1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዛው ድብደባ ተጠናክሮ መቀጠል

ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 2006

የእስራኤል የጋዛ ድብደባ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል ። እስራኤል ተጨማሪ ተጠባባቂ ጦር ወደ ጋዛ አዝምታለች ። የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችም ወደ ደቡባዊ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሳቸውን ቀጥለዋል ። ስደተኞች በተጠለሉበት በጋዛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትምሕርት ቤት ላይ የደረሰውን ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና አሜሪካን አውግዘዋል ።

https://p.dw.com/p/1Cn5A
Gaza Zerstörung Moschee Gaza Stadt Minaret
ምስል Reuters

ደም መፋሰሱ እንዲቆም ዓለም ዓቀፍ ጥሪ ቢቀርብም የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ በጋዛው ዘመቻ ለመግፋት ወስኗል ። እስራኤል በጋዛ አጠናክራ የቀጠለችው ድብደባ እንዲህ በቀላሉ የሚቆም አይመስልም ። ዛሬ ተጨማሪ 16 ሺህ ተጠባባቂ ጦር ወደ ጋዛ ማዝመቷን አረጋግጣለች ።በጋዛው ዘመቻ የተሰለፈው ተጠባባቂ ጦር ቁጥር አሁን ወደ 86 ሺህ ከፍ ብሏል ። የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔም ጦሩ ጥቃቱን አስፋፍቶ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል ። ድንበር ተሻጋሪ የዋሻ መስመሮች ሙሉ በሙሉ እስኪወድሙ ድረስ ወታደሮቿ ከጋዛ እንደማይወጡ እስራኤል አስታውቃለች። እስራኤል ዘመቻውን እንድታቆም ተደጋጋሚ ጥሪ በሚቀርብበት በዚህ ወቅት ላይ አሜሪካን እየተመናመነ በመሄድ ላይ ያለውን የእስራኤል የጥይት ክምችት ለመተካት ተስማማታለች ። የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችም ወደ ደቡባዊ እስራኤል ጓዳ ሰራሽ ሮኬቶችን መተኮሳቸውን ቀጥለዋል ።ትናንት ብቻ ከጋዛ ወደ ደቡብ እስራኤል ከ130 በላይ ሮኬቶች ተወንጭፈዋል ።ሁለት ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው አሁን የሚታሰብ አይደለም ።የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ዛሬ ልዩ የካቢኔ ስብሰባ ከመጀመራቸው በፊት እንደተናገሩት የእስራኤልን ጦር ወደ ጋዛ ከዘመተበት ዓላማ የሚያደናቅፍ ማንኛውንም የተኩስ አቁም ሃሳብ አይቀበሉም ።

Gaza Zerstörung Feuer Rauch Bombe Einschlag
ምስል Reuters

«እስካሁን በርካታ የአሸባሪዎች ዋሻዎችን አውድመናል ። ይህን ዘመቻችንን በተኩስ አቁምም ሆነ ያለ ተኩስ አቁም ከፍፃሜ ለማድረስ ቆርጠን ተነስተናል ። ስለዚህ ለእስራኤል ደህንነት ስል የእስራኤል ጦር ይህን ዋነኛ ተግባር ከፍፃሜ እንዳያደርስ በሚያደርግ ማንኛውም ሃሳብ አልስማማም »

ትናንት ብቻ የሞቱት ፍልስጤማውያን ቁጥር ወደ 119 ከፍ ብሏል ።እስከዛሬ ከቀትር በኋላ ድረስ በእስራኤል የጋዛ ድብደባ ጋዛ ውስጥ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 1370 በልጧል። የቆሰሉት ቁጥር ግሞ 7680 ናቸው። በትናንቱ ጥቃት ከሞቱት መካከልበሰሜን ጋዛ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትምህርት ቤት ሲመታ የተገደሉት 20 ሰላማዊ ሰዎች ይገኙበታል ።በዚሁ ጥቃት 85 ሰዎች ቆስለዋል ። የእስራኤል ወታደሮች በአካባቢው በነበረ መስጊድ አቅራቢያ ከተደበቁ ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር ሲታኮሱ የደረሰው ይኽው ዘግናኝ ጥቃት በእጅጉ ተወግዟል ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን ከምንም ጋር የማይስተካከል ያሉትን ይህን ጭካኔ አውግዘዋል ።

«ሴቶችና ህፃናት ደህንነታቸው እንደሚጠበቅ በተረጋገጠበት በዚህ ስፍራ ተኝተው ነበር ። ዘገባዊች እንደሚያመለክቱት ቢያንስ 16 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል ። ጥቃቱን በፅኑ አወግዛለሁ ። እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ተግባር ለመፈፀም ምንም ምንም አሳማኝ ምክንያት የለም።»

Lage in Israel Palästina (Tag der Waffenruhe)
ምስል Mahmud Hams/AFP/Getty Images

ዩናይትድ ስቴትስም በጃባልያ ትምህርት ቤት ላይ የደረሰውን የትናንቱን ጥቃት አውግዛለች ። የአሜሪካን ብሔራዊ የፀጥታ ምክርቤት ቃል አቀባይ ቤርናዴት ሜሃን የእስራኤል ጦር ከየቤታቸው እንዲወጡ ያዘዛቸው ፍልስጤማውያን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠለያዎችም ውስጥ ደህንነታቸው አለመጠበቁ በእጅጉ ያሳስበናል ብለዋል ።ቃል አቀባይዋ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችም በስፍራው የጦር መሳሪያዎችን መደበቃቸውን እንዲሁ አውግዘዋል ።

የእስራኤል የጋዛ ጥቃት እንዲቆም አሜሪካንም ለእስራኤል መሣሪያ መስጠቷን እንድታቆም ዓለም ዓቀፍ ጥሪ ቢቀርብም ሰሚ አላገኘም ። እስራኤል እንደምትለው ጋዛ የሚገኙ ዋሻዎችን ለመደምሰስ አጠናክራ የቀጠለችው ዘመቻ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ