1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ግድያ ምርመራ የኦነግ ሥጋት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባለፈው ሳምንት በትውልድ አከባቢያቸው መቂ የተገደሉት የአቶ ቤቴ ዑርጌሳ የግድያ ምርምራ ላይ እምነነት እንደማኖረው ዐስታወቀ ። ኦነግ ይህን ያለው መንግስት 13 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጾ የሂደቱን መጀመር በይፋ ማሳወቁን ተከትሎ ነው ።

https://p.dw.com/p/4er7x
Äthiopien Beti Urgessa
ምስል Private

በበቴ ዑርጌሳ ግድያ የምርመራ ሂደት የኦነግ ስጋት

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባለፈው ሳምንት በትውልድ አከባቢያቸው መቂ የተገደሉት የአቶ በቴ ዑርጌሳ የግድያ ምርምራ ላይ እምነነት እንደማኖረው ዐስታወቀ ። ፓርቲው ከሰሞኑ በይፋ ባወጣው መግለጫ፦ ይህን ያለው የፖለቲከኛውን ግድያ ለመመርመር መንግስት 13 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጾ የሂደቱን መጀመር በይፋ ማሳወቁን ተከትሎ ነው ።

የተጀመረው የመንግስት ምርመራ

ባለፈው ሳመንት ማክሰኞ ሌሊት ሚያዚያ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ ተገድለው አስከሬናቸው ረቡዕ ጠዋት ከመንገድ ተጥሎ የተገኘው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ለመመርመር 13 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ባለፈው ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዐስታውቆ ነበር ።

የመምሪያው ኃላፊው ረዳት ኮሚሽነር ታሪኩ ድርባባ በእለቱ ለክልሉ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ሲናገሩ ወንጀሉ በምርመራ ተለይቶ ይፋ እስኪሆን ድረስ ኅብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ጠይቀውም ነበር ።

በሂደቱ የኦነግ ስጋት

ይሁንና በዚህ የወንጀሉ ምርመራ ሂደት ላይ እምነት እንደሌለው ባወጣው መግለጫ የገለጸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)   በአቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ ተፈጸመ ላለው «አሰቃቂ» ግድያው በመንግስት የተጀመረው የምርመራ ሂደት አሳስቦኛል ብሏል ።

ኦነግ በመግለጫው የፖለቲከኛው ግድያ የሕገወጥነት እና ከሕግ ውጪ ግድያ በአገሪቱ እየተስፋፋ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ሲል የከሰሰ ሲሆን፤ የሂደቱን አሳሳቢነትም አስረድቷል ። በዚሁ ግድያ ምርመራ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ገለልተኝነትና ኃላፊነትም ያሳስበኛል ብሏል ። 

ፓርቲው ይህን ያለበትን ምክንያት በዶይቼ ቬለ የተጠየቁት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ "ሁሉም እንደሚያውቀው ጓዳችን አቶ በቴ ዑርጌሳ በዚሁ ስርዓት ነው ሲታሰር የነበረው ። በኛ በኩል ብዙ ጥያቄዎች አሉን ። አቶ በቴ ከዚህ በፊት ከሌሎች ከፍተኛ አመራር ጋር ታስሮ በቆየበት ጊዜ በሞት አፋፍ ላይ ባደረሰው ህምም ምክንያት ነበር ከእስር የወጣው ። ከዚያም እስከ ኅልፈቱ በእስር ቤት እና ፍርድ ቤት ስያመላልሱት ነበርና ፍትሕ ያረጋግጣሉ የሚል እምነት አጥተን ነው በዚህ ላይ መግለጫ ያወጣነው» ብለዋል ።

የኦነግ መግለጫ አቶ በቴ በኅልፈታቸው እለት ሌሊቱን መቂ ከተማ ውስጥ ካረፉበት አበበ ግራዝማች ከተሰኘ ማረፊያ ቤት በፀጥታ አካላት ተወስደው ክፉኛ መደብደባቸውን ተጨባጭ ማስረጃ አለኝ ይላል፡፡ በእለቱ በስፍራው የነበሩ የሆቴሉ ጥበቃ እስካሁን መሰወራቸው ጥርጣሬዬን አባብሷልም ብሏል ፓርቲው፡፡ ከዚያም አቶ በቴ በተሽከርካሪ ተጭነው መወሰዳቸውንና በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ኦነግ በመግለጫው አትቷል፡፡

አቶ በቴ በተሽከርካሪ ተጭነው መወሰዳቸውንና በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ኦነግ በመግለጫው ጠቅሷል
አቶ በቴ በተሽከርካሪ ተጭነው መወሰዳቸውንና በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ኦነግ በመግለጫው ጠቅሷልምስል Seyoum Getu/DW

የገለልተኛ ምርምራ ጥያቄ

በመሆኑም በግድያው ዙሪያ ገለልተኛ እና ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ሲል ፓርቲው ጠይቋል፡፡ ቃል አቀባዩ አቶ ለሚ በዚህ ላይ እንዳከሉትም፤ "ገለልተኛ የሆነ ዓለማቀፋዊ ወይም አህጉራዊ አሊያም እንደ ኢትጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያሉ ተቋማት በምርመራው ሂደት እንዲሳተፉልን እንፈልጋለን፡፡ ከየትኛውም የፖለቲካ ዓለማ ውጪ የሆኑ አካላት ነው ሂደቱን እንዲመረምርልን የምንፈልገውም» ብለዋል ።  ከፖለቲከኛው መቀበር በፊት  የምርመራ ቡድኑን ወደ ስፍራው የላከው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ከዚህ አንጻር አዎንታዊ ሚናውን እንደሚጫወት ኦነግ ያምናልም ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዘው ስለ ኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ ሁኔታ የተጠየቁት አንድ የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያ አሁን ላይ ለመገናኛ ብዙሃን የሚበቃ የተጠናከረ ሪፖርት ባይኖርም ኮሚሽኑ በጉዳዩ ላይ የራሱን ምርመራ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባለፈው ሳምንት የፖለቲከኛውን መገደል ተከትሎ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ የፀጥታ አካላት ምርመራውን አጠናቀው ትክክለኛ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እስኪያደርጉት ድረስ መሰረታዊ ካልሆኑ ውንጀላዎች ሁሉም አካላት እነዲቆጠቡ ሲል ማሳወቁ ኤዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ