1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠፋዉ የማሌዢያ አዉሮፕላን ጉዳይ

ሐሙስ፣ የካቲት 26 2007

ከጠፋ አንድ ዓመት ሊሞላዉ ጥቂት ቀናት የቀረዉ የማሌዢያ አዉሮፕላን ጉዳይ ዛሬም እንዳነጋገረ ነዉ። በበረራ ታሪክ ለደረሰ አደጋ ከፍተኛ ወጪና ኃይል አሰባስቦ ከተከናወነ ፍለጋ በኋላ ያለ ዉጤት የተጠናቀቀበት የበረራ ቁጥር MH 370። አዉሮፕላኑ የጠፋበት ቀን ሲታሰብ ፈላጊዎቹ ለተሳፋሪዎቹ ቤተሰቦች የሚሰጡትን የመጨረሻ ቃል እየፈለጉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1EmGA
Suche Malaysian Airlines MH370 22.03.2014
ምስል Reuters

ወዳጅ ዘመዶቻቸዉን አጋጣሚዉ ያጡት ወገኖችም አንዳች ምላሽ እናገኝ ይሆን የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። እስካሁን ግን በበርካታ ሚሊዮን የሚገመት ወጪ ለፍለጋዉ ቢፈስም የማሌዢያዉ አዉሮፕላን ግን እዚህ ጋ ነዉ የወደቀዉ የሚል ፍንጭ አልተሰማም።

ኳላላምፑር በሚገኘዉ አንድ ታዋቂ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዉስጥ ከጠፋ የፊታችን እሁድ አንድ ዓመት የሚደፍነዉን የማሌዢያዉን አዉሮፕላን በመፈለግ የሚተባበሩ የአዉስትራሊያ፤ የቻይና እና የባለቤቷ የማሌዢያ ባለስልጣናት ተቀምጠዋል። ለወትሮዉ በዚህ ስፍራ የገባበት እስካሁን ያልታወቀዉ የበረራ ቁጥር MH 370 የማሌዢያ አዉሮፕላን የበረራ ሠራተኞች እየተሰባሰቡ አንዱ ሌላዉን ለመደገፍ ይሚመካከሩ፤ ይነጋገሩበት ነበር። የጠፋዉ አዉሮፕላን ተሳፋሪ ቤተሰቦች እስካሁን ይህ ነዉ የሚባል ዉጤት ባለመስማታቸዉ ልባቸዉ እንደተንጠለጠለ፤ አንዳንዴም አዉሮፕላኑ ምን እንደደረሰበት ስላልተነገረ የተስፋ ጭላንጭል እየታያቸዉ በዋዠቀ ስሜት እንዳሉ አሉ። ካልቪን ሺም የማሌዢያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረች ባለቤቱን በዚህ አጋጣሚ አጥቷል። እሱም ሆነ ሌሎች የሆነዉን ሁሉ መቀበል እንዲችሉ ምላሽ እንፈልጋለን ይላል።

Bildergalerie MH 370 Suche
ምስል Reuters/Australian Defence Force

«የሆነ ምላሽ ማግኘት እፈልጋለሁ ገባህ፤ ራሴን ለማሳመን ምንም ዓይነት ቢሆን መልስ እፈልጋለሁ።»

ከኳላላምፑር በሀገሩ አቆጣጠር ከቀኑ 6 ሰዓት ከ41 ደቂቃ ሲሆን ተነስቶ ወደቤጂንግ ያቀናዉ የማሌዢያ አዉሮፕላን በረራ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ዉስጥ የቪየትናምን የበረራ ክልል እንኳ ሳያልፍ መሬት ላይ ከሚገኘዉ የሲቪል የበረራ መቆጣጠሪያ ጣቢያ እይታ ቢሰወርም ከአንድ ሰዓት በላይ በወታደራዊ የበረራ መቆጣጠሪያ እይታ ዉስጥ እንደነበር ነዉ የሚነገረዉ። እንዲያም ሆኖ የጦር ኃይሉ የወሰደዉ ርምጃ አልነበረም። የማሌዢያ አየር ኃይል አዛዥ አዉሮፕላኑ ወደኳላላምፑር ተመልሶ ይሆናል ብለዉ ነበር። በተቃራኒዉ ሁለት የተሰረቁ የይለፍ ሰነዶች የያዙ መንገደኞች በዚህ አዉሮፕላን ተሳፍረዋል መባሉ የአሸባሪ ጥቃት ደርሶበት ይሆን የሚል ጥርጣሬ አስነሳ። ይህ ግን የማሌዢያ ፖሊስ ባደረገዉ ምርመራ ሰዎቹ ኢራናዉያን ሕገወጥ ስደተኞች መሆናቸዉን ከመግለጹ ዉጭ ስለአደገኝነታቸዉ ያሳየዉ መረጃ የለም። እንዲህ እንዲህ እያለም ቀናት ቀናትን ሳምንታት ወራትን እየወለዱ ፍለጋዉ ተጠናክሮ ቀጠለ። 239 ተሳፋሪዎችን ይዞ የተሰወረዉን አዉሮፕላን ለማግኘትም 120 ሚሊዮን የአዉስትራሊያ ዶላር ወይም 83 ሚሊዮን ፈሷል። በከባድና አደገኛ ማዕበል በሚታመሰዉ ደብባዊ የህንድ ዉቅያኖስ ላይም 60ሺህ ስኩየር ኪሎሜትር አካባቢን የሸፈነ በመርከቦችና አዉሮፕላኖች የታገዘ አሰሳም ተካሄደ። እስካሁን ግን አንዳችም ፍንጭም ሆነ ዉጤት የለም። ሁኔታዉ ያሰላቻቸዉ የመሰሉት የአዉስትራሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዋረን ትሩስ ፍለጋዉ እልባት እንዲኖረዉና የተሳፋሪዎቹ ቤተሰቦችም የተገኘዉን ዉጤት ይስሙ ነዉ የሚሉት።

Suche MH 370 Malaysia Airlines
ምስል cc-by/ATSB/Photo by Chris Beerens/RAN

«በርካታ የተሳፋሪዎቹ ቤተሰቦች አዉሮፕላኑ ተገኝቶ እንደሆነ ለማወቅና ከተቻለም የወዳጆቻቸዉ አስከሬን ተገንኝቶም ከሆነም ማወቅ ይሻሉ። ይህ ነዉ የአብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ቤተሰቦች ፍላጎት። እኛም እነሱ ማወቅ የሚፈልጉትን እንዲያዉቁ ለማድረግ የምንችለዉን ሁሉ እያደረግን ነዉ። እናም ለዘለዓለም እንዲህ እያደረግን መቀጠል አንችልም አንድ ቦታ ላይ ዉሳኔ መሰጠት ይኖርበታል።»

ከአዉሮፕላኑ አብራሪዎች የአንዱ ባለቤት የሆኑት አኩዊታ ጎንዛሌዝ ግን ተስፋ የቆረጡ አይመሉም። የማሌዢያ መንግሥት አዉሮፕላኑን እስኪያገኝ የጀመረዉን ፍለጋ አላቆምም ያለነዉን ቃሉን ቢጠብቅ ይመኛሉ።

«ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ የማሌዢያ መንግሥት አዉሮፕላኑ እስኪገኝ ድረስ ፍለጋዉን እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል። ይህን ቃላቸዉን ይጠብቃሉ ብዬ እገምታለሁ። ሆኖም ግን ፍለጋዉን ካቆሙ ምን ማድረግ እችላለሁ። እንደአንድግለሰብ እኔ ምን አደርጋለሁ? አቅሙም የለኝም። ግን እንዳይረሱት መጠየቃችንን እንቀጥላለን።»

እሳቸዉ ይህን ቢሉም ግን በተቃራኒዉ አዉሮፕላኑ የጠፋበት ዓመት ከመታሰቡ አስቀድሞ እጅግ አድካሚ ቢሆንም ካለዉጤት የተጠናቀቀዉ የፍለጋ ዘመቻ ማክተሙ ይፋ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ሆኖም እንደሳቸዉ ሁሉ ሌሎችም ተመሳሳይ ሃሳብ ነዉ ያላቸዉ፤ አዉስትራሊያን ጨምሮ በፍለጋዉ የተባበሩ ሌሎች ሃገራት በቃ ታከተን ቢሉ እንኳ የማሌዢያ መንግሥት አሰሳዉን መቀጠል አለበት ባዮች ናቸዉ። ሊ ኪም ሚስታቸዉን በዚሁ አደጋ አጥተዋል፤

Suche MH 370 Malaysia Airlines
ምስል cc-by/ATSB and Geoscience Australia

«ፍለጋዉ ይቁም በሚለዉ በፍፁም አልስማማም። በተለይም የእኛ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍለጋዉ እንደሚቀጥል በየጊዜዉ ቃል ሲገቡልን ነበር። እናም ፍለጋዉን ለማቆም የሚያበቃ ምንም አሳማኝ ምክንያት አይኖርም።»

ባለፈዉ ዓመት የካቲት 29 ቀን የማሌዢያዉ አዉሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ሲሰወር የተለያዩ ጥርጣሬዎች ተሰንዝረዉ ነበር። እስካሁንም ምን እንደደረሰበት ይህ ነዉ የሚል አሳማኝ ማብራሪያ አልተሰማም። ወዳጅ ዘመዶቻቸዉን በዚህ አጋጣሚ ያጡት ወገኖች አንዳችም ግምት ከመሰንዘር ተቆጥበቁ ያሉበትን ለማወቅ እንደጓጉ ነዉ። ተካሂዷል የሚባለዉን ፍለጋና አሰሳም የሚያምኑ አይመስሉም።

ዑዶ ሽሚት/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ