1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል ውስጥ "በእሥር ላይ ናቸው" የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3 2016

በሐረር ፣ ሚዛን አማን እና ነገሌ ቦረና አካባቢ የሚኖሩ የሠራዊቱ አባላት ቤተሠቦች እንዳሉት፤ ቤተሰቤቻቸው "በጦርነቱ ሞተዋል" ተብለው በመንግሥት መርዶ ተነግሯቸው ነበር። ይሁንና ይህ ከሆነ በኋላ በቀይ መስቀል በኩል ከወታደር ቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ እንደተገናኙና አሁንም አልፍ አልፎ ስልክ እንደሚደውሉላቸው የወታደሮቹ ቤተሰቦች ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4ef2X
Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

ትግራይ ውስጥ "በእሥር ላይ ናቸው" የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት

በትግራዩ ጦርነት ወቅት በክልሉ ተዋጊ ኃይሎች ተይዘው በእሥር ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጉዳይ እጅጉን እንዳሳሰባቸው ቤተሰቦቻቸው ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። በሐረር ፣ ሚዛን አማን እና ነገሌ ቦረና አካባቢ የሚኖሩ የሠራዊቱ አባላት ቤተሠቦች እንዳሉት፤ ቤተሰቤቻቸው "በጦርነቱ ሞተዋል" ተብለው በመንግሥት መርዶ ተነግሯቸው ነበር። ይሁንና ይህ ከሆነ በኋላ በቀይ መስቀል በኩል ከወታደር ቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ እንደተገናኙና አሁንም አልፍ አልፎ ስልክ እንደሚደውሉላቸው የወታደሮቹ ቤተሰቦች ነግረውናል።በጉዳዩ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው ልናገኛቸው አልቻልንም። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፈው መጋቢት 2016 ዓ .ም "በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በእሥር ላይ የቆዩ" ያላቸውን 212 የመከላከያ ሠራዊት አባላት መልቀቁን አስታውቆ ነበር።በመቀሌ ወህኒ ቤት የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጉዳይ

የወታደር ቤተሰቦች ምን አሉ ?

"የሰሜን ኢትዮጵያ" በሚል በሚታወቀውና በፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት በተቋጨው ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን ባደቀቀው ጦርነት ተሳታፊ ከነበሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ከ 1997 ዓ.ም ጀምሮ ጦሩን ያገለገሉት የነገሌ ቦረናው ሰው ይገኙበታል። የእኒህ ሰው የእህት ባል የሆኑትና ሁኔታውን የነገሩን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ቤተሰብ ወታደሩ መንግሥት እንደሞተ ሲያረዳቸው የወታደሩ እህት በድንጋጤ መሞታቸውን ነግረውናል።

"ሞቷል ተብሎ ደብዳቤ ተልኮ ፣ ከዚያ በድንጋጤ እህቱም ሞተች። አንድ ወንድሙም ሞተ ፤ በድንጋጤ። አሁን አጋጣሚ ቀይ መስቀሎች ናቸው እኔ ጋር የደወሉት።" ብለዋል።በተመሳሳይ አሁን ከባለቤታቸው ቤተሰቦች ተጠግተው ሐረር እንደሚኖሩ የነገሩን ሴት ባለቤታቸውን እዚያው ትግራይ አግብተው ልጆች ወልደው ይኖሩ እንደነበር ገልፀዋል።
አሁን ጭንቀት ላይ መሆናቸውን የገለፁት እኒሁ ሴት መረጃዎች ተጣርተው ሀቁ እንዲገለጽላቸው አቤት ብለዋል።

በትግራዪ ጦርነት ወቅት በመሆኒ ከተማ አንዲት ሴት በታንክ አጠገብ ስታልፍ
በትግራዪ ጦርነት ወቅት በመሆኒ ከተማ አንዲት ሴት በታንክ አጠገብ ስታልፍ ምስል Eduardo Soteras/AFP

"ባለቤቴ ሻለቃ ነው። 25 ዓመት ነው ትግል ከገባ። ሞቷል ብሎ መንሥትም ነግሮን ነበር። ወረቀት መጥቶልናል። ሞቷል ብሎ ከነገረን በኋላ አንድ ዓመት ተቀምጠን ነው አለ የሚባል ወሬ የሰማነው።" ከሚዛን አማን ቤተሰባቸውን ጨምሮ ሌሎች 15 ሰዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ አሁንም በእሥር ላይ መሆናቸውን መስማታቸውን የገለፁልን ሌላ ቤተሰብ ወታደሮቹ የሚገኙት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ማወቃቸውን ገልፀዋል። ትግራይ ውስጥ ታፍነው የነበሩ የሠራዊት አባላት  
"ሞቷል ተብሎ መርዶ ደርሶናል። ሰሞኑን ሲደውል ደንግጠን ከምን አንፃር ነው እያልን ነው ያለነው። ሞተ የተባለው ሰኔ 17 2013 ነው። እኛ የተረዳነው ሰኔ 17 2014 ነው።" ብለዋል።

የተለቀቁት የሠራዊቱ አባላት

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር "በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በእሥር ላይ የቆዩ" ያላቸውንና ከፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት በፊት በትግራይ ኃይሎች ተይዘው የነበሩ 212 ምርኮዎችን መልቀቁን ባለፈው መጋቢት አስታውቋል። ውሳኔው አዲስ አበባ ላይ የተደረገን የስምምነቱ አፈፃፀም ግምገማ ተከትሎ የተደረሰ መሆኑንም ገልጾ ነበር። አሁን ያልተፈቱ የተባሉትን በተመለከተ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ደጋግሜ ብደውልም ስልካቸው አይሰራም።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላና አቶ ጌታቸው ረዳ በናይሮቢ ስለ ፕሪቶሪያው የሰላምm ስምምነት አተገባበር በተነጋገሩበት ወቅት
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላና አቶ ጌታቸው ረዳ በናይሮቢ ስለ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር በተነጋገሩበት ወቅት ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

በጉዳዩ ላይ የኢሰመጉ ማብራሪያ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ( ኢሰመጉ ) "የአካል ነጻነት መብት" በሚል መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ "በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ተነስቶ የነበረውን የትጥቅ ግጭት ተከትሎ በተለያዩ ጊዜዎች ውስጥ ግጭቱ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እስከሚገባደድ ጊዜ ድረስ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት በትግራይ ክልል ውስጥ ታስረው እንደነበረ እና እነዚህ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አንዳንዶቹ ከሁለት አመት በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ እንዲሁም እነዚህ በእስር ላይ ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ" ገልጿል። ጥሪ የተደረገላቸው የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት 

ተገቢውን የፍርድ ሂደት በመከተል ምንም አይነት ፍርድ ሳያገኙ ቆይተው እንደነበርና ይህንንም ጉዳይ ሲከታተል መቆየቱን የገለፀው ኢሰመጉ "አሁንም በክልሉ በእስር የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖራቸውን" መረዳቱን አስታውቋል። "በእስር ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የምግብ፣ የመጠጥ ውኃ እና የልዩ ልዩ መሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት እንዳለ" መገንዘቡን የመብት ድርጅቱ አስታውቋል።

ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ 
ሸዋዬ ለገሠ