1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደራሲዉ ህያዉ ብዕር «ጉንተር ግራስ»

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 8 2007

የጉንተር ግራስ ሥነ-ጽሑፎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በአማርኛ ከተተረጎሙት የጉንተር ግራስ አጫጭር ድርሰቶች መካከል በጀርመንኛ ሊንክስ ሄንድር የሚለዉ ጽሑፍ መሆኑን በአዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን የባህል ማዕከል የቤተ-መጽሐፍት ክፍል ገልጾአል።

https://p.dw.com/p/1F9fo
Deutschland Geschichte Film Filmszene Die Blechtrommel
«የቆርቆሮ ከበሮ» የተሰኘዉ የጉንተር ግራስ ልበወለድ ታሪክ በፊልምም ቀርቧልምስል ullstein - Tele-Winkler

በሳምንት መጀመርያ ሰኞ (13.04.2015) ታዋቂዉ ጀርመናዊ የሥነ-ጽሑፍ ጉንተር ግራስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ ከተሰማ በኋላ ከሃገር ዉስጥና ከተለያዩ የዓለም ሃገራት የሃዘን መግለጫ እየጎረፈ ነዉ። የጀርመን የተለያዩ የብዙሃን መገናኛዎችም የእዉቁን የሥነ-ጽሑፍ ሰዉ ሥራዎች እያነሱ ደራሲዉን በመዘከር ላይ ይገኛሉ። ከሥነ- ጽሑፍ ሌላ፤ በማሕበራዊና ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሰላ ብዕራቸዉን በመሰንዘራቸዉ ይታወቁ የነበሩት ጉንተር ግራስ የፖለቲካ ፈጣሪም ተደርገዉ ይታዩ ነበር።


በ 87 ዓመታቸዉ በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ሰኞ (13.04.2015) ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታዋቂዉ ጀርመናዊ የሥነ ጽሑፍ ሰው ጉንተር ግራስ ፣ ቀራጺና ሠዓሊም ነበሩ። ጉንተር ግራስ በጎርጎረሳዉያኑ 1929 ዓ,ም በዛሬዋ የፖላንድ የወደብ ከተማ ዳንትዚግ ዉስጥ ነዉ የተወለዱት። ጀርመናዊዉ ጉንተር ግራስ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ በ1959 ዓ,ም የጻፉት «የቆርቆሮ ከበሮ» በጀርመንኛ መጠርያዉ «Die Blechtrommel» የተሰኘዉ ልብ ወለድ መጽሐፋቸው እዉቅናን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ዝናን አስገኝቶላቸዋል። በዚሁም ሥነ - ጽሑፋቸዉ በጎርጎረሳዊዉ 1999 ዓ,ም የሥነ- ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እዉቅናን ያገኙት የጉንተር ግራስ የሥነ-ጹሑፍ ሥራዎች በአማርኛ መተተርጎማቸዉን በተመለከተ በአዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን የባህል ማዕከል የቤተ-መጽሐፍትና የኢንፎርሜሽ ሃላፊ ዮናስ ታረቀኝ ተናግረዋል።

Verleihung des Literatur-Nobelpreises 1999 an Günter Grass
ጉንተር ግራስ በጎአ1999 የሥነ- ጽሑፍ ኖቤል ሽልማትን ሲቀበሉምስል AP


ከሥነ- ጽሑፍ ሌላ፤ በማሕበራዊ የፖለቲካ ሕይወት ክርክር ይወዱ የነበሩት ጉንተር ግራስ፣ የቀድሞው የጀርመን መራኄ መንግሥት፣ ቪሊ ብራንት፤ ከፖላንድ ጋር ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ የተከተሉትን የውጭ የፖለቲካ መርሕ ከመደገፋቸውም በላይ፣ በምርጫ ዘመቻ ለሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ (SPD) መታገላቸው ይነገርላቸዋል። ምክትል መራሄ መንግሥታና የሶሻል ዴሞክራቱ ፓርቲ ዋና ተጠሪ ዚግማር ገብርኤል የጉንተር ግራስን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በሰሙበት ወቅት እዉቅ የሥነ-ጽሑፍ ሰዉ ብቻ አይደለም ነዉ ያጣነዉ ነበር ያሉት።


«በርግጥ፣ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ወዲህ በጀርመን የሥነ-ፅሑፍ ዘርፍ ጉልህ ሚናን ያበረከተ ጀርመናዊ ደራሲን ብቻ ሳይሆን ያጣነዉ፤ እጅግ ጥሩ እና ትልቅ የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ ወዳጅንም ነዉ። ከቪሊ ቭራንት ጋር በጋራ በመሥራት ያበረከቱትም ድርሻ የሚደነቅ ነው።

Buchcover Biografie Günter Grass EINSCHRÄNKUNG
የጉንተር ግራስ-የሕይወት ታሪክምስል Oskar

ከዚያም በኋላ በቀጠሉት ዓመታት፣ እስካለፉት ሳምንታትና ወራት ድረስም ገንቢ አስተያየት እና ግንዛቤ ያስጨበጡ ትንታኔ በመስጠት ከሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲያችን ጋ አብሮ ተጉዟል። በሌላ በኩል ጉንተር ግራስ እንደ አንድ የተከበረ ታላቅ ምሑር በጀርመንና በአዉሮጳ በተካሄዱ ክርክሮችና ዉይይቶች ላይ የበኩላቸውን አሻራ ያሳረፉ ደራሲም ነበሩ። በጉንተር ግራስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ከብዙሃኖች ጋር በጋራ ጥልቅ ሃዘን ላይ እንገኛለን። »


ጀርመን ካፈራቻቸዉና በተለይ በዓለም ዓቀፍ መድረክ እዉቅናን ካገኙና የኖቤል ሽማትን ከወሰዱ የጀርመን ደራስያን መካከል የጉንተር ግራስ ግጥሞችና ልብ-ወለዶች እዚህ በጀርመን ረዘም ላለ ጊዜ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድም ተወዳጅ መሆናቸዉን በጀርመን ከአርባ ዓመታት በላይ የኖረዉ የዶቼ-ቬለ ጋዜጠኛ ይልማ ኃይለሚካኤል ተናግሮአል።
እዉቁ ጀርመናዊ ደራሲ ጉንተር ግራስ ፤ በመጨረሻው የአዛውንት ሕይወታቸው በጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ,ም ፤ በናዚ ጀርመን ጦር ውስጥ በውጊያ ረዳት ወታደርነት ብቻ ሳይሆን ከ 1844 ዓም ጀምሮ የናዚ ፓርቲ ልዩ ጦር አባል እንደነበሩም በሥነ ፅሑፋቸዉ አምነዋል። ይህን ጉዳይ እስከዛን ጊዜ ድረስ ይፋ ባለማድረጋቸው የተፈራረቀባቸውን ወቀሳ ትክክለኛ ሲሉ ነበር የተቀበሉት ያሉት

Bildergalerie Günter Grass Waffen SS US Dokument
ጉንተር ግራስ በናዚ ጀርመን ጦር ውስጥ በውጊያ ረዳት ወታደር እንደነበሩ የሚጠቁመዉ መታወቅያምስል Sean Gallup/Getty Images


« ስለዚህ ጉዳይ ለመጀመርያ ጊዜ መናገር የቻልኩት አሁን ነዉ ። ሊፈርድብኝ የፈለገ መፍረድ ይችላል።»
እንድያም ሆኖ ጉንተር ግራስ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ እአአ በ1959 ዓም ባወጡት የመጀመሪያ ድርሰታቸው በናዚ ጦር በፈጸመው ወንጀል ላይ የጀርመናዉያንን ጥፋተኝነት ካጠያየቁት የመጀመርያዎቹ ደራስያን መካከል አንዱ ነበሩ። ጉንተር በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሁሉ ነገር የተከሰተዉ እያወቅን ነዉ ነበር ያሉት።


« እስካሁን ድረስ የሆነ መንፈስ ጀርመኖችን ጥፋት እንዲሰሩ ያታለላቸዉ ወይም የገፋፋቸዉ ተደርጎ ነው ሲቀርብ የነበረው። ይህ ግን ስህተት ነዉ። በዚያን ጊዜ በነበረኝ የወጣትነት አመለካከቴ እንኳን ይህ ልክ እንዳልሆነ አዉቅ ነበር። ይህ ሁሉ ነገር የተከሰተዉ እያወቅን ነዉ። » ፒፓ ወይም ጋያ ሲጃራን ለኩሰዉ መነጥራቸዉን አፍንጫቸዉ ላይ ሸትረት አድርገዉ አስቀምጠዉ ጢሱን ቡልቅ እያደረጉ ብዕራቸዉን ይዘዉ የሚታዩት ጉንተር ግራስ አከራካሪ በሆኑ ጽሑፎቻቸዉንና ርዕሶቻቸዉ እንደሚታወቁም በጀርመን ረዘም ላለ ግዜ የሚኖረዉ ጋዜጠኛ ይልማ ኃይለሚካኤል ይገልጻሉ።


የጉንተር ግራስ ሥነ-ጽሑፎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በአማርኛ ከተተረጎሙት የጉንተር ግራስ አጫጭር ድርሰቶች መካከል በጀርመንኛ ሊንክስ ሄንድር የሚለዉ ጽሑፍ መሆኑን በአዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን የባህል ማዕከል የቤተ-መጽሐፍትና የኢንፎርሜሽ ሃላፊ ዮናስ ታረቀኝ ገልፀዉልናል።
በጎርጎረሳዉያኑ 2009 ዓ,ም ጀርመን ላፕዚግ ከተማ በተካሄደዉ የመጽሐፍ ዓዉደ ርዕይ ላይ ተገኝተዉ የጉንተር ግራስን ንግግር በቀጥታ በመድረክ መከታተላቸዉን ዮናስ ታረቀኝ ገልፀዋል። ደራሲ ጉንተር ግራስ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ ፋሺስትን በጥብቅ በመቃወማቸዉ የሚታወቁት የመጀመርያዉ የጀርመን ሬፐብሊክ መራሄ መንግሥት ከቪሊ ብራንት ጋር የቅርብ ጓደኛም ነበሩ። ግራስ የወግ አጥባቂ የቀን ክንፍ ቡድኖችን ወይም ናዚዎችን ባሰሙዋቸው ንግግሮቻቸው ከመተቸት ወደ ኋላ ብለው አያውቁም ነበር።

Neueröffnung Günter Grass-Haus Lübeck
ጉንተር ግራስምስል picture-alliance/dpa/Gambarini

የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ጉንተር ግራስን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት እንደሰሙ ይህን ነበር የተናገሩት « ባለፉት ዓመታት በወጣቱ ትዉልድ ዘንድ ጉንተር ግራስ ከአንድ አስጠንቃቂ መሪ የላቀ ተድርገዉ ቢታዩም፤ በኔ ትዉልድ ባሉት ዘንድ የሚታወቁት አዲስ የተመሰረተችዋን የጀርመን ፊደራል ሬፐብሊክ ስነ ጽሑፍ እና አስተሳሰብ በማነጽ ዓቢይ ሚና የተጫወቱ አባታዊ ክብር የተላበሱ ግለሰብ በመሆናቸው ነው »


እዉቁ ጀርመናዉ ደራሲ ጉንተር ግራስ ባለፈዉ ሰኞ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ እንደተሰማ የጀርመን የመገናኛ ብዙኃን መገናኛ ሥራዎቻቸዉን እያነሱ በመዘከር ላይ ይገኛሉ። ስለ ታዋቂዉ ጀርመናዊ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚ ጉንተር ግራስ ያወሳንበትን መሰናዶ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።


አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ