1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስረኞች መፈታት፡ የኦነግ መግለጫ

ሰኞ፣ መጋቢት 9 2016

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ.ም. የተፈቱበትን ውሳኔ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አጣጥሎ ነቀፈ። ኦነግ በመግለጫው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በግፍ አፈናቅለዋል ያላቸው የቀድሞ ክልላዊ ፕሬዝዳንቱ ሲለቀቁ ክስ እንኳ ያልተመሰረተባቸው አመራሮቼ በእስር ላይ ይገኛሉም ሲል ውሳኔውን ተቃውሞታል፡፡

https://p.dw.com/p/4drlR
 Logo Oromo Liberation Front

የእስረኞች መፈታት፡ የኦነግ መግለጫ

ተቃውሞ በባለስልጣናቱ መፈታት ላይ 


የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)የቀድሞ ባለስልጣን ከእስር መለቀቅን በተቸበት በዚህ መግለጫው፤ ያለፍርድ እና ክስ በእስር ላይ የሚገኙትን የፓርቲው ባለስልጣነት መንግስት እንዲለቃቸውም ጠይቋል፡፡ ኦነግ በመግለጫው የቀድሞ የሶማሌ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሃመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) በኦሮሚያ እና ሶማሌ አዋሳን ላይ የሚገኙትን በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን በግፍ ያፈናቀለ ሲል በወንጀል መጠየቅ የነበረባቸው በለት ከሷል፡፡ ከአቶ አብዲ በተጨማሪ በተመሳሳይ እለት ከእስር የተለቀቁትን የቀድሞ ብረታብረትና ኢንጂነሪግን ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ኃላፊ የነበሩትን የሜጀር ጄነራል ክንፌ ዳኘው ከእስር የመለቀቅንም ውሳኔ ኦነግ ነቅፎ ነው ያጣጣለው፡፡ያለሕግ አግባብ የቀጠለዉ የኦነግ አመራሮች እስር
ፓርቲው በመግለጫው በተለይም የከፋ ሰብኣዊ መብት ጥሰት ፈጸሙ ያሏቸውን የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንትን ስነቅፍ እሳቸውን የለቀቀውን መንግስትንም ፍትህን በማጓደል ነው የወቀሰው፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብዲ ገመቹ በዚህ ላይ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ “በዚያን ጊዜ ያፈናቀሉት ህዝብ አሁንም ድረስ ዘርፈ ብዙ ችግር ላይ ነው የወደቁት፡፡ ታዲያ ይህን የፈጸሙ እኚህ ሰው ላይ ተጠያቂነት መስፈን ስገባው ለፖለቲካ ጥቅም ተለቀዋል” ነው ያሉት በአስተያየታቸው፡፡

በቀድሞ ባለስልጣናቱ መለቀቅ የሒዩማን ራይትስ ዎች አስተያየት

የቀድሞ የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንቱ መለቀቅን  የሰባዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋችም ተችቷል፡፡ ሰብዓዊ ተቋሙ በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በቀድሞው የሶማሌ ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ላይ የተመሰረተውን ክስ ውድቅ አድርጓል በማለት፤ ለከባባድ የህግ ጥሰቶች የተጠያቂነት አለመስፈን የሚያሳይ ብሎታል፡፡በኦነግ አመራሮች እስራት የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥሪ

ሰብዓዊ ተቋሙ የቀድሞው ክልላዊ ፕሬዝዳንቱ የክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው አስርት ዓመታት በጄይል ኦጋዴን ፈጸሙ ከተባለው የማሰቃየት ተግባር ጀምሮ በቀድሞ ልዩ ፖሊስ መዋቅር ፈጽመዋል በተባለው ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ልክ መጠየቅ የነበረባቸው መሆኑንም በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የቀድሞ ባለስልጣናቱ ከዓመታት በኋላ መለቀቅን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር እስረኞቹ የተለቀቁት ለህዝብ ፍላጎት ሲባል ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡

የሂዩመን ራይትስ ዋች አርማ
የሂዩመን ራይትስ ዋች አርማ

የባለስልጣናቱ መለቀቅ እና የኦነግ ባለስልጣነት እስራት

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የቀድሞ ባለስልጣናቱን ከእስር መፈታት በተቃወመበት በዚሁ መግለጫው አክሎ እንዳብራራም፤ በከባባድ ወንጀሎች ተጠርጥረው ከታሰሩት ከቀድሞ ባለስልጣናቱ ምትክ ክስ እንኳ ያልተመሰረተባቸው እና ፍርድ ቤት በነጻ ያለቀቃቸው አመራሮቼ መፈታት ነበረባቸው ብሏል፡፡ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ አክለውም “እነዚህ ነጻ ናችሁ ተብለው ከመልቀቅ ይልቅ በፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ነጻ ናችሁ ተብለው የተለቀቁት እስካሁን በእስር ላይ የሚገኙ አመራሮቻችን መለቀቅ ነበረባቸው” ነው ያሉትም፡፡
ኦነግ በመግለጫው እንዳብራራው አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ከኔሳ አያና፣ ገዳ ኦልጅራ፣ ገዳ ገቢሳ፣ ለሚ ቤኛ እና ዳዊት አብደታ እንዲሁም ግርማ ጥሩነህ የተባሉ አመራሮቹ እስካሁንም ከሁለት እስከ ስድስት ዓመታት ለሚሆኑ ጊዜያት በእስር ላይ ናቸው፡፡ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ እንደሚሉት በፓርቲው ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴ ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰባት ፖለቲከኞች እስካሁንም በቡራዩ ታስረው ይገኛሉ፡፡ዋስትና የተፈቀደላቸው የኦነግ አባላት እንዳልተፈቱ ጠበቃቸው ተናገሩ
ስለ እነዚህ ፖለቲከኞች እስራት ከዚህ በፊት አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ሰጥተው የነበሩ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ፖለቲከኞቹ በእስር ላይ የሚገኙት በኦሮሚያ በትጥቅ መንግስትን ለመጣል ከሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን ጋር ቁርኝት አላቸው ተብለው በመጠርጠራቸው ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ 
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ 
ታምራት ዲንሳ