1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጉዞ ዓድዋ

ሐሙስ፣ የካቲት 26 2007

«…የሃገሬ ሰዉ ፤ ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፤ አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበት እርዳኝ፤ ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሓይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ።

https://p.dw.com/p/1ElFW
Äthiopien Gedenken an Schlacht von Adua
ምስል DW/A. Tadesse-Hahn

ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጠየቃለህ አልተዉህም። ማራያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፤ዘመቻዬም በጥቅምት ነዉና ነዉና፤ የሸዋ ሰዉ እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረይሉ ከተክ ላግኝህ»

Äthiopien Gedenken an Schlacht von Adua
ምስል DW/A. Tadesse-Hahn

ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ,ም የጣልያን ወራሪን ለመመከት ካስነገሩት የክተት አዋጅ የተወሰደ ቃል ነዉ። «ዓድዋ - ይከበር ይዘከር ለዘልዓለም» በሚል መሪ ቃል የዓድዋን ድል ለማሰብ በየዓመቱ ከአዲስ አበባ ወደ ዓድዋ በእግር በመጓዝ ለዚህ ቀን ያበቁንን የጥንታዊ ጀግኖች ታሪክ እንወቅ የሚለዉ የተጓዞች ቡድን ከአዲስ አበባ ተነስቶ 1010 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘዉ ዓድዋ ከተማ ገብቶአል። ይህ ዘንድሮ ለሁለተኛ ግዜ የተካሄደዉ ወደ ዓድዋ ጎዞ የተሰኘዉ የተጓዦች ቡድን አንድ ሴትን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ያካተተ ነበር። በሰላሳ ስምንት ቀኑ ዓድዋ ከተማ የደረሰዉ ይህ ቡድን 119ኛዉን የዓድዋን ድል ክብረ በዓል ዓድዋ ከተማ ላይ በደማቅ አክብረዋል።

አንዲት ሴትና አምስት ወንዶችን ያካተተዉ ዘንድሮ ለሁለተኛ ግዜ የተካሄደዉ ዝክረ ዓድዋ ጉዞ ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ተጓዦችን ለማሳተፍ እቅድ ቢይዝም፤ ጉዞዉን ለመሳተፍ ከተመዘገቡት ከመቶ በላይ እጩዎች ለጉዞዉ መስፈርቶችን አሟልተዉ የተገኙት ስድስት ተሳታፊዎች ነበሩ።ከጉዞዉ አስተባባሪዎችና መካከል አቶ መሃመድ ካሳ አሊ የተሳካ ጉዞ እንደነበር ገልፀዋል።

« ዝግጅቱ በጣም ጥሩ ነበር። ይህ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገዉ «ጉዞ ዓድዋ» ዓላማ ዓድዋ ይዘከር ይከበር ለዘላለም የሚል ነዉ። የተጓዦቹ ቡድን በጉዞአቸዉ መጠናቀቅያ ሶሎዳ ተራራ ላይ ደርሰዉና አዳራቸዉን እዚሁ ተራራ ላይ አድርገዉ ማለዳ ጠዋት ሰንደቅ ዓላማን ሰቅለዋል። ከዝያም ነዉ የከተማዉ ነዋሪ ሞቅ ያለ አቀባበልና ደማቅ በዓል የተከበረዉ። በክብረ በዓሉ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ የዓድዋ ከተማ ከንቲባ ፤ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች፤እናት አባት አርበኞች በርካታ ሕጻናት ተገኝተዋል። ይህን ጉዞ ስናዘጋጅ የዓድዋን ታሪክ ከትዉልድ ትዉልድ ለማስተላለፍ ታሪኩን ለዓለም ለመንገር ለማስተማር ነዉ»

Feier 118. Schlacht von Adua
ምስል Getachew T. Haile-Giorgis

የ 28 ዓመትዋ ወጣት ጽዮን ወልዱ የመጀመርያዋ የ «ጉዞ ዓድዋ» ተሳታፊ ናት። የዓድዋ ክብረ በዓል ለኔ እስከዛሬ ይህን ያህል ትርጉም አልነበረዉም ያለችን ወጣት ጺዮን፤

« ጉዞዉ እጅግ ደስ የሚል ነበር ። መነሻችንን ያደረግነዉ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ ጣይቱ ሆቴል ሚኒሊክ አደባባይ አካባቢ ነዉ ። በአጠቃላይ የፈጀብን ሰላሳ ስምንት ቀናቶች ነዉ። ዓድዋን ስናስብ የዓድዋ ጦርነት ብቻ አልነበርነዉ ። ከዝያ በፊት ሁለት ጦርነቶች ተካሂደዋል፤ አንባላጌ ላይ እና መቀሌ ላይ፤ ከዝያ በኋላ የመጨረሻዉ ጦርነት ዓድዋ ላይ የነበረዉ። በጉዞአችን ታሪኩን ለማወቅ መጽሐፍ የማንበብ ፕሮግራምም ስለነበረ እያንዳንዱን ቦታ በደንብ እያየየን እየገለፁልን ነዉ የተጓዝነዉ። ጉዞዉ የዝያን ግዜዎቹን ማንንነት የምትረጂበትም ነዉ። በተለይ ስለ አፄ ምንሊክ ሲታሰብ በጣም ጥልቅ አስተሳሰብ የነበራቸዉ ንጉስ እንደነበሩ በተለይ ለጣይቱ የነበራቸዉ ጦታ በጣም ያስደስታል። እናም ያድዋ ጦርነት ጦርነት ብቻ ሳይሆን ከጦርነቱ ጀርባ የነገስታቱን ጥልቅ አስተሳሰብ በጉዞአችን በደንብ አይተናል።»

ዓድዋ ከደረሳችሁ በኋላ የከተማዉ ነዋሬ አቀባበል እንዴት ነበር?ለሚለዉ ወጣት ጽዮን «የአካባቢዉ ነዋሪ አቀባበል እጅግ ደማቅ ነበር አድዋ እንዲህ በደማቅ እንደሚከበር አላዉቅም ነበር። ሁሉም በአንድ መንፈስ ነበር እጅግ ደማቅ በዓል እጅግ ጥሩ አቀባበል ነበር።

የ «ጉዞ ዓድዋ» ዋና አስተባባሪ አቶ ያሬድ ሹመቴ በበኩላቸዉ ተጓዦች ዓድዋ እስኪደርሱ በመኪና መንገድ በመጓዛቸዉ ይህ ነዉ የሚባል አዉሪ እንዳላጋጠማቸዉ ገልፀዋል። ይህ ጎዞ ወጣቱን ታሪኩን በግልፅ እንዲያዉቅ ይረዳል ሲሉ ገልፀዋል።

Äthiopien Gedenken an Schlacht von Adua
ምስል DW/A. Tadesse-Hahn

« አባቶቻችን በአፄ ምንሊክ በመመራት ከኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን የከተቱ ጀግኖች ወደ ዓድዋ ያደረጉትን ጉዞ በማስታወስ የመጨረሻ መስዋዕትነት የከፈሉበትን ቦታ በመርገጥ ለማሰብና ለመዘከር ያደረግነዉ ጉዞ ነዉ። በሌላ በኩል የዓድዋ ድል በየዓመቱ በተለየ መንገድ ታስቦና ተከብሮ እንዲዉል ያደረግነዉ እቅድም ነዉ። ዓድዋ ድል ኢትዮጵያዉያን በብቸኝነት በጋራ ሊያከብሩት የሚችሉት ብቸኛዉ በዓል ነዉ። የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ሲነሳ ትልቁና ሁሉንም ቋንቋ ሁሉንም ሐይማኖት እኩል አስማምቶ በጋራ የሚያሰልፈዉ የኢትዮጵያዊነት መሰረት የሆነዉ ትልቁ ጥንስስ የዓድዋ ድል ነዉ ። የዓድዋ ድል መገኘት የኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን ለመላዉ አፍሪቃ ለመላዉ ጥቁር ህዝቦችም በዓልም ጭምር ነዉ። ምክንያቱም ከዓድዋ ድል በኋላ የየጥቁር ህዝብ ከዳር እስከዳር ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመዉጣት የተነሳሳበት እና ይቻላል የሚለዉን መንፈስ ሁሉም አፍሪቃዊ ያገኘበት ድል ነዉ።»

«ዓድዋ - ይከበር ይዘከር ለዘልዓለም» በሚል መሪ ቃል 119 ኛዉን የዓድዋን ክብረ በዓል አድዋ ድረስ በእግሩ በመጓዝ ያከበረዉ ቡድን አስተናናሪ አቶ መሃመድ እንደገለፁት የአድዋን ታሪክ በዝርዝር ለማሳወቅ ይህ ጉዞ መጀመሩ አስፈላጊ ነዉ።

« የዓድዋ ድል የአንድ ቀን ትግል ብቻ አይደለም። ለምሳሌ የመጀመርያዉ ጦርነት የተካሄደዉ አንባላጌ በሚባል ቦታ ላይ ነዉ የተካሄደዉ። ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ መቀሌ እንዳእየሱስ በሚባል ቦታ ላይ ተካሂዶአል፤ ከዝያ በኋላ ነዉ ዓድዋ ላይ ጦርነቱ ተካሂዶ የመጨረሻዉ ድል የተገኘዉ። ይህ ሁሉ የሆነዉ ከህዳር 28 እስከ የካቲት አድዋ ድል ሶስት ግዜ በነዚህ ቦታዎች ከጣልያን ጋር ከፍተኛ ዉግያ ተካሂዶአል። ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያዉያን ጥሩ ጨዋነት ያሳዩበት እንደሆነም ይታወቃል። በሶስቱም ጦርነቶች በጦርነቱ የወደቁት በፍትሐት ተቀብረዋል፤ ለዚህ ማስረጃዉ መቃብሮቹ እስካሁን መኖራቸዉ ነዉ። እስካ በዛሪ በየትኛዉም ጦርነት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፤ ጣልያኖቹ ከተሸነፉ በኋላ መሳርያቸዉን ጭምር ይዘዉ ከነተማረኩት ሰራዊቶቻቸዉ እንዲመለሱ ተደርጎአል።»

Äthiopien Gedenken an Schlacht von Adua
ምስል DW/A. Tadesse-Hahn

የጣልያን ወራሪን በማባረር የሴቶች ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ ነበር ያሉት አቶ መሃመድ ካሳ እንደሚሉት፤ « በዓድዋዉ ድል የሴቶች ዉለታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የዓድዋ ድል እስኪገኝ በፈጀዉ የአምስት እና የስድስት ወራት ጦርነት፤ ሴቶች ጦሩን ሲቀልቡ ሲያበረታቱ አጋሰሱን ዉሃና ምግብ ሲቀልቡ፤ በጦርነቱ የቁሰለዉን ህክም መመስጠትም ጭምር ለድሉ ከፍተኛ ጽናት፤ ትልቅ አስተፅዖ አድርገዋል። ሌላዉ የአካባቢዉ ዉለታም የሚረሳ አይደለም። ዛፉ ተራራዉ ምንጩ፤ ሸንተረሩ ለዚህ ድል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የጋማ ከብቱ በጭነት፤ በግ ፍየሉ በእርድነት በመቅረብ ሌሎቹ ለዚህ ድል ስኬታማነት አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸዉ። የኢትዮጵያ መልካምድር አቀማመጥን ጨምሮ በአንድ ላይ ኢትዮጵያዊነት ስሜትን በማነቃቃት ጦርነቱን በድል እንድናጠናቅቅ ፤ ፀረ የቅኝ አገዛዝ አስተዋፅኦ በማድረግ ለዚህ ጦርነት ትልቅ ማኅበራዊ እዉደትን ፈጥረዋል። ፊደራሊዝም የሚለዉን ስሜት፤ የሚያስተሳስር የፍቅር ስሜት የፈጠረ፤ የጀግንነት፤ የጦርነት ዉጤት ነዉ ዓድዋ። ይህን ሁሉ በጋራ ለማስተንንተን በማሰብ ነዉ ጉዞ ዓድዋን አጠናክረን ለሁለተኛ ዓመት የቀጠልነዉ። ወደፊትም ዓድዋን ለማክበርና ጉዞ ዓድዋን በሰፊዉ ለማካሄድ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ነዉ»

የዓድዋን ድል በተለይ «ጉዞ ዓድዋ»ን በመሳተፍ ዓድዋን ደማቅ በዓላችን ማድረግ አለብን ያሉት የ«ጉዞ ዓድዋ» ዋና አስተናባሪ አቶ ያሬድ ሹመቴእንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የዓድዋን ድል ለማክበር በዓመት አንዴ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ይህን ታሪካዊ ጉዞ ቢካፈል ሲሉ ጋብዘዋል። ሙሉ ቃለ-መጠይቁን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ