1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የሩዋንዳ ትብብር

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2006

የጀርመን ሩዋንዳ ትብብር በመግባባትና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ የሩዋንዳ ባለስልጣን አመለከቱ። የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር ዴታ ማቲያስ ሃርባሙንጉ ሀገራቸዉ በአሁኑ ወቅትም በትምህርት ዘርፍ ከጀርመን የዳበረ ልምድ እየተጠቀመች ነዉ ይላሉ።

https://p.dw.com/p/1BfuK
Symbolbild Beziehungen Deutschland Ruanda
ምስል John MacDougall/AFP/Getty Images

በልማት ትብብር ረገድ ሩዋንዳ ዓለም ዓቀፍ ተወዳጅነት ያተረፈች ሀገር መሆኗ ይነገርላታል። ዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ፣ በዚህ በኩል ከሀገሪቱ ጋ በቅርበት ይሠራሉ። ፈረንሳይ፣ ቤልጂግ፣ ብሪታንያ፣ እንዲሁም ቻይና ለኪጋሊ ዋነኛ ተጓዳኞች ናቸዉ። የሃምበርግ የማኅበራዊ ምርምር ተቋም ባልደረባ ጌርድ ሃንከል እንደሚሉት ሩዋንዳ በለጋሾች ተመራጭ ያደረጋት የምታገኘዉን የርዳታ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ አዉላ በመታየቷ ነዉ፤

«በልማት ትብብሩ ረገድ ሩዋንዳ እንደ ብርሃን ማማ እንድትታይ ያደረጋት እንደሀገር የምታገኘዉን የርዳታ ገንዘብ በትክክል በአግባቡ ስለምትጠቀም ነዉ። በተለይም ይህ የብርሃን ማማ በአካባቢዋ ከሚገኙ ሃገራት ለምሳሌ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ እንዲሁም ደግሞ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ አኳያ ሲታይ ይበልጥ ይደምቃል።»

የዘር ማጥፋት ከተፈጸመበት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1994ዓ,ም ወዲህ ሩዋንዳ ያን አሰቃቂ ታሪኳን ወደኋላ በመተዉ በልማት ጎዳና ትርጉም ያለዉ ለዉጥ እንዳስመዘገበች ይነገርላታል። የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር ዴታ ማቲያስ ሃረባሙንጉ ምንም እንኳን ሩዋንዳ በአሁኑ ወቅት ኤኮኖሚዋ 60 በመቶ ራሱን ችሎ ለመቆም በቅቷል ቢባልም ቀጣይ የዉጭ ርዳታ ያስፈልጋታል ይላሉ። በተለይም በትምህርት የታነፀ ትዉልድ ለማፍራት በሚያከናዉናቸዉ ተግባራት የጀርመንን ድጋፍ እንደሚሻ አመልክተዋል።

Neues Rathaus von Kigali im Bau
ምስል DW/A. Le Touzé

«በእዉቀት የታነፀ ማኅበረሰብ ለማሳደግ እንፈልጋለን። ለዚህም ከጀርመን የትምህርት ሥርዓታችን እና የትምህርት መሣሪያዎቻችን ላይ ያተኮረ ድጋፍ እንሻለን።»

ጀርመን የሩዋንዳ ዓይነተኛ ተጓዳኝ ናት። በሁለትዮሹ ትብብርም በርሊን ለኪጋሊ የምትሰጠዉ ርዳታ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጀርመን ለሩዋንዳ ከምትሰጠዉ ድጋፍ ገሚሱ የሚመጣዉ ከሀገሪቱ የራይንላንድ ፋልስ ፌደራል መንግስት ነዉ። የጀርመኑ ራይንላንድ ፋልስ ፌደራል መንግስት ከሩዋንዳ ጋ በተጓዳኝነት ሢሠራ ከ30 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1982ዓ,ም አንስቶ ነዉ ፌደራል መንግስቱ አንድ ሀገር ላይ ብቻ አተኩሮ የልማት ትብብሩን ለማከናወን የወሰነዉ። የራይንላንድ ፋልስ እና የሩዋንዳ ትብብር ፕሬዝደንት ሪሻርድ አወርንሃይመር እንደሚሉት ለየት ያለ ነዉ፤

«የተለየዉ ነገር ምንድነዉ፤ ዜጎቻችን ከሩዋንዳ ዜጎች ጋ ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸዉ። በርካታ የራይንላንድ ፋልስ ኗሪዎች የግል ፕሮዤዎቻቸዉን የእኛ ድጋፍና ትብብር ሳያስፈልጋቸዉ ራሳቸዉ እያካሄዱ ነዉ።»

ከሩዋንዳ ጋ ለሚከናወኑ የልማት ትብብር ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ ከጀርመን መንግስትና ከፌደራል መንግስቱ የሚገኝ ቢሆንም ከሕዝብ የሚሰበሰዉ ልገሳም 30 በመቶዉን እንደሚይዝ አመልክተዋል። በዚህም 361 ሺ ገደማ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መቻሉንም ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ አሁን የሩዋንዳ ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ሳንክ ገጥሞታል። ከምክንያቶቹ አንዱ የተመድ ባለሙያዎች ከሁለት ዓመት በፊት ኪጋሊ ምሥራቅ ኮንጎ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ አማፅያንን ትደግፋለች የሚል ዘገባ ይፋ ማድረጋቸዉ ነዉ። ከዚያም ጀርመን ለሩዋንዳ መንግስት የምትሰጠዉን በሚሊዮኖች የሚገመት ዶላር አቆመች። ከጥቂት ወራት በኋላም የሀገሪቱ የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ኪጋሊ በሰላም ሂደቱ መልካም ሚና መጫወቷን በመግለፅ ማዕቀቡን መላላቱን አስታወቁ። ሆኖም የወቅቱ የጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ድሪክ ኒብል ሀገሪቱ የገንዘብ ድጋፍ የምትሰጠው በቀጥታ ለመንግስት ሳይሆን ለፕሮጀክቱ እንደሚሆን አመለከቱ ። በሌላ በኩል ደግሞ የሩዋንዳ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ባለመሆን ይተቻል።

Paul Kagame Präsident Ruanda
ምስል picture-alliance/dpa

ባለፈዉ መስከረም ምክር ቤታዊ ምርጫ ሲከናወን የተቃዉሞ ሰልፎች እንዳይካሄዱ ቢሮክራሲዉ ማነቆ እንደሆነባቸዉ ታይቷል። ዓለም ዓቀፍ ሕጎችን ከመጣስ በተጨማሪ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ በሀገሪቱ ይህን ነዉ የሚባል ተቃዋሚ እንዲኖር ባለማስቻላቸዉ ይተቻሉ። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽlታይንማየር ልማት እድገትና ዴሞክራሲ አይነጣጠሉም የሚል አቋም አላቸዉ። ፕሬዝደንት ካጋሜ ለልማት ቅድሚያ እንደሰጡ ሁሉ ዴሞክራሲም ሊከተለዉ ይገባል ነዉ ያሉት። የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር ዴታ ሐረባሙንጉ መንግስታቸዉ ይህን መሰል ትችት አይቃወምም ይላሉ። ትችትቱ ግን ገንቢ መሆን አለበት፤

«ሌላዉ ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ዉስጥ ወላጆችና ልጆች በጋራ ተቀምጠዉ ትችት በመሰንዘር የማያግባቡ ነጥቦች ላይ ሊወያዩ ይችላሉ። ሩዋንዳ የማትቀበለዉ እዉነት ያልሆኑ ጭምጭምታና ምንጩ የማይታወቅ ጉዳይ ሲነዛ ነዉ። ስለሀገራችን እዉነታዉን ማወቅ የሚቻልበት ብቸኛዉ መንገድ ባለስልጣናትና ዜጎችን መጠየቅ ነዉ።»

የራይንላንድ ፋልስ እና የሩዋንዳ ትብብር ፕሬዝደንት ሪሻርድ አወርንሃይመር በበኩላቸዉ ከዴሞክራሲ አኳያ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙ አዉሮጳ ልትወስድ የምትችለዉ ርምጃ መኖሩን ያመለክታሉ።

«አንዳንድ ርምጃዎች ልማትን የሚያደናቅፉ በመሆናቸዉ ምክንያት አዉሮጳ ይህንን መሠረታዊ መርሕ ማጠናከር ይገባር ነበር። ሩዋንዳም ርምጃዋን አጢና በተገቢዉ አቅጣጫ ወደፊት መራመድ ይገባታል። ይህንን መብት እኛ አዉሮጶች ለረዥም ጊዜ ተጠቅመንበታል።»

ፊሊፕ ዛንደነር/ ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ