1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬን ወቅታዊ ሁኔታ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 17 2006

የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ ምዕራቡ ዓለም ዩክሬይንን ለመቆጣጠው እያሴረ ነው ሲሉ ወቀሱ። በደቡብ ምሥራቅ ዩክሬይን የሚገኙት መፍቀሬ ሩስያ ሚሊሺያዎች የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን የሚፈቱት በመዲናይቱ ኪየቭ የተተከለው የተቃውሞ ሰፈር ሲበተን ብቻ መሆኑን ላቭሮቭ አክለው አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/1Bo6k
Ukraine Konflikt Pro Russland
ምስል Reuters

ዩክሬን ጠ/ሚንስትር አርሰኒ ያዜንዩክ፤ ሩሲያ 3ኛ የዓለም ጦርነት መጀመር ትፈልጋለች ሲሉ መንቀፋቸው ተነግሯል። እንደርሳቸው አባበል የሞስኮ ወታደራዊ ቁርቁስ ፍለጋ በአውሮፓ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል። በዩክሬን የሰፈነው ውጥረት ተባብሶ ወደ ግጭት ተሸጋግሯል ። የዩክሬን ወታደሮች ምሥራቅ ዩክሬን ከሚገኙት መፍቅሬ ሩስያ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው ቢያንስ ሁለት ሚሊሽያዎችን መግደላቸውን መንግሥት አስታውቀዋል ። ስሎቭያንስክ በተባለችው ከተማ በሚገኝ ኬላ መንግስት ባካሄደው በዚሁ ዘመቻ የቆሰለም አለ ። ሞስኮ ክየቭ የወሰደችው እርምጃ መዘዞችን ማስከተሉ እንደማይቀር አስጠንቅቃለች ። ትናንት ስሎቭያንስክ በተባለችው ከተማ የተካሄደው ውጊያ የዩክሬን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ኦሌክሳንድር ቱርቺኖቭ ስልጣን ከያዙ ወዲህ በዩክሬን የተካሄደ የመጀመሪያው ውጊያ ነው ። ከትናንት በስቲያ ነበር ፕሬዝዳንቱ ከሩስያ መቀላቀል የሚፈልጉ የዩክሬን መንግሥት ተቃዋሚዎች በሚገኙበት በምሥራቅ ዩክሬን ወታደራዊ ዘመቻው እንዲቀጥል ትዕዛዝ ያስተላለፉት ። ምሥራቅ ዩክሬን ውስጥ ቢያንስ 10 በሚሆኑ ከተሞች ጭንብል ያጠለቁ ታጣቂዎች የመንግሥት ህንፃዎችን ይዘው መንገዶችንም ዘግተው ቆይተዋል ። ከዚህ የዪክሬን ትዕዛዝ በኋላ ሩስያ በዩክሬን ጥቅሞቿን የሚነካ ማናቸውንም የመንግሥት እንቅስቃሴ እንዲሁ እንደማታልፍ አስጠንቅቃ ነበር ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሰርጌይ ላቭሮቭ የሩስያ እርምጃ በዓለም ዓቀፍ ህግ መሰረት የሚካሄድ እንደሚሆንም ነበር ትናንት ያሳወቁት።

« ከተጠቃን ያለ አንዳች ማወላወል የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን ። ጥቅሞቻችን ህጋዊ ጥቅሞቻችን የሩስያውያን ጥቅሞች በቀጥታ ጥቃት ከተፈፀመባቸው ደቡብ ኦሴሽያ ውስጥ እንደሆነው በዓለም ዓቀፍ ህግ መሠረት እርምጃ ከመውሰድ ሌላ መንገድ አይታየኝም ።»

Ukraine Unruhen in Slowjansk 24. April
ምስል Reuters

ከትናንቱ የዩክሬን ጦር እርምጃ በኋላም ሞስኮ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰንዝራለች ። የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኬቭ መንግሥት የወሰደው ይህ እርምጃ ይህ ነው ብለው ያልጠቀሷቸውን መዘዞች ሊያስከትል እንደሚችል ዝተዋል ። ፑቲን የኬቭ መንግሥት ጦር በራሱ ህዝቦች ላይበግልፅ አስከፊ ወንጀል እየፈፀመ ነው ሲሉም ከሰዋል ። የዩክሬን መንግሥት እና ምዕራቡ ዓለም በምስራቅ ዩክሬን ከዩክሬን ተገንጥሎ ከሩስያ ጋር የመቀላቀል እንቅስቃሴ የሚያካሂዱትን ኃይሎች ሩስያ በቀጥታ ትደግፋለች ሲሉ ይከሳሉ ። ሩስያ በአሁኑ ጊዜ በዩክሬን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የምታካሂድበትን አመቺ ሁኔታ እየጠበቀች ነው ብለው የሚያስቡት ዩክሬንንም ሆነ የምዕራቡ ዓለም ስጋት አሁን ተባብሷል ። ሩስያ አሁን ከዩክሬን ጋር በሚያዋስናት የዩክሬን ምሥራቃዊ ድንበር ላይ 40 ሺህ ወታደሮችን አስፍራለች ። የሩስያን እርምጃ ዩናይትድ ስቴትስ ተቃውማለች ። ሩስያ ባለፈው ሳምንት ጄኔቫ ስዊትዘርላንድ ውስጥ በተደረሰበት ስምምነት ላይ በምሥራቅ ዩክሬን የሰፈነውን ውጥረት ለማርገብ የገባችውን ቃል አልጠበቀችም ሲሉ ጃፓንን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ወቅሰዋል ። በዚህ ከቀጠለችም እንደ ኦባማ ተጨማሪ መዘዞች ይከተላሉ የተጠናከሩ የማዕቀቦቹም እርምጃዎችም ይወሰዳሉ ። ሩስያ በምሥራቅ ዩክሬን ጥቅሞቿ ከተነኩ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኃላ እንደማትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የሰጡትን መግለጫ አሜሪካ አጣጥላለች የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጄን ፕሳኪ ዛቻውን መሰረተ ቢስ ሲሉ ውድቅ አድርገውታል ።

Ukraine Unruhen in Slowjansk 24. April
ምስል KIRILL KUDRYAVTSEV/AFP/Getty Images

« እንደሚመስለኝ በቃለ ምልልሱ የተናገሯቸው አብዛኛዎቹ ቅሬታዎች አስቂኝ ናቸው ። እንደ እውነቱ ከሆነ በዩክሬን ውስጥ የሚፈፀመውን መሰረት ያደረገም አይደለም ። የዩክሬን መንግሥት በአንዳንድ የዩክሬን ከተሞች በህገ ወጥ መንገድ ህንፃዎች በመያዛቸው የወሰደው ህጋዊ እርምጃ ነው ። »

ከስሎቭያንስክ በስተሰሜን በሚገኝ መንገድ ላይ ትናንት ወደ 10 የሚሆኑ የዩክሬን መንግሥት ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችም መታየታቸውን ሁለት ሄሊኮፕተሮችም አካባቢውን ከበው ይበሩ እንደነበረ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ።ነዋሪዎችም ከአካባቢው እእንዲወጡ ትዕዛዝ ደርሷቸዋል ።ሞስኮ ደግሞ ዩክሬንን በሚያዋስኑ ግዛቶቿ በሙሉ አዲስ ወታደራዊ ልምምድ መጀመሩን ዛሬ አስታውቃለች።የሩስያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ክየቭ ከ11ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎችን በምሥራቅ ዩክሬን አስፍራለች ። ከዚሁ ጋር 160 ታንኮችና ከ230 የሚበልጡ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችም አሰማርታለች ብለዋል ሚኒስትሩ ። የዩክሬን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ቱርቺኖቭ ደግሞ ሩስያ ወታደሮችዋን ከድንበርዋ አካባቢ እንዳታነሳ በዩክሬን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባም ጥሪ አስተላልፈዋል ። በተያያዘ ዜና በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ፤ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ፣ ዛሬ ከሜርክልና ከሌሎች ከታወቁ የአውሮፓ ፖለቲከኞች ጋር በስልክ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ