1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፀረ ኤቦላ ምክክር በብራስልስ

ማክሰኞ፣ የካቲት 24 2007

የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን በምዕራብ አፍሪቃ የተከሰተውን የኤቦላ ስርጭት ለማብቃት ያደረገውን ጥረት ውጤት ለመመልከት ዛሬ በብራስልስ ጉባዔ አካሄደ።

https://p.dw.com/p/1EkUF
Belgien Ebola Konferenz in Brüssel
ምስል T. Charlier/AFP/Getty Images

በዚሁ የአንድ ቀን ጉባዔ ላይ የተሳተፉት በምዕራብ አፍሪቃ ኤቦላ ያጠቃቸው የላይቤሪያ፣ ሲየራ ልዮን እና የጊኒ መሪዎች ስርጭቱን ለማስቆም ለጀመሩት ትግል ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እንዲተባበራቸው ጥሪ አሰምተዋል። ኤቦላ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ጊኒ ውስጥ ከተከሰተ ወዲህ ከ9,000 የሚበልጥ ሰው ሞቶዋል።

የብራስልሱ ጉባዔ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት በኤቦላ ስርጭት አንፃር ለሚያደርጉት ትግል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመስጠት የአምስት ቢልዮን ዶላር ርዳታ ለመስጠት የገባውን ቃል እንዲጠብቅ እና ስርጭቱን ለማስቆም ጥረቱን እንዲቀጥል ለማስታወስ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል። ከ600 የሚበልጡ ከፍተኛ አፍሪቃውያን እና አውሮጳውያን ባለሥልጣናት፣ ጠበብት እና የርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ጉባዔ የበሽታው ስርጭት በወቅቱ የሚገኝበትን ሁኔታ የመረመረው ህብረቱ በሶስቱ ሀገራት ባለፉት ጊዚያት ቀንሶ የነበረ የኤቦላ ስርጭት አሁን በሲየራ ልዮን እንደገና መጨመሩን አሳሳቢ አድርጎ ተመልክቶታል፣ አሁን ከሲየራ ልዮን እንደተሰማውም የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሳምዌል ሳምሱማና አንዱ ጠባቂያቸው በኤቦላ ከሞተ በኋላ ራሳቸውን ከህብረተሰቡ አግልለዋል። አዲስ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር እንዳይጨምር ስርጭቱን በጠቅላላ የማስቆም ጥረቱ ሊቀጥል እንደሚገባ ህብረቱ ማሳሰቡን ጉባዔውን የተከታተለችው የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ባርባራ ቬዝል አስታውቃለች።

Symbolbild - Ebola Virus
ምስል picture-alliance/dpa

« ስርጭቱ ባለፉት ሁለት ወራት በጉልህ መቀነሱ ታይቷል። ይሁንና፣ በሲየራ ልዮን እና በጊኒ በስርጭቱ አዲስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ባለፉት ጊዚያት እንደገና ቀስ በቀስ በመጨመር ላይ ነው፣ የተላላፊውን በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር የሚሰሩት ጠበብት የዚህኑ አሳሳቢ ሂደት ምክንያት ለማወቅ በመሞከር ላይ ናቸው። አዲሱ ስርጭት በጠቅላላ ለማስቆም ስለሚቻልበት ጉዳይም መክረዋል። »

ስርጭቱን በማስቆም ረገድ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትም ሆነ የአውሮጳ ህብረት ተገቢውን ርምጃ በመውሰዱ ረገድ በመዘግየታቸው ከርዳታ ድርጅቶች እና ጠበብት ጠንካራ ወቀሳ መሰንዘሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ባጠቃላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ካለፈው ስህተት ትምህርት በመቅሰም ይህ ዓይነቱ ስህተት በማይደገምበት ጉዳይ ላይ መክሮዋል።

« ይህ ዓይነቱ ስህተት እንዳይደገም ምን መደረግ አለበት፣ ምን ዓይነት ዘዴዎችን ማዘጋጀት ይቻላል የሚሉት ጉዳዮች ዓቢይ መወያያ ርዕስ ሆነዋል። ለምሳሌ፣ ጀርመን ከሀገር ሀገር በመሄድ ፈጣን ርምጃ ሊወስዱ የሚችሉ ጠበብት የሚጠቃለሉበት ቡድን ልታቋቁም የምትችልበት ወይም ከአውሮጳ ህብረት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ቡድኖች ፈጣን ርዳታ የሚቀርብበት ሀሳብ በሰፊው እየተመከረበት ነው፣ ባጠቃላይ ወደፊት ተመሳሳይ ችግር በሚከሰትበት ጊዜ አስቸኳይ ርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። »

Logo Zentrale IWF in Washington
ምስል DW/A.Becker

ዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት ለሲየራ ልዮን 187 ሚልዮን ዶላር የዕዳ ስረዛ እና ርዳታ ለማድረግ በትናንቱ ዕለት ወስኖዋል። ግብረ ሰናዩ ድርጅት ኦክስፋም በኤቦላ ለተጎዱት ሀገራት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ለጀርመን የተደረገው ዓይነቱ ማርሻል ፕላን እንዲደረግ ጥሪ አስምቷል። በዓለም ባንክ ግምት መሠረት፣ ኤቦላ ባስከተለው መዘዝ ላይቤሪያ፣ ሲየራ ልዮን እና ጊኒ በዚህ ዓመት ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢያቸው መካከል 12% ያጣሉ።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ