1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፈርጉሰን፤ የዳኞች ዉሳኔና የሕዝብ ተቃዉሞ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 16 2007

ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የፍርድ ሸንጎ ያልታጠቀ ጥቁር ታዳጊ ወጣትን በመግደል የተጠረጠረዉን ነጭ ፖሊስ ከመከሰስ ነፃ ማድረጉ በፈርጉሰን ሚዙሪ ግዛት የከፋ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ እንዲያገረሽ ማድረጉ ተነገረ።

https://p.dw.com/p/1DtJN
ምስል Reuters/A. Latif

የአካባቢዉን ፖሊስ በመጥቀስ የጀርመን የዜና ወኪል እንደዘገበዉ አሁን በዚህ ስፍራ የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ ባለፈዉ ነሐሴ ወር ድርጊቱ እንደተፈፀመ ከታየዉ እጅግ የከፋ ነዉ። በመቶዎች የሚገመቱ የአካባቢዉ ኗሪዎች በ28 ዓመቱ ፖሊስ ዳረን ዊልሰን ላይ የዳኞች ዉሳኔ ከመሰማቱ አስቀድመዉ ተሰባስበዉ ነበር። ዘጠኝ ነጮችና ሶስት ጥቁሮችን ያካተተዉ የፍርድ ሸንጎዉ ፖሊሱ የ18 ዓመቱን ማይክል ብራዉንን ለመግደሉ በቂ መረጃ እንደሌለ መግለጹ ከባድ ተቃዉሞን አስከትሏል። የአካባቢዉ ፖሊስ አዛዥ ጆን ቤልማር፤

«ቢያንስ በደርዘን የሚገመቱ ሕንጻዎች በእሳት መጋየታቸዉን አዉቃለሁ አብዛኞቹም ፍፁም ወድመዋል። ፍሎሪሳንት ጎዳና ላይም ሁለት የፖሊስ ተሽከርካሪዎች መጎዳታቸዉንም አዉቃለሁ። ፖሊሶች በድንጋይ፣ በባትሪ እና በመሳሰሉ ነገሮች የተደበደቡበት አጋጣሚ አለ፤ እኔ እራሴ ወደ150 የሚሆን ተኩስ ሰምቻለሁ።»

Ferguson Entscheidung Grand Jury - Protest in New York 24.11.2014
ምስል picture-alliance/dpa/Peter Foley

እንዲያም ሆኖ ፖሊስ የሰዉ ሕይወት ባለማለፉ እፎይታዉን ቢገልጽም ትናንት ማምሻዉን 29ሰዎችን ማሠሩን አስታዉቋል። ባለፈዉ ነሐሴ ወር ለተፈጸመዉ ግድያ ተቃዋሚዎች ፖሊሱ ነፍስ በማጥፋት እንዲከሰስ ይጠይቃሉ፤ ፖሊሱን የሚደግፉ ወገኖች ደግሞ ራስን በመከላከል ሂደት የተፈጸመ ነዉ በማለት ይከራከራሉ። ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ተቃዉሞ የሚያሰሙት ወገኖች ከአመፅ እንዲታቀቡ ፖሊስም አደብ እንዲገዛ አሳስበዋል።

«በመጀመሪያ እና ከሁሉ አስቀድሞ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ሀገር ነዉ ያለን። እናም ይህ የከፍተኛ ዳኞች ጉባኤ ዉሳኔ መሆኑን መቀበል አለብን። በዚህ የሚስማሙ አሜሪካዉያን አሉ፤ እንዲሁም በዚህ ያዘኑ እንደዉም የተቆጡም አሉ። የሚጠበቅ የስሜት ነፀብራቅ ነዉ። ሆኖም ከማይክል ቤተሰቦች ጎን በመሆን ዉሳኔዉን የተቃወሙ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲያደርጉት እጠይቃለሁ።»

በነጮች የተሞላዉ ፍርድ ሸንጎ ያሳለፈዉ ዉሳኔ ፈርጉሰን ብቻ ሳሆን በሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች የሚኖሩ ጥቁሮችንም ቁጣ ቀስቅሷል። የዩናይትድ ስቴትስዋ ፈርጉሰን ከተማ ዛሬ በጥቁር ነዋሪዎችዋ አመፅ እና በነጭ ፀጥታ አስከባሪዎችዋ አፀፋ ስትታበጥ ነዉ የዋለችዉ።የአመፅ፤ ግጭቱ ሰበብ ባለፈዉ ነሐሴ አንድ ጥቁር ወጣትን በመግደል ወንጀል የተጠረጠረዉ የከተማይቱ ነጭ ፖሊስ በተጠረጠረበት የወንጀል ጭብጥ እንዳይከሰስ የከተማይቱ ፍርድ ሸንጎ ትናንት በመወሰኑ ነዉ።በነጮች የተሞላዉ ፍርድ ሸንጎ ያሳለፈዉ ዉሳኔ ፈርጉሰን ብቻ ሳሆን በሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች የሚኖሩ ጥቁሮችንም ቁጣ ቀስቅሷል።የዋሽግተኑ ወኪላችን አበበ ፈለቀን በሥልክ አነጋግሬዋለሁ።

አበበ ፈለቀ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ