1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አላማጣ በ10 ሺህዎች እየተፈናቀሉ ነው

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እንደገና የተቀሰቀሰው የአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ነዋሪዎችን በገፍ ማፈናቀል መጀመሩ ተገለጠ ። ወደ 10ሺህ የሚሆኑ የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ቆቦ ከተማ ደርሰዋል ተብሏል ።

https://p.dw.com/p/4equM
Äthiopien Southern Tigray, Alamata
ምስል Alemenew Mekonnen Bahardar/DW

እንደገና የተቀሰቀሰው የአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እንደገና የተቀሰቀሰው  የአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት  ነዋሪዎችን በገፍ ማፈናቀል መጀመሩ ተገለጠ ። ወደ 10ሺህ የሚሆኑ የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ቆቦ ከተማ ደርሰዋል ተብሏል ። ይህንኑም ተፈናቃዮችና የራያ አላማጣ አስተዳደር ዐስታውቀዋል ።  የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕስ መስተዳድር በበኩሉ፦ «ግጭቱን እየቀሰቀሱ ያሉት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይተገበር የሚፈልጉ አካላት ናቸው» ብለዋል ።

ባለፈው ቅዳሜ በራያ አላማጣ ወረዳ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን አዲስ ግጭት በመስጋት የራያ አላማጣና የኮረም ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀል መጀመራቸውን የተፈናቀሉ ሰዎችና የወረዳው አስተዳደር አመልክተዋል፡፡

ትናንት ከአላማጣ ከተማ ተፈናቅለው ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ  ከተማ ከደረሱ ተፈናቃዮች መካከል አንዱን አስተያየታቸውን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ "ትናንት የተፈጠረው፣ የመማር ማስተማርና ሌሎችም የቢሮ ስራዎች ነበሩ፣በኋላ ላይ ግን ሕዝቡ እንዳለ ተደናገረ ቤቱን ጥሎ ወጣ፣ ወደ ቆቦ ነው ሰው የሄደው፣ ወዴት ናችሁ? የት ናችሁ? ያለን እንኳ የለም፣ ወደ ወገናቸው ሲመጡ ከየት እንደተተኮሰ ባታወቅም ተተኩሶባቸው የተገደሉ ተፈናቃዮችም ነበሩ” ብለዋል፡፡

ተፈናቅለው ቆቦ ከተማ ቢደርሱም የተቀበላቸው አካል እንደሌለና በየቦታው ማደራቸውን ነው እኚሁ ተፈናቃይ የሚናገሩት፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ብዙዎች በየበረንዳውና በየጥጋጥጉ ያደረ ሲሆን ገንዘብ ያላቸው ደግሞ አልጋ ይዘው አድረዋል፣ ነጋዴዎች ደግሞ ዋጋ በሁሉም ነገር መጨመራቸውን ገልጠዋል፡፡

ከራያ አላማጣ ግጭቱ ሰሞኑን ከተቀሰቀሰበት አስታምባ፣ ጋርጃሌ ቀበሌ ተፈናቅለው ቆቦ ከተማ የሚገኙ ሌላ ተፈናቃይ ባገኙት ተሸከርካሪ ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውንና መንገድ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ተፈናቃዮች እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡ በአንድ መኪና እስከ 70 እና 80 ሰዎች እተሳፈሩ አካባቢያቸውን ለቅቀዋል ነው ያሉት፡፡

ትናንት ከኮረም ከተማ ተፈናቅለው ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ የደረሱ ተፈናቃይ እንዳሉት ቁጥሩን በትክክል ማወቅ ባይችሉም በርከት ያለ ሰው ከኮረም እየተፈናቀለ ነው ብለዋል፣ የፀጥታ ኃይሎች ተፈናቃዮን ሲመልሱም መመልከታቸውን ገልጠዋል፡፡

የወሎ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሊቀመንበርና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ "ችግሮች በህገመንግስቱ መሰረት እንዲፈቱ የኢትዮጵያ መንግስትና የትግራይ ባለስልጣናት የተስማሙበት የፕሪቶሪው ስምምነት” በግልፅ ተጥሶ የትግራይ ታጣቂዎች ጦርነት ከፍተውብናል ብለዋል፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር  የአላማጣና አካባቢው ነዋሪም ተፈናቅሎ ወደ ቆቦ ሄዷል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ ቀደምም በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ግጭት በርካቶች ተፈናቅለው ነበር ። ፎቶ፦ ከማኅደር
ከዚህ ቀደምም በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ግጭት በርካቶች ተፈናቅለው ነበር ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Alamata City Youth League

የትግራይ ተዋጊዎች አብዛኛውን የወረዳውን አካባቢ እየተቆጣጠሩ እንደሆነ ነው አቶ ኃይሉ የሚናገሩት፣ ቀደም ሲልም ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ለሚመለከተው አካል ሲያሳውቁ እንደነበር ከንቲባው አስታውሰው የሚሰማ በመጥፋቱ ነው ችግሩ የተከሰተው ብለዋል፡፡

ከፌደራሉም ሆነ ከክልሉ መንግስት እስካሁን ጥቃቱን በተመለከተ የተባለ ነገር ስለመኖሩ የሰሙት ነገር እንደሌላ አቶ ኃይሉ ገልፀዋል፡፡ አንድ የቆቦ ከተማ ነዋሪ፣ "ቆቦ ከተማ ከትናንት ቀን 10 ሰዓት ጀምሮ በአላማጣ ተፈናቃዮች ተጥለቅልቃለች” ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ድርጊቱን እስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰራጩት ጽሑፍ፣ "ሁለቱ ወገኖች (መንግስትና የትግራይ ባለስልጣናት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት  ተግባራዊ ለማድረግ እያደረጉት ያለውን አዎንታዊ ግንኙነት ለማደናቀፍ የፈለጉ "የስምምነቱ ጠላቶች” የፈጠሩት ነው” ብለዋል፡፡

ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት  ለአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ያደረግሁት የስልክ ጥሪ  ስልካቸው መነሳት ባለመቻሉ አልተሳካልኝም፡፡ የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፋንታው ውዝግብ በሚነሳባቸው የትግራይና የአማራ ክልል አካባቢዎች መፍትሄ በተመለከተ በቅርቡ ጠይቀናቸው፣

"ሕዝባችን ሰላም ወዳድ ነው፣ የትግራይ ሕዝብ ወንድም እህታችን ነው፣ ከወንድም እህት ሕዝብ ጋር አብረን በሐይማኖት፣ በባህል በጋብቻ፣ በኢኮኖሚ ከተሳሰረው ሕዝባችን ጋር ዳግም ወደ ጦርነት አንገባም፣ ስለዚህ (ችግሮች) በሰላማዊ መንገድ እንዲያልቁ እንፈልጋለን፣ በተቀመጠው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ጉዳዮቹ መታየት አለባቸው፣ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ይህን እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፡፡” ብለው ነበር፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ