1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአላማጣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለስ ፍላጎት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 17 2015

ከአላማጣና አካባቢው ተፈናቅለው ከአንድ ዓመት በላይ በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ጃራ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ተፈናቃዮች አሁን ወደ አካባቢያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ እየገለጹ ነው። መንግሥት በበኩሉ «ጊዜ ስጡኝ» ብሏል።

https://p.dw.com/p/4Ikln
Alamata Flüchtlingsunterkünfte Jara in Region Amhara
ምስል Alamata City Youth League

ከአንድ ዓመት በፊት ህወሓት አላማጣንና አካባቢውን እንደገና ሲቆጣጠር፣ «ታጣቂው ኃይል ጥቃት ሊያደርስብን ችላል» በሚል ስጋት፣ በአብዛኛው የአማራ ማንነት ያላቸው ሰዎች፣ አካባቢያቸውን ጥለው በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ በጃራ የተፈናቃዮች ጣቢያ ቆይተዋል። ሰሞኑን የመከላከያ ሠራዊትና ተባባሪዎቹ አላማጣንና አካባቢውን ከህወሓት ነፃ ካደረጉ በኋላ ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢቸው መንግሥት እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ አቅም ያላቸው በራሳቸው ጊዜ መጠለያ ጣቢያውን እየለቀቁ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል፤ አሁን በመጠለያ ጣቢያው ምንም ዓይነት አገልግሎት እንደሌለና የፀጥታ ችግሮችም እንዳሉባቸው ስጋታቸውን ገልፀዋል። «መመለስ እንፈልጋለን መንገድ ዝግ ነው ስላሉን ነው ቆቦ ላይ፣ እንደገና እዚህ ህክምና የለ፣ ምን የለ ፀጥታ አካል የለ፣ አሁን ህዝቡ እንደገና ከጊዜ ወደ ጊዜ አሁን “ነግቶ” እንኳን ሰላም መሆን አልቻለም እኛ በጣም ችግር ላ ነን ሰው ቢታመም ህክምና የለም፣ ከዚህ በፊት ህክምና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ  የሉም፣ የፀጥታ አካል የለም፣ አሁን የሚረዳን ያለው ከመጀመሪው ጀምሮ የድሬ ሮቃ ህዝብ ነው፣ ሚሊሺያ መድቦ ዙሪያውን የሚጠብቀን እስ ነው።»

Alamata Flüchtlingsunterkünfte Jara in Region Amhara
የአላማጣ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ጃራ የስደተኞች መጠለያምስል Alamata City Youth League

ሌላዋ ተፈናቃይም በመጠለያ ጣቢያው የቀሩት በአብዛኛው ሴቶች፣ ሕጻናትና አቅመ ደካሞች በመሆናቸው ለሌላ ችግር ከመጋለጣችን በፊት መንግሥት ይድረስልን ነው ያሉት፡፡

« የምንፈልገው ወደ አገራችን መሄድ ብቻ ነው፣ ልጆች ይዘናል ምናለ ብንወጣ? ምክንያቱም ህክምና የለም፣ ምግብ ቤት ተዘግቷል ምንም መጠቀም አልቻልንም፣ እኛ ልጆች የያዝን ሰዎች በጣም ተሰቃይተናል፣ ምንም አማራጭ የለንም፣ እንዳንሄድ መንገድ ዝግ ነው እተባልን ነው፣ መንግሥት ምን እንደሚጠብቅ አናውቅም፣ ምንም ነገር አቅርቦት የለም ውሀም ቆሟል፣ ዛሬ ከግቢው ስምንት መኪና ሙሉ ተፈናቃይ ሄዷል፣ ትናንትም ተመሳሳይ፣ ህዝቡ እየሄደ ነው፣ የቀረው ልጅ ያለው፣ ደካማው ነው።»

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
የአላማጣ ተፈናቃዮች ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ብዙዎቹ ተፈናቃዮች ካለባቸው ስጋት አንፃር መጠለያ ጣቢያውን እየለቀቁ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመው መንግሥት በአፋጣኝ እንዲመልሳቸው ነው የሚጠይቁት። በመጠለያ ጣቢያው የተሟላ ነገር ማግኘት ስለማይችሉ መንግሥት ካልደረሰላቸው ኃላፊነት ወስደው በራሳቸው መንገድ ወደ ቀያቸው ለመመለስ መወሰናቸውንም የተናገሩ አሉ። የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ሰኢድ ተፈናቃዮቹ የሚያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ገልጠዋል። ሆኖም ከዞን አስተዳደር ጋር በመነጋገር ወደ ቄቸው በቅርቡ ይመለሳሉ ብለዋል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በራሳቸው መንገድ ከመጠለያ ጣቢያው መውጣታቸውንም አመልክተዋል፡፡በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ አወል ሀሰን እንደተባለው በራሳቸው ከመጠለያ ጣቢያው የለቀቁ ከ4 ሺህ እንደማይበልጡ ጠቅሰው ሆኖም ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ «የተባበሩት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) የትራንስፖርት በጀት አዘጋጅቶ ለማጓጓዝ ታስቧል፣ የተወሰነ ሰው መውጣት ጀምሯል እንደተባለው፣ ግን አመቻችተን የተወሰነ ዕቃ ባለፈው ስለተዘረፈባቸው ምትክ ሰጥተናቸው ይዘው እንዲሄዱ የሚል ሀሳብ ተነስቷል፣ እሱን እጠበቅን ነው፣ ለማጓጓዝ አሁን በዝግጅት ላይ ነው ያለነው፣ ሲሄዱ ባዶ ቤት እንዳገቡ የተወሰነ ዕቃ ይዘው እንዲሄዱ ታስቦ ነው፣ በራሳቸው እንዳይሄዱ ለማጓጓዝ ታስቧል አሁን።» ብለዋል። ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉና በአብዛኛው የአማራ ማንነት ያላቸው 30,000 ያህል ተፈናቃዮች ይኖሩበታል።

 ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ