1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬን ቀውስና ያልሰመረው የጄኔቫው ስምምነት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 15 2006

በዩክሬን የተባባሰውን ቀውስ ያረግባል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የጄኔቫው ስምምነት እስካሁን ተግባራዊ መሆን አልቻለም ። ከስምምነቱ በኋላም የዩክሬን ውጥረት ተባብሶ ቀጠለ እንጂ አልቀነሰም ።

https://p.dw.com/p/1BmJd
Ukraine ukrainische Soldaten in Ostukraine
ምስል picture-alliance/AP Photo

ከዕለት ወደ እለት እየተባባሰ የሚሄደው የዩክሬን ቀውስ ምዕራባውያንን ማሳሰብ ማሰጨነቁን ቀጥሏል ።ከእስከዛሬው ጥረት ለችግሩ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ይበልጥ ተስፋ የተጣለበት ባለፈው ሳምንት ጄኔቫ ስዊትዘርላንድ ውስጥ የተደረሰበት ስምምነት ነበር ። ሆኖም የዩክሬን የሩስያ የአሜሪካን ና የአውሮፓ ህብረት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የደረሱበት ይኽው ስምምነት ግን እስካሁን ሲተገበር አልታየም ። ስምምነቱ ከተፈረመ ማግስት አንስቶ ሩስያና ዩክሬን አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን በመጣስ እየከሰሱ ነው ። ውጥረቱም ከመርገብ ይልቅ የመካረሩ አዝማሚያ ነው የሚታየው ። በተንታኞች አስተያየት ችግሩ ከዚህም ብሶ ይቀጥላል የሚል ስጋት አለ ።ሊና ፊክስ በጀርመን የውጭ ጉዳዮች ምክር ቤት የአውሮፓና የሩስያ ጉዳዮች አዋቂ ናቸው ። በርሳቸውም አስተያየት ቀውሱ ተባብሶ የመቀጠሉ እድል አለ ። የጄኔቫው ስምምነት አተረጓጎምና አፈፃጸምም ችግር ይታይበታል ።

«ችግሩ የመቀጠሉ እድል ግማሽ በግማሽ ነው ። ምንም እንኳን በጄኔቫው ስምምነት ላይ ሰዎች ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም ውጥረቱን የሚያረግብ የመጀመሪያው እርምጃ አልሆነም ። ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱን የሚተረጉሙት በተለያየ መንገድ ነው ። ማን የትኛዎቹን እርምጃዎች መቼ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት እንዲሁም እርምጃዎቻቸውን የመቆጣጠር ሃላፊነቱ የማን እንደሆነ የጋራ መግባባት የለም ። »

Liana Fix Expertin Deutsche Gesellschaft für Auswärtige Politik in Berlin
ሊና ፊክስምስል Peter Himsel

የጄኔቫው ስምምነት ምሥራቅ ዩክሬን ውስጥ በኃይል የመንግሥት ህንፃዎችን የያዙ ወገኖች ህንፃዎቹን ለቀው እንዲወጡ እንዲሁም ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ይጠይቃል ። ከነዚህ አንዱም ግን እነዚህ ኃይሎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች አልተተገበረም ። ይባስ ብሎ ስላቭያንስክን በመሳሰሉ ከተሞች የዩክሬን መንግሥት ተቃዋሚዎች በተያዙ ህንፃዎች ፊት ለፊት ከጥቃት መከላከያዎችን እያጠናከሩ ነው ። ከዩክሬን መገንጠል እንፈልጋለን የሚሉት ኃይሎች ደግሞ ትጥቃቸውን እንደማይፈቱ ነው የተናገሩት ። ትጥቅ የሚፈቱ ከሆነም ምዕራብ ዩክሬን የሚገኙት ቀኞቹ የዩክሬን ብሄረተኛ ቡድን አባላትም መሳሪያቸውን ማስረከብ አለባቸው ነው የሚሉት ።ሩስያ እንደምትለው ቀኞቹ ሩስያኛ ተናጋሪዎችን እያስፈራሩ ነው ። ኬቭና ምዕራባውያን ደግሞ ማስፈራሪያው በአብዛኛው በሩስያ የመንግሥት መገናና ብዙሃን የተፈበረከ ነው ሲሉ ያጣጥላሉ ። ከዚህ ሌላ ከዩክሬን መገንጠል የሚፈልጉ ታጣቂዎች በሚቆጣጠሩት ኬላ ከትናንት በስተያ በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ሶስት ሰዎች መገደላቸው ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል። ፊክስ በዩክሬን ተቀናቃኝ ኃይላት የሚወስዱት እነዚህን መሰል እርምጃዎች ቀውሱን በማባባስ ትልቅ ሚና አላቸው ይላሉ። ፊክስ እንደሚሉት ዩክሬን ውስጥ በይፋ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በይፋ የማይታወቁ ኃይላት ጥቂት አይደሉም ።

«በሃገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ዜጎች የተደረጁባቸው ቡድኖች አሉ ።እነዚህ ወገኖች የዩክሬን አሰላለፍ ይበልጡን ወደ ሩስያ እንዲሆን ነው የሚፈልጉት ። ሆኖም እነዚህ በክሪምያው ግጭት ወቅት ከነበሩት በቁጥር የሚያንሱ ናቸው ። ከዚህ ሌላ በምሥራቅ ዩክሬን የታጠቁ ኃይሎች አሉ ። እነዚህ ኃይሎች ራሳቸውን ነፃ የምሥራቅ ዩክሬን ሚሊሽያ ብለው ነው የሚጠሩት ። ግን ምናልባትን ከሩስያ ድጋፍ ያገኙ ይሆናል ። በክዬቭ ደግሞ የብሔረተኞች ቡድኖች አሉ ። የቀደመውና የተደላደለው የስቮቦዳ ፓርቲ ይገኛል ከአስተያየት መመዘኛዎች መረዳት እንደሚቻለው ግን በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየቀነሰ ሄዷል ። ሩስያ ይበልጥ የምታተኩርበት ቀኝ ፅንፈኛው ፕራቪ የተባለው ቡድንም አለ ። የዚህን ቡድን ተፅእኖ አሳንሶ ማየት አይገባም ።»

Bewaffnete Separatisten in Slowjansk
ምስል DW/R. Goncharenko

የተለያየ አቋም የሚያራምዱትን አነዚህን ወገኖች እንዲህ በቀላሉ ማስማማትም ሆነ ማቀራረብ መቻሉ ያጠራጥራል ። ሆኖም ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሩስያ የሚጠበቅባትን ድርሻ በአግባቡ መወጣትዋ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል እንደ ፊክስ ።ከዚህ ሌላ ቀውሱን በድርድር ለመፍታት መሞከሩ ሌላ አማራጭ ቢሆንም እንገንጠል ለሚሉት ኃይሎች እውቅና መስጠቱ ደግሞ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ።

« በመሰረቱ አዎ ሩስያ ከፈተኛ ተፅእኖ ታሳድራለች ። ሆኖም ሩስያ የሚጠበቅባትን ሚና ተረድታ እስካልተወጣች ድረስ የመገንጠል እንቅስቃሴ ስለ ጀመሩ ምሥራቅ ዩክሬን ስለሚገኙ ወገኖች ከሞስኮ ጋር የሚካሄድ ድርድር ፍሬ አልባ ነው የሚሆነው ። ክየቭ ውስጥ የቀድሞዋ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዩልያ ቲሞሼንኮ እንገንጠል የሚሉ ወገኖች ሊካፈሉ የሚችሉበት የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲካሄድ ሃሳብ አቅርበዋል ። ሆኖም ለነዚህ ኃይሎች እውቅና መስጠቱ በጣም አሳሳቢ ነው ። እነዚህ ኃይሎች እስከ ምን ድረስ የምሥራቅ ዩክሬናውያንን አመለካከት እንደሚወክሉ ግልፅ አይደለም ። ሰዎች ለመተንኮስ የሚፈልጉ ዘላቂና አረጋጊ መፍትሄ የማይፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ ።»

ለዩክሬኑ ቀውስ መባባስ ምዕራቡ ዓለም በዋነኛነት ተጠያቂ የሚያደርጋት ሩስያን ነው ። ምዓራቡ ዓለም ሩስያ በጄኔቫው ስምምነት መሠረት በእነዚህ ኃይሎች ላይ ጫና እንድታደርግ ይፈልጋል ።የጄኔቫው ስምምነት እንዲተገብር ለማድረግ እንገንጠል የሚሉት ኃይሎች በህገ ወጥ መንገድ የያዟቸውን ህንፃዎች እንዲሁም ኬላዎች እንዲለቁ ሩስያ በይፋ ጥሪ እንድታስተላልፍ ነው የሚጠይቀው ። ከዩክሬን መገንጠል የሚፈልጉት ሩስያን የሚደግፉት ኃይሎች ላለፉት 2 ሳምንታት በቁጥጥራቸው ስር ካደረጓቸው የመንግሥት ህንፃዎች ለቀው ካልወጡ ግን አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በሩስያ ላይ አዳዲስ የኤኮኖሚ ማዕቀቦች እንደሚጥሉ እያስጠነቀቁ ነው ።ተስፋ የተደረገበት የጄኔቫው ስምምነት ምንም ለውጥ ካላስገኘ ከአሁን በኋላ ምዕራቡ ዓለም የሚቀረው አማራጭ እንደዛተው ጠንካራ የማዕቀብ እርምጃ መሆኑ እንደማይቀር ፊክስም ጠቁመዋል ። ይሁንና ይህ እርምጃ ዝም ተብሎ የሚገባበት አይደለም ። ማዕቀቡ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት መረጋገጥ ያለበት ጉዳይ አለ ።

Krise in der Ostukraine
ምስል DW/A. Sawitzkiy

« አሁንም ቢሆን ሩስያ ላይ የኤኮኖሚ ማዕቀቦችን የመጣሉ አማራጭ አለ ። ሶሶተኛ ደረጃው ማዕቀብ ተግባራዊ የሚሆነው ግን ሩስያ በምሥራቅ ዩክሬን ወታደሮቿን ማስገባቷ ግልፅ ከሆነ ብቻ ነው ። እንደሚታወቀው እስካሁን ለዚህ ማስረጃ የለም ። ስለዚህ ምስራቅ ዩክሬን ውስጥ ማን ምን እየሰራ ነው የሚለውን ለማጣራት የትኛዎቹ እንቅስቃሴዎች የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ለማወቅ ተጨማሪ ታዛቢዎችን ወደ ምሥራቅ ዩክሬን መላኩ አስፈላጊ ነው ። ዋናው ጥያቄ ግን ከዩክሬን እንገንጠል የሚሉት ኃይሎች ድጋፍ የሚያገኙት ከየት ነው የሚለው ነው ። ሩስያ እገዛ ስለማድረግዋ እስካሁን ትክክለኛ ማስረጃ ይጎድላል ።»

የሚፈለገው መረጃ ባልተጨበጠበት በአሁኑ ጊዜ ሩስያ የተጠየቀችውን ካላደረገች በሚቀጥሉት ቀናት መዘዙ መቀበሏ እንደማይቀር ማስጠንቀቂያ ተስጥቷታል ።ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ህብረት ሞስኮ ባለፈው ወር ሩስያ ዩክሬንን ወደ ራስዋ ግዛት በማጠቃለልዋ ምክንያት በአንዳንድ ሩስያውያን ላይ የቪዛ እገዳ ጥለዋል እንዲሁም ሃብት ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስም አድርገዋል ። በሩስያ ላይ ሰፊ የኤኮኖሚ ጫና እንዳያርፍ ቀውሱም እንዳይባባስ ታስበው የተጣሉትን እነዚህን ውስን ማዕቀቦች ሩስያ ትርጉም የለሽ ስትል ቀልዳባቸዋለች ። በርካታ የአውሮፓ ሃገራት የሩስያ የኃይል አቅርቦት ጥገኛ በመሆናቸው የአውሮፓ ህብረት ጠንካራ የኤኮኖሚ ማዕቀብን ወደ ሚያጠቃልለው ሶስተኛው እርምጃ ቢሸጋገር ሩስያ የአፀፋ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማትል ሳይታለም የተፈታ ነው ። ይህም ሃገራቱ የተቆጠቡ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ማስገደዱ ግልፅ ነው ። የሩስያ የኃይል አቅርቦት ጥገኛ የሆኑት ጀርመንን የመሳሳሰሉት ሃገራት ወደ ኤኮኖሚ ማዕቀቡ መሸጋገሩን የፈሩት ይመስላል ። ፊክስ በሩስያ ላይ በሚጣለው ማዕቀብ የጀርመን እንቅስቃሴ የተመጠነ እንደነበር ይናገራሉ።

Krise in der Ostukraine
ምስል DW/A. Sawitzkiy

« ጀርመን እስካሁን በተመዘነ መንገድ ነው የተንቀሳቀሰችው ። ሆኖም በርሊን የመጨረሻውን መደራደሪያ በማንሳት በሩስያ ላይ የኤኮኖሚ ማዕቀብ ተግባራዊ በመሆኑ ላይ ማመንታትዋ ብልህነት መሆን አለመሆኑ የሚያጠያይቅ ነው ። አሁን የቀሩት አማራጮች ጥቂት ናቸው ። ለዚህም ነው ጀርመን የመጨረሻውን መደራደሪያ ይዛ እስካሁን የተቀመጠችው ።

ሩስያ የኃይል አቅርቦቷን በማገድ አውሮፓን ልትቀጣ የመቻሏን ኃይል የአውሮፓ ሃገራት እንዴት ሊቋቋሙት እንደሚችሉ ቢያንስ ለጊዜው ግልፅ አይደለም ። አሁን የታወቀ ነገር ቢኖር ዩክሬን ከአንድ ወር በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማካሄዷ ነው ።ፊክስ ይህ ቀጠሮ የተያዘለት ምርጫ ዩክሬንን ለማረጋጋት የሚጫወተው ሚና ይኖራል ይላሉ ።

«ግንቦት 17 2006 ዓም የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዩክሬንን ለማረጋጋት ወሳኝ ምርጫ ነው ።እስካሁን ድረስ የኬቭ መንግሥትህጋዊ አይደለም እየተባለ ይወቀሳል ። ሆኖም ህጋዊ ፕሬዝዳንት ስልጣን ከያዘ በሚካሄዱት ድርድሮች በአጋርነት እውቅና ሊሰጠው ይገባል ።አሁን ግን ጥያቄው ምሥራቅ ዩክሬን የሚገኙት እንገንጠል የሚሉት ወገኖች ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ ወይስ አይፈልጉም ወይም ደግሞ ምርጫው እንዲካሄድስ ይፈቅዳሉ ወይ ነው ። መፍቅሬ ሩስያዊ እጩ የማሸነፉ እድል ግን በጣም ከፍ ያለ አይደለም ። »

ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄደው ምርጫው ውጤት ምን ሊሆን እንደምችል አሁን ብዙም ያሳሰበው ያለ አይመስልም ፤ ዋናው ትኩረት ወቅታዊው የዩክሬን ቀውስ ላይ ነውና ። መፍትሄው የሰማይ ያህል የራቀ የሚመስለው የዩክሬን ቀውስ የመርገቡ ወይም የመባባሱ ምልክቶች ከጥቂት ቀናት በኋላ ይታዩ ይሆናል ።

የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አበቅቷል አድማጮች ለአውሮፓ ና ጀርመን ዝግጅት ጥቆማ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካላችሁ በSMS በEMAIL እንዲሁም በFACEBOOK ብትፅፉልን እናስተናግዳለን ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ