1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀሐይ ኃይል ዓለም አቀፍ ተፍላጊነትና ተቀባይነት

ረቡዕ፣ ጥር 6 2007

አመቺ፤ በውጪም፤ ቀለል በሚለው የፀሐይ ኃይል ላይ ያተኮሩ አገሮች ቁጥር በሚያስደንቅ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል። እ ጎ አ በ 2014 ዓ ም ብቻ፤ በ 20 ከመቶ ነው ያሻቀበው። ይኸው ታዳሽ የኃይል ምንጭ፣ የወደፊቱ ዋንኛ የሥነ ቴክኒክ ፀጋ ያህል

https://p.dw.com/p/1EKa6
ምስል picture-alliance/dpa

እንደሚቆጠርም ነው የኅይል ምንጭ ጉዳይ ተመራማሪዎች የሚናገሩት። በዚህ ሥነ ቴክኒክ ግሥጋሤም ሆነ የቀዳሚነት ድርሻ ካላቸው አገሮች መካከል ፣ ጀርመን፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዝጋሚ መስላለች። በዓለም ዙሪያ የፀሐይን ኃይል የሚያጠምዱ አውታሮች በሰፊው በየቦታው በመተከል ላይ ናቸው። በዋጋ ደረጃም ቢሆን፣ በዲዘል ፤ በጋዝ፤ ድንጋይ ከሰልና አቶም ፤ ኃይል ከሚያመነጩ አውታሮች ዝቅ ያለ ነው። በዓለም ዙሪያ እ ጎ አ በ 2014፤ ጊዜያዊ ግምገማዎች እንደሚያሳዩት 45 «ጊጋዋት » የሚያመነጩ የጸሐይ ኃይል አመንጪ አውታሮች ናቸው የተተከሉት። ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ፤ መጪው ዘመን ፣ የተጠቀሰው የኅይል ምንጭ በዓለም ዙሪያ ይበልጥ የሚስፋፋበት ጊዜ ነው። ዘንድሮ ከ 50 ጊጋዋት በላይ ፤ ከ 5 ዓመት በኋላ ደግሞ በ 100 እና 150 ጊጋዋት መካከል የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል የፀሐይን ኃይል ከሚያጠምዱ አውታሮች እንደሚቀርብ ነው የተነገረው። ይህን የሚሉት በአውሮፓ በጸሐይ ኃይል ምንጭ ምርምር ረገድ የመሪነቱን ሥፍራ ይዘዋል የተባሉት፤ በፍራውንሆፈር ተቋም፣ የኃይል ምንጭ ጉዳይ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ዶ/ር አይከ ቬበር ናቸው።

«ዓለም አቀፉ ፤ የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ልዩ ሰሌዳ (ፎቶቢልቴክ) ገበያ የደራ ነው። ዋጋው ዝቅ ብሎ በሰፊው እስከመሸጥ የደረሰበት ምክንያት በዚህ ለሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚከፈለው ዋጋ ዝቅ ያለ ማለትም ለኪሎዋት- ሰዓት፣ ከ 10 ዩውሮ ሴንት በታች ስለሚከፈል ነው። የ አውታሩ ትልቅነት እየታዬ ፣ ከ 8 እስከ 12 ሳንቲምም ሊከፈልበት ይችላል። ነገር ግን የፀሐይ ብንርሃንና ሙቀት በገፍ በሚያገኙ አገሮች ፤ ከ 5 እስከ 7 እና 8 ሳንቲም ቢሆን ነው ክፍያው ክፍያው። የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ከሆነው ልዩ ሰሌዳ (ፎቶቮልቴክ) ማለትም በቀጥታ የጸሐይን ሙቀትና ብርሃንን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ለውጦ አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት አሠራር በዓለም ዙሪያ በብዙ ቦታዎች በማቋቋም ረገድ የፉክክሩ ደረጃ እስከዚህም መበላለጥ የሚታይበት አይደለም። »

Solarflugzeug Solar Impulse USA Flugzeug FREI FÜR SOCIAL MEDIA
ምስል Reuters

በአውሮፓና በእስያ የተጀመረው ይኸው ከዘመኑ ታዳሽ የኃይል ምንጮች አንዱ በላቲን አሜሪካና በአፍሪቃም ሳይውል ሳያድር ነው የመስፋፋት ዕድል ያገኘው። የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት በገፍ ከሚያገኙት የዓለም ክፍሎች አንዱ አፍሪቃው መሆኑ የታወቀ ነው። ያም ሆኖ በተለይ ከሰሐራ ምድረ በዳ በስተደቡብ በሚገኙት ሃገራት፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ የሚያገኘው የኤልክትሪክ አገልግሎት 25 ከመቶ በታች መሆኑን ነው የዓለም ባንክ የገለጠው ፤ ከከተሞች ራቅ በሚሉ የገጠር ቦታዎች እንዲያውም 10 ከመቶ ገደማ ቢሆን የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ። በዓመት በአማካኝ 56 ቀናት የኤልክትሪክ አገልግሎት የሚቋረጥ በመሆኑም፤ ለዚህ የክፍለ ዓለሙ ከፊል አህጉራት የኤኮኖሚ ዕድገት ደንቃራ በመሆኑ፣ የኃይል ምንጭ አቅርቦቱን ችግር ለማስወገድ በየዓመቱ በግምት 4o ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ሥራ ላይ ማዋል ሳያስፈልግ አልቀረም። ለምሳሌ ያህል ፣ ከብዙዎቹ ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙት ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ፣ እስካሁን በሀገሪቱ በመላ የሚቀርበው የኤልክትሪክ አገልግሎት 55 ከመቶ ሲሆን አሁን በገባው 2015 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት Green Technology Africa ከተሰኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኩባንያ ጋር በመተባበር፣ በአንድ ዓመት ውስጥ 300 ሜጋዋት ኤልክትሪክ በማመንጨት ፤ መጠኑን ወደ 75 ከመቶ ከፍ ለማድረግ እቅድ እንዳላት ነው የምትገልጸው። ከውሃ ኃይል ሌላ፣ በፀሐይ፤ በከርሠ - ምድር እንፋሎትና በነፋስ ኃይልም የመጠቀም አማራጭ ዕድል እንዳላት የታወቀ ነው።

ኤርትራ ፤ 12 ሜጋዋት ኤልክትሪክ የሚያመነጩ አውታሮችን በመትከል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይ ፈንጠር ብለው የሚገኙ መንደሮች፤ 65 ከመቶ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማብቃቷ ይነገራል። ከፀሀይ ኃይል ላቅ ያለ የኤልክትሪክ ኃይል ምንጭ ማግኘት የሚቻልባቸው ቦታዎችም ተጠንተው በካርታ መነሣታቸው ተወስቷል። ወጪ ለመቀነስ ፣ በከፊል ብርሃን ና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎች እንዲሁም ባትሪዎች የሚሠሩት በሀገር ውስጥ ነው።

ደቡብ አፍሪቃ የታዳሽ ኃይል ምንጭ አቅርቦትን እ ጎ አ በ 2012 ከነበረው 1 ከመቶ እስከ 2020 በ 12 ከመቶ ከፍ በማድረግ 3,725 ጊጋዋት ለማመንጨት ነው እቅዷ!። ከሰሐራ በስተደቡብ ከሚገኙ አገሮች፤ የመጀመሪያውን በቀጥታ በልዩ መስታውት አማካኝነት የፀሐይን ብርሃንና ሙቀት ኃይል ያጠመደ ( Concentrated Solar Power ) የተሰኘውን አውታር የዘረጋች ሀገር ደቡብ አፍሪቃ ናት።

Symbolbild Regenerative Energiequellen Wasser Wind Sonne
ምስል DW-Montage

ልዩ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳ ፋባሪካዋም ፣በአፍሪቃ ወደር ያልተገኘለት ነው።

አውሮፓ ውስጥ፤ በፀሐይ ኃይል የኤልክትሪክ ኃይል ማግኘት የሚያስችሉ አውታሮች በመጀመሪያ ከእስፓኝና ኢጣልያ ሌላ በጀርመን ነበረ የተዘረጉት። እ ጎ አ ከ 2013 ወዲህ በፀሐይ ኃይል ለሚሠሩ አውታሮች የሚዘጋጁ ልዩ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎች በገፍ ነበረ እየተሠሩ የሚቀርቡት። ጀርመንና ኢጣልያ ከሚያመርቱት በላይ ደግሞ፤ ቻይና፣ ጃፓንና ዩናይትድ ስቴትስ ማምረቱን ተያያዙት። ለጊዜው የቀረበው ግምታዊ ጥናት እንደሚጠቁመው ከሆነ እ ጎ አ በ 2014 ዓ ም፤ ቻይና ውስጥ 13 በጃፓን ዘጠኝ፤ በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ሰባት ጊጋዋት ኃይል ያላቸው ልዩ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎች የተመረቱት። በዚህ ረገድ የጀርመን ምርት ፤ በጣም ቀንሶ ባለ 2 ጊጋዋት ነበረ የቀረበው። እንዲያውም መጀመሪያ ላይ በዚህ ዘርፍ ተቀጥረው ይሠሩ ከነበሩት 127,000 መካከል፤ ከ 50 ,000 በላይ የሚሆኑ ከሥራ መሠናበታቸው ነው የተገለጠው። እ ጎ አ በ 2010 እና 2012 ግን በያመቱ ሰባት ጊጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያላቸው ልዩ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎች የተመረቱት። Solar wirtschaft የተሰኘው ሌላ ኩባንያ ዋና ጸሐፊ Jörg Mayer እንዲህ ይላሉ።

«ያኔ የነበረው መንፈስ ምንድን ነው--? ሁሉም ከሚገባ በላይ በምርት ማሳደጉ ረገድ እንዳሽቆለቆልን ተገንዝበው ነበር። በ 2014 ከ 2 ጊጋዋት በታች ኃይል የሚሰጡ ልዩ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎች የተመረቱት። አሁን በያዝነው 2015 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፣ ባፋጣኝ ምርትን ለማሳደግ የተዘጁ የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች መኖራቸውን ተመልክተናል። ስለሆነም ፤ በ 2014 ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከደረስንበት ሁኔታ በማንሠራራት ከዓለም አቀፉ ገበያ እንደምንሰለፍ ተስፋ አለ»።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁንም ፕሮፌሰር ዶ/ር አይከ ቬበር የሚሉት አላቸው።

«በ 2014 (እ ጎ አ ) በዓለም ገበያ በግምት 45 ጊጋዋት የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ ልዩ አውታሮች የተተከ ሲሆን ፤ ሥራው ፣ ወደፊት ይበልጥ እየተስፋፋ ነው የሚኼደው። በ 2020 ፣ የጊጋዋቱ መጠን በ 100 እና 150 ከፍ ማለቱ አይቀርም ። ይህ ደግሞ ፈጣን ዕድገት የሚባል ነው የሚሆነው። »

የ Solarworld ኩባንያ ቃል አቀባይ ሚላን ኒችከ እንደሚሉት፤ የሚመጡት ዐሠርተ ዓመታት በዚህ ረገድ የአፍሪቃ የዕድገት ዘመን ነው የሚሆነው።

Solarbetriebener Wagen in Äthiopien
ምስል Phaesun

ፕሮፌሰር ዶ/ር አይከ ቬበር፤ ስለወደፊቱ ዝርዝር አቅድና አዲስ ሥነ ቴክኒክ ስላስጨበጠው ተስፋ ሲያብራሩ ---

«እ ጎ አ ከ 2017 እና 2018 አንስቶ ተግባራዊ የሚሆነው፤ የአዲሱ ሥነ ቴክኒክ ዝርዝር እቅዳችን ፤ አሁን በፍርይቡርግ የሚገኘውን ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ አውታር ተጋግባር የሚገታ ይሆናል ። ይህ ደግሞ በኪሎዋት በሰዓት 6 ዩውሪ ሳንቲም የሚያስወጣ ነው። እናም በዚያው ተመሳሳይ አውታር ቫሌንትሲያ (እስፓኝ ) ውስጥ ፣ በኪሎዋት ሰዓት ከ 3 እስከ 4 ሳንቲም ብቻ ሊከፈልበት የሚችለውን ኃይል ማመንጨት አያዳግትም። ይህ ደግሞ በጀርመን፣ ከልዩ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎች በአሁኑ ጊዜ ከሚከፈልበት ዋጋ በእርግጥ ዝቅ ያለ ነው የሚሆነው። »

በዓለም ገበያ 80 ከመቶውን ፣ ብርሃንና ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎችን በመሸጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዘች ቻይና ናት። በመንግሥት ጠንካራ ድጎማ ነው ከዚህ ደረጃ ለመድረስ የበቃች በማለት የ «ሶላርወርልድ» ኩባንያ ቃል አቀባይ ሚላን ኒችከ ከመውቀሳቸውም፤ ጀርመን ፣ በዚህ ረገድ በከፍተኛ ደረጃ እንቅሥቃሴ ማድረግ ይበጃታል ብለዋል።

«እኛ አሁን እንደ ቀድሞው የዚህ ሥነ ቴክኒክ ማለትም በፀሐይ የኤልክትሪክ ኃይል አመንጪ ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሽ ሆነናል። የኃይሉ መጠን እንዲጨምር ምርቱም ፍጹም ጥራት እንዲኖረው ማብቃት ይኖርብናል። ስለሆነም ፤ በዓለም ዙሪያ ከታወቁት 10 ሃገራት ተራ መሰለፍ አለብን። ከቻይና ቀጥሎ በብዛት ሙቀት ሳቢና ወደ ኤሌክትሪክ ለዋጭ ሰሌዳዎችን በማምረት የ2ኛነቱን ደረጃ ይዘናል። በዚያው መቀጠልና ማሳደግ ይኖርብናል።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ