የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ምላሽ

ሰኞ፣ ሐምሌ 10 2015

ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በቀጣይ ዓመት ለሚጀመረው ሀገር አቀፍ ምክክር በየክልሎች እያደረገው ባለው «የተሳታፊ እና የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦች ልየታ» ሥራ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች አብረውት እየሠሩ መሆኑን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4U0Zo
Äthiopien Kommission für den nationalen Dialog
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሳሰቢያ እና የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ምላሽ

ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በቀጣይ ዓመት ለሚጀመረው ሀገር አቀፍ ምክክር በየክልሎች እያደረገው ባለው «የተሳታፊ እና የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦች ልየታ» ሥራ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች አብረውት እየሠሩ መሆኑን አስታወቀ። በሌላ በኩል የመንግሥት የወረዳ ተሿሚዎች እና የገዢው ፓርቲ አባላት የውይይት ተሳታፊ ሆነው እየተለዩ መሆኑን እና ስም ዝርዝር እና ሰዎቹ የሚሠሩባቸው የመንግሥት ተቋማት ጭምር የፖለቲካ ድርጅት አባል ካልሆኑ ግለሰቦች ጥቆማ እየደረሰው መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እርምት እንዲደረግ ጠይቋል። በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሔ ለማምንጨት የሚያግዘው ብሔራዊ ምክክር አምስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን አሁን በሦስተኛና በአራተኛ ደረጃዎች ማለትም በሂደት እና ትግበራ ሥራ መሃል ላይ መሆኑን አስታውቋል። ኮሚሽኑ    በየክልሎች የጀመረው የልየታ ሥራ ግን የፖለቲካ ተሳትፎ እና የድርጅት አባልነት ውስጥ በማይገኙ ግለሰቦች ሳይቀር በልየታው የመንግሥት ተሿሚዎች ያለ አግባብ እየተካተቱ ነው የሚል ጥቆማ እያቀረቡ መሆናቸውን በመጥቀስ ተስተዋሉ የተባሉ የገለልተኝነት ጥያቃዎች እርምት እንዲደረግባቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ራሔል ባፌ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ይህ ጥቆማ ከዜጎች ሲቀርብ ቅሬታ የሚቀርብባቸው ሰዎች ስም ዝርዝር እና የሚሠሩባቸው የመንግሥት ተቋማት ጭምር አብረው መሆኑንም ገልፀዋል። ይህ ሕዝብ ለጋራ ምክር ቤቱ እየላከው ነው የተባለው ጥቆማ «የሕዝቡን ዝግጅት አሳይቶናል" ያሉት ዶክተር ራሔል መንግሥት ይህንን መድረኩ ካመቻቸው ተስፋ ሰጪ ነው» ብለዋል። ለዚህ ምክንያት ያሉት ደግሞ ብሔራዊ ምክክሩ «የእኔ ነው የሚል ትውልድ እየተፈጠረ ነው» የሚል ነው። «ይንንን ጉዳይ መንግሥት ቆም ብሎ ሊያየውና ሊመረምረው ይገባልም» ብለዋል።

ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህ ችግር መስተዋሉን አልሸሸገም። ከኮሚሽኑ ጋር ተባባሪ ሆነው የሚሰሩትን የማሰልጠን ሥራ አየተከናወነ ነው ያሉት ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች መሠል ህፀፆች እንዲታረሙ አብረዋቸው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል። ሌላ በኩል አምስት በጋራ የሚሠሩ መሆናቸውን ያስታወቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ከብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራ ጋር «የማይቀላቀል እና ሊምታታ የማይገባው» ያሉት «አስቸኳይ ሀገር የማዳን» ውይይት እንዲካሄድ ባለፈው ሳምንት ጠይቀዋል። ይህንን አስመልክቶ የተጠየቁት ዶክተር ራሔል መፍትሔው ከውስጥ መሆኑ የሚበጅ ነው ይላሉ። የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አባሉ ዶክተር ዮናስ አዳዬ «የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በዋናነት በኢትዮጵያውያን ነው» በማላት ምሳሌ ጭምር አጣቅሰው ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ችግር አፈታት ላይ እንዲያተከረ ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል።

 ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር