1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጥምን በጃዝ በመሃል በርሊን

ሐሙስ፣ ሐምሌ 17 2006

ጦቢያ ግጥምን በጃዝ የተሰኘዉ የኪነ-ጥበብ ቡድን ማሃል አዉሮጳ ላይ ግጥምን በጃዝ አሳይቶ ከጀርመናዉያንን እና ሌሎች ምዕራባዉያን ጋር ልምድ ተለዋዉጦ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶአል።

https://p.dw.com/p/1Cich
TOBIYA Poetic Jazz Berlin
ምስል DW/A. Tadesse Hahn

ወር በገባ በመጀመርያዉ ረቡዕ ምሽት በራስ ሆቴል፤ ወጣት ገጣምያን፤ የወግ ፀሃፊዎች፤ ሙዚቀኞች እና ዲስኩር አቅራቢዎች፤ የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ሙዚቃ አጅበው ያቀርባሉ ። የዚሁ መድረክ መስራቾች በርሊን ከሚገኘዉ የሥነ-ጥበብ ተቋም ጋር በመተባበር ግጥሞቻቸውን በጃዝ በማቀናበር ለበርሊን ታዳሚ አቅርበዋል። በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር በክብር እንግድነት የተገኙበት ይህ መድረክ፤ በርካታ አዉሮጳዉያን ታዳሚዎችን በማቀፉ ግጥሙ ተተርጉሞ ለአዉሮጳዉያኑ በሚገባ መልክ ቀርቦላቸዋል ።
ጀርመን በርሊን ከተማ ከተገኙት ሶስት ወጣቶች መካከል የሰዓሊና ገጣሚ ምህረት ከበደ፤ የሥነ ጥበብ ክህሎትዋ ለየት ያለ እንደሆን ይነገርላታል። ወደ አዉሮጳዉያኑ ሃገራት የኪነ-ጥበብ ስራችንን ይዘን ሥንሄድ እንዲገባ ብንተረጉመዉና ብናቀርበዉ ለሃገራችን አንባሳደር እንሆናለን ሥትል ተናግራለች። ይህ የኛ የበርሊን ጉዞ ግጥሞቻችንን በትርጉም መልክ በማቅረባችን ባህላችንን በማስተዋወቃችን ክህሎታችንን በማሳየታችን ተሰስቻለሁ ፤ ለቀቅ ብንል ደስ ይለኛል ስትል ገልፃለች። በርካታ ኢትዮጵያዉያን እንዲሁም ጀርመናዉያን እና ሌሎች ከምዕራቡ ዓለም የመጡ ታዳሚዎች የተገኙበት ይህ መድረክ እጅግ የደመቀ እንደነበር ተነግሮለታል። ወጣት ምህረት ከበደ ግጥምን በጃዝ መድረክ የተሰኘዉን መረሃ- ግብር ከመሰረቱት ወጣቶች መካከል አንዷ ነች፤ ሰዓሊ ምህረት ሥነ-ጥበብን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ሁለት ግዜ ወደ በርሊን ከተማ መጥታ ነበርም አጫዉታናለች።
በተለያዩ ሥነ-ጽሁፎቹና በተለይ በሥነ-ግጥም ችሎታዉ የሚታወቀዉ ጋዜጠኛ እና ፀሃፊ አበባዉ መላኩ ጦብያ ግጥምን በጃዝ በርሊን ከተማ በተዘጋጀዉ መድረክ ላይ ያቀረበዉ ግጥም ነበር ያደመጥነዉ። አበባዉ መላኩ በርሊን ከአቀባበሉ ጀምሮ ስኬታማ እንደነበር ሳይገልፅ አላለፈም። የኢትዮጵያ ባህላዊ ግጥምን ይዘን ለመጀመርያ ግዜ ወደ ዉጭዉ ዓለም የተጓዝ እኛ መሆናችንኝ አምናለሁ፤ በዚህም ኩራት ይሰማኛል ሲል ገልፆአል። ለ13 ቀናት በርሊን ላይ ቆይታን ያደረጉት ሶስቱ ወጣት ጻህፍት፤ ባለፈዉ ማክስኞ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት በርሊን እንደገቡ ጀርመን የዓለም የእግር ኳስ ግጥምያን ለማሸነፍ በመቃረብ ላይ ሳለች ነበር። እንደ ገጣሚ አበባዉ መላኩ እግራችንም ርጥብ በመሆኑ ከጀርመናዉያኑ ኳስ አፍቃሪዎች ጋር አብረን ታመን በማሸነፋቸዉ ደስተኞች ነን አንድ ታሪክንም ለማየት በቅተናል ሲል ተናግሮአል። በቴሌቪዥን ሲከታተለዉ የነበረዉንም የአዉሮጳዉያን የኳስ ፍቅር ጀርመን ዋንጫዉን ስትወስድ፤ ከቢራ ጋር ከጀርመናዉያን እና ኢትዮጵያዉያን ጋር ከደስታ ጋር በጋራ ሲከበር ማንጋቱንና ይህንኑ ቀን እንቅልፉን ለጀርመናዉያኑ የኳስ አፍቃሪዎች እንደሰዋ በፈገግታ ገልጾልናል።
ኢትዮጵያዉያኑን ገጣምያን ወደ ጀርመን የጋበዘዉ፤ በበርሊኑ ዩንቨርስቲ ስር የሚገኘዉ Institut für Raumexperimente በመባል የሚታወቀዉ በሥነ-ጥበብ እና ኪነ-ጥበብ ላይ የተለያዩ ልዉዉጦች እና ጥናቶችን በሚያደርገዉ ተቋም ፤ በኢትዮጵያ ከሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ጋር እንደሚሰራ የገለፁልን የሥነ -ግጥሙ ምሽት አስተናባሪ ጀርመናዊትዋ ክርስቲና ቨርነር፤ የሥነ-ግጥም መድረኩ፤ የተሳካ ዝግጅት ሥለ ነበር በቀጣይ ይህን አይነት ሰፊ ዝግጅት ለማቅረብ እንደታሰበ ገልፀዋል። ዝግጅቱም እጅግ አመርቂ ስለነበር ደስተኛ ናቸዉ

«ከሙዚቀኞችና ከገጣምያን ጋር ያዘጋጀነዉ ይህ ፕሮግራም፤ ወደፊት በሰፊዉ ለማዘጋጀት ያቀድነዉ የአንድ ግዙፍ መረሃ-ግብር አንድ ትንሹ አካል ነዉ። ይህ ተሞክሮ ፤በፊልም መልክ ተቀርፆ በማስተማርያነት እንዲዉል ለኢትዮጵያ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ለሚሰራዉ የማሰልጠኛ ማዕከል ይሰጣል። ስለዚሁ ዝግጅት አንድ ዘጋቢ ፊልም ተሰርቶ በተቋማችን ድረ- ገፅም ላይ እናስቀምጣለን»
ጦብያ ግጥምን በጃዝ ባህል በማስተዋወቁ በማስተማሩ እንዲሁም በማዝናቱ ረገድ እያደረገዉ ያለዉ ሥራ ይበል የሚያሰኝ ይመስለናል። ከተቋቋመ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረዉና ኢትዮጵያዊ ባህልን ገላጭ ግጥምን በጃዝ ይዞ ለመጀመርያ ግዜ ወደ መሃል አዉሮጳ የመጣዉ ቡድን በጀመረዉ ባህልን የማስተዋወቅ ሥራ እንዲቀጥል ስንል መልካም ምኞታችንን እንገልፃለን፤ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ፤ ምህረት ከበደ፤ አበባዉ መላኩ እና ሙዚቀኛ ጆርጋ መስፍን ላደረጉልን ትብብር ምስጋናችን እናቀርባለን። ሙሉ ቅንብሩ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ

አዜብ ታደሰ
ሂሩት መለሰ

TOBIYA Poetic Jazz Berlin
ምስል DW/A. Tadesse Hahn
TOBIYA Poetic Jazz Berlin
ምስል DW/A. Tadesse Hahn
TOBIYA Poetic Jazz Berlin
ምስል DW/A. Tadesse Hahn