1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ኤቦላን አስመልክቶ ያደረገችው ጥሪ

ማክሰኞ፣ መስከረም 13 2007

የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ኦዙላ ፎንዴር ላይን፤ የኤቦላ ተዋኅሲ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገዉ ጥረት ለመካፈል በፈቃደኝነት ወደ ምዕራብ አፍሪቃ ለሚሄዱ ወታደሮችን እና ሲቪል ሰራተኞች ትናንት ጥሪ አደረጉ።

https://p.dw.com/p/1DH94
Pressekonferenz von der Leyen Steinmeier zu Waffenlieferungen an irakische Kurden
ምስል Odd Anderson/AFP/Getty Images

ጀርመን የኤቦላን ተህዋሲ ለማስቆም እስካሁን 17 ሚሊዮን ዮሮ ረድታለች። ነገር ግን እንደ ሰደድ እሳት የሚዛመተውን ተህዋሲ ለመዋጋት ገንዘብ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ታድያ የጀርመንመከላከያሚኒስትርኦዙላፎንዴርላይን ሰኞ ጠዋት የኤቦላ በሽታ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች መዝመት የሚሹ የጀርመን ጦር ባልደረባዎች በፍቃደኝነትመመዝገብእንደሚችሉ ሲያስታውቁ፤ ወታደር በፍቃደኝነት የሚዘምትበት ተግባር ግራ ያጋባቸው አልጠፉም። ለዛውም ሚኒስትሯ ወታደራቸውን ለማግባባት አንዳንድ ያመቻቹትን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝረው ነው።

« በመጀመሪያ በስፍራው ምን እንደሚጠብቃቸው እና ምን አይነት የጤና ዋስትና እንደሚያገኙ መረጃ ያስፈልጋቸዋል፣ 2ኛ አጭር ስልጠና ያገኛሉ። በስፍራው የሚገኙ በርካታ ሀኪሞች እና የህክምና ባለሙያዎች የሚያውቁትን ስልጠና ይሰጣቸዋል።3ኛ ደግሞ በስፍራው አንድ ነገር ቢያጋጥማቸው ወደ ጀርመን ተመልሰው ክትትል እንደሚደረግላቸው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።»

እንዲያም ሆኖ ከጀርመን ወታደሮች በፍቃደኝነት መዝመት የሚፈልግ ከጠፋስ? በሙያቸው ሀኪም የሆኑት የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር፤ አደጋም ሆነ በበሽታው መያዝ ቢገጥማቸው ወዲያው ወደ ጀርመን የሚላኩ እና የሚታከሙ ከሆነ በፍቃደኝነት መሄድ የሚለውን ጥያቄ በአዎንታ ይመልሳሉ።ለጀርመን ጦር ወታደሮችም ይሁኑ ሲቪል ማህበረሰቡ የክፉ ቀን ቢመጣ እና በትዋህሲው ቢያዙ እንዴት ይሆን ይህን ሚኒስትሯ ዕውን ሊያደርጉ ያሰቡት።« በአሁኑ ሰዓት ለዚህ ለየት ያለ ተልዕኮ በዓለም ያልታየና እስከዛሬ ያልነበረንን ልዩ አዉሮፕላኖችና ሄሌኮፕተሮችን እያዘጋጀን ነዉ።ለዚህ ዝግጅት ደግሞ አራት ሳምንታት ያስፈልገናል።»

Soldatin der Bundeswehr
ምስል picture-alliance/dpa

ከዚህም ሌላ በዚህ አራት ሳምንታት ውስጥ ጊዜያዊ ሀኪም ቤት በአካባቢው እንደሚሰራ እና በቂ የህክምና ባለሙያዎች ለማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሯ አስረድተዋል። ለታቀደው ድጋፍ ጀርመን ምን ያህል ሰዎች ያስፈልጓት ይሆን? ሚኒስትር ፎን ዴር ላይን፤« ይህን ጥሪ ለጀርመን ጦር ካደረኩ በኋላ በሚቀጥሉት ቀናት የምናየው ይሆናል። ለግንዛቤ ያህል ለ50 የሀኪም ቤት አልጋዎች ወደ 100 የሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። በሽታው ወደ ሌላ እንዳይተላለፍ በሚደረገው ልብስ ውስጥ አንድ ሰው ከ አራት እስከ ለአምስት ሰዓት ያህል ነው ልቆይ የሚችለው። ከዛ ዕረፍት መውሰድ ይኖርበታል።በሌላ በኩል አንድ ክፍል ውስጥ የሚገቡ እና ተባብረው የሚሰሩ ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ። በዚህ አጭር መግለጫ ነገሩ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።»

Merkel - von der Leyen - Steinmeier
ምስል Reuters

በርግጥ ጉዳዩ ውስብስብ ሆኖ ይሆናል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስካሁን ጠንካራ ርምጃ ያልወሰደው፤ መፍትሄ ያሹት የላይቤሪያን ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሌፍ ለጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የርዳታ ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ እስከመላክ ያደረሰው። የጀርመን ፌደራሊያዊ መንግሥት ባለስልጣን ሲወያዩ ቢቆዩም፤ ከፍቃደኛ ዘማቾች ጥያቄ ውጪ ሌላ መፍትሄ ያላቸውን ነገሮችን ይዞ አሁን መጥቷል። ከዮናይትድ ስቴትስ እና ፈረንሳይ ጋር በመተባበር ሴኔጋል ላይ በሚመሰርተው ጊዜያዊ ጣቢያ አማካይነት ርዳታው ይላካል።«ምግብ ፣ መድሀኒት እና ሌሎች የርዳታ ቁሳቁሶችን በሳምንት ውስጥ እስከ 100 ቶን ያህል ማመላለስ እንችላለን። ከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከአጋሮቻችን ጋር ዝግጁ ነን።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ