1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩኤስ አሜሪካና የኪዩባ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 9 2007

ዬኤስ አሜሪካና ኪዉባ ከሃምስ ዓመታት በላይ ያቋረጡትን ዲፕሎማስያዊ ግንኙነት ማሻሻል እንደሚፈልጉ ከገለፁ በኋላ የዓለም መንግሥታት ዉሳኔዉን በደስታ ተቀበሉት።

https://p.dw.com/p/1E70Z
Soweto Handschlag Castro Obama Beerdigung Mandela 10.12.2013
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና ፕሬዚዳንት ራዉል ካስትሮ በማንድላ ቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ ተገናኝተዉ ተጨባብጠዋልምስል picture alliance/epa/Kim Ludbrook


የዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከኪዉባዉ አቻቸዉ ከራዉል ካስትሮ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በቴሌቭዝን በሰጡት መግለጫ ከኪዉባ ጋር የነበረዉን አስቸጋሪ ግንኙነት ፈፅመዉ « አዲስ ምዕራፍ » መክፈት ይፈልጋሉ።
ዩኤስ አሜሪካና የኪዉባ ስምምነት ከ 50 ዓመታት በላይ የዘለቀዉን ፀብና ፍጥጫ የሚያስወግድ ነዉ። ሁለቱ ሃገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸዉን እንደገና መጀመራቸዉ እንደተሰማ ከቻይና እንከ ቺሌ የሚገኙ መንግሥታት ድጋፋቸዉን ሲገልጹ ሃቫና ደግሞ በጭፈራና በፊሽታ ደምቃ ነዉ ያመሸችዉ። ሁለቱ ሃገሮች ግንኙነታቸዉን በአዲስ መንገድ እንደሚቀጥሉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ትናንት ነበር ያስታወቁት። ኦባማ ለሃገራቸዉ ህዝብ ንግግር ከማሰማታቸዉ በፊት ከኪዩባዉ ፕሬዚዳንት ራዉል ካስትሮ ጋር ለረጅም ግዜ በስልክ ተነጋግረዉ ነበር። ኦባማ በትናንቱ መልዕክታቸዉ የሁለቱ ሃገሮች እስካሁኑ ግንኙነት ዘመን ያለፈበት ነዉ ብለዋል፤

« እስካሁን የነበረዉ ግንኙነት ያረጀ በመሆኑ እንፈፅመዋለን። ለአስርተ ዓመታት የቀጠልነዉ ይህ ዓይነቱ ግንኙነት ደግሞ ፍላጎታችንን አላሳደገልንም፤ በመሆኑም በዚያ ምትክ ግንኙነታችን እናሻሽላለን»

ዩኤስ አሜሪካ ኪዉባ መዲና ሃቫና ዉስጥ ኤንባሲ እንደምትከፍትና የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተለያዩ ዲፕሎማስያዊ ዉይይቶችን ኤንባሲ ዉስጥ እንደሚያካሂዱም ተመልክቶአል። በኪዉባ ላይ የተጣለዉ የንግድ እና የፊናንስ ማዕቀብ እንደሚነሳም ነዉ የተገለፀዉ። ከኪዩባ ጋር ግንኙነቱን በማሻሻል ላይ የሚገኘዉ የአዉሮጳዉ ሕብረት በበኩሉ የሁለቱ ሃገሮች ድንገተኛ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጅማሮን «ታሪካዊ» ሲል ድጋፉን ሰጥቶአል። ከሃያላን መንግሥታት መካከል ቻይና ፈጣንና ገንቢ መልስን በመስጠት የመጀመርያዋ ስትሆን፤ ይህን የሁለቱን ሃገሮች ግንኙነት የቻይና መንግሥት «ለዓለም ጠቃሚ» ብሎታል። የደቡብ አሜሪካ መንግስታትም የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመርን አድንቀዋል። የሮማዉ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በበኩላቸዉ ዉሳኔዉን አወድሰዋል ። ዩኤስ አሜሪካና ኪዩባ ለዲፕሎማሲ ግንኙነት የመጀመርያ ዉሳኔ ላይ እንዲደርሱ የቫቲካኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ቁልፍ ሚናን መጫወታቸዉ ነዉ የተነገረዉ። ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሁለቱ ሃገራት ላላቸዉ ልዩነት ሰብዓዊ መልስን እንዲያፈላልጉ ለአሜሪካኑ ፕሪዚዳንት ባራክ ኦባማና ለኪዩባዉ አቻቸዉ ለራዉል ካስትሮ ባለፉት ወራቶች ደብዳቤ ሲፅፉ እንደነበር ተዘግቦአል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ትናንት ለመጀመርያ ግዜ በሰጡት አስተያየት « የተደነቀ ሥራ » ማለታቸዉ ተጠቅሶአል። ይሁንና ይህ ከዓለም ሃገር መንግሥታት ከፍተኛ ዉዳሴን ያገኘ ዜና ተቃዉሞም ቢሆን አላጣዉም ከተቃዋሚዎቹ መካከል ደግሞ የአሜሪካዉ ሪፐብሊካኑ የፍሎሪዳ ሀገረ ገዥ ማርኮ ሩቢዎ ናቸዉ። እንደማርኮ ይህ ዩኤስ አሜሪካ ከኪዩባ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር የያዛችዉ መንገድ « የፖለቲካ ቀዉስ» ሲሉ ገልፀዉታል
«ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ባስተላለፉት ዉሳኔ ግዴለሽነታቸዉን ብቻ ሳይሆን ያሳዩት፤ ዓለም በምን ርምጃ ላይ እንዳለች ችላ ማለታቸዉንም ጭምርም ነዉ»
ፕሬዚዳንት ኦባማ በሰጡት ምክንያት ሃገራቸዉ ከቻይና እና ከቬትናም ጋርም ያላትን ዲፕሎማስያዊ ግንኙነት መገንባት ጀምራለች።
የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር « በዚህ ቀዉስ ባጠላበት ወቅት አንድ ሰናይ ዜና » ሲሉ የሁለቱ ሃገሮች የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሻት ዉሳኔን አሞግሰዋል። የተመድ ዋና ፀሃፊ ባንኮሙን እና የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ፊሪድሪካ ሞግሄሪኒ የሁለቱን ሃገራት ርምጃም አወድሰዋል።

አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

TV-Übertragung Rede Raul Castro Havanna, Kuba 17.12.2014
ፕሬዚዳንት ራዉል ካስትሮ በቴሌቭዥን ለሃገራቸዉ ሕዝብ መግለጫ ሲሰጡምስል Reuters/Enrique De La Osa
Rede Obama Kuba Politik 17.12.2014
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለሃገራቸዉ ሕዝብ መግለጫ ሲሰጡምስል Reuters/Doug Mills/Pool
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ