1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግድግዳ ጡፍ ወይም ግራፊቲ በሐዋሳ ከተማ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3 2007

በምዕራቡ ሀገራት የግድግዳ ጡፍ ወይም ግራፊቲ እንደ ተመልካቹ እና ማህበረሰቡ አተረጓጎም ይለያያል። አንዳንዶች ግራፊቲን ከውንብድና ጋር ሲያገናኙ ሌሎች ስሜት የሚገለፅበት አንድ መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ። ሐዋሳ ከተማ የሚገኙ የተወሰኑ ወጣቶች የግድግዳ ጡፍን እንደ አንድ የስዕል ጥበብ ነድፈው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/1E3Bp
Behulum Graffiti
ምስል Behulum Graffiti

የጣሊያንኛው ቃል «ግራፊቶ» ለብዙዎች ግራፊቲ ፤ በድንጋይ ላይ ተጫጭሮ የሚቀረፅ ጹሁፍ ወይም ምስል እንደማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ምዕራባዊያን ግራፊቲ ብለው የሚጠሩት አፃጻፉ ወይም አሳሳል ብዙም የተለመደ ባይሆንም፤ የግድግዳ ጡፍ በተለይ በትምህርት ቤት ክፍሎች እና መፀዳጃ ቤቶች ይስተዋላል። የግድግዳ ጡፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ፣ ግድግዳ ላይ በተለያዩ ደማማቅ ቀለማት ይፃፉ ወይም ይሳሉ ከጀመረ በርከት ያሉ አመታት ተቆጠሩ። በሐዋሳ ከተማ« ግራፊቲ ኢትዮጵያ የወጣቶች ማህበር» ብለው አንድ ማህበር በመመስረት ላይ ያሉ ወጣቶች እንደዚህ አይነቱ አሳሳል ዛሬ በከተማዋ የሚታወቁበት ሆኗል። የ 22 ዓመቱ ወጣት በሁሉም መንግስቱ ከነዚህ አንዱ ነው። በሐዋሳ ከተማ የ12 ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው በሁሉም፤ ለስዕል የተለየ ፍቅር እንዳለው ይናገራል።

የግድግዳ ጡፍ በብዛት በሚስተዋልበት ጀርመን በጎዳናዎች ላይ የሚታዩት ስዕሎች ሀሳብን ከመግለፅ ይልቅ በማህበረሰቡ ዘንድ ወንበዴ እና ወሮ በላ ተብለው የተፈረጁ፣ በተለይም ደሀ በሚበዛባቸው የከተማ ክፍሎች የሚኖሩ ወጣቶች ያለ ፍቃድ የሰውን ንብረት ከሚያበላሹበት ድርጊት ጋር ይዛመዳል። ምንም እንኳን በሁሉም እና ባልደረቦቹ ፤ የግራፊቲ ስልቱን ከምዕራቡ ሀገራት ቢወስዱም፤ ስራቸውን ለመስራት ባለቤቱን ፍቃድ ጠይቀው ነው።

Behulum Graffiti
በሁሉም መንግስቱምስል Behulum Graffiti

ሳያስፈቅዱ ጎዳናዎች ላይ መሳል፤ ጀርመን ውስጥ በህግ ያስቀጣል። ህጉም ባስቀመጣቸው ሁለት አንቀፆች መሰረት፣ በህገ ወጥ መንገድ መቃብሮች፣ ሀውልቶች እና ጎዳናዎች ላይ ያሉ ጥበቦችን ያበላሸ ሰው የገንዘብ ቅጣት ወይም እስከ ሶስት ዓመት እስራት ይጠብቀዋል። አብዛኞቹም የግድግዳ ጸሀፊዎች እንይያዙ ስለሚፈሩ የሚፅፉት ወይም የሚስሉት ሌሊት ነው ።ሳያስፈቅዱ ጎዳናዎች ላይ ከመሳል ጋር በተያያዘ ጀርመን ውስጥ የደረሱ ጥፋቶችን ብንመለከት፤ ከ10 ዓመት በፊት ያለ ፍቃድ የግለሰብ ቤቶችና ህንፃዎች ላይ የግድግዳ ጡፎችን ለማስለቀቅ የወጣው ገንዘብ 500 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚደርስ የጀርመን የቤቶች እና የመሬት ንብረት ባለቤቶች አስታውቋል። የጀርመን የባቡር ድርጅት ከ 2 ዓመት በፊት በባቡሮቹ ላይ በደረሰ ጥፋት ለ33 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ሲዳረግ፤ ከደረሱት 30 ሺ ጥፋቶች 14 000 የግድግዳ ጡፍ እንደነበር አስታውቋል።

በሐዋሳ ከተማ የግድግዳን ጡፍ ወይም ግራፊቲን እንደ አንድ የአሳሳል ስልት ከሚያየው ሌላው ወጣት አንዱ የበሁሉም ጓደኛ በረከት ተሾመ ነው። በረከት በቴክኒክ ሙያ ተመርቆ ኮምፒውተር እና ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ይጠግናል። እሱም የግድግዳ ጡፍን የሚገልፀው እንደ በሁሉም ሀሳብን ለመግለፅ ነው።

Behulum Graffiti
ምስል Behulum Graffiti

በሁሉም እንደገለጸልን የ« ግራፊቲ ኢትዮጵያ የወጣቶች ማህበር» አባላት ራሳቸውን ለሌሎች የሚያስተዋውቁበት የመረጃ ገፅ በአሁኑ ሰዓት በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ። ወጣቶቹ ሙያቸውን ለማዳበር ፌስ ቡክ እና ዩ ቱይፕ ከመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛ ድረ ገፆች መረጃ ያፈላልጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ወደእነሱም ብቅ ይሉ እና ሀሳብ ይለዋወጣሉ።

በምዕራቡ ሀገራት በብዛት በአውራ ጎዳና ግድግዳዎች እና ግንቦች ላይ የሚስተዋሉ የግድግዳ ጡፎችን በሐዋሳ ከተማ ከሚስሉ ወይም ከሚፁፍ ወጣቶች ጋር ያደረግነውን ቆይታ በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ