1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩኤስ አሜሪካ የአየር ጥቃት እና አማፂው ቡድን

እሑድ፣ ጳጉሜን 2 2006

ዩኤስ አሜሪካ ኢራቅ ሃዲታህ የተሰኘ ግድብ አካባቢ ራሱን እስላማዊ መንግሥት «IS» ብሎ በሚጠራዉ ቡድን ላይ የአየር ድብደባ ማካሄድዋን ገለፀች።በሌላ በኩል ሊባኖስ ዉስጥ IS በመባል የሚታወቀዉ አክራሪዉ እስላማዊ ቡድን አፍኖ የወሰደዉን ሊባኖሳዊ ወታደር አንገት መቀላቱን የሚያሳይ ቪዲዮ መሰራጨቱ ተዘገበ።

https://p.dw.com/p/1D8RG
Irak Kurden Peshmerga Checkpoint Khazer 14.8.
ምስል picture-alliance/Landov

ዩኤስ አሜሪካ ካለፈዉ ነሐሴ ወር ጀምሮ ከ 100 በላይ የአየር ድብደባን ኢራቅ ዉስጥ ማካሄድዋ ይታወቃል። የዩኤስ አሜሪካ ማዕከላዊ ወታደራዊ አዛዥ እንደገለጸዉ በኢራቅ መንግስት ጥያቄ በጋራ የተቀናጀ የአየር ድብደባ በኢራቅ በሚገኙ እስላማዊ አክራሪዎች ላይ ጥቃት ተካሂዷል።

Irak Kurdische Peschmerga-Soldaten im Kampf gegen IS
ምስል Reuters/A. Jadallah

የአየር ድብደባዉ የተካሄደዉ አክራሪ ቡድኑ ሃዲታ ግድብን እየተቆጣጠረ ያለዉ የኢራቅ የፀጥታ ኃይል ስራ እንዳያጨናግፍ በማሰብ ነዉ። ባለፈዉ ወር IS አክራሪ እስላማዊ ቡድን ግድቡን በእጃቸዉ ለማስገባት ዉግያ ቢያካሂዱም፤ የኢራቅ ወታደሮች አካባቢዉ ላይ ከሚገኙት የሱኒ ነዋሪዎች ድጋፍና ጥረት ማስመለስ መቻላቸዉ ይታወቃል። ስድስት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ያለበት የሃዲታ ግድብ ለኢራቅ ሁለተኛዉና ግዙፉ የኤሌክትሪክ እና የመጠጥ ዉኃ ማመንጫ ነዉ። እስላማዊ ቡድኑ ባለፈዉ ወር በሰሜናዊ ኢራቅ የሚገኘዉን የሞሱል ግድብ ተቆጣሮ እንደነበርና፤ በዩኤስ አሜሪካ የአየር ድብደባ ኃይል መልሶ በመንግሥት እጅ መግባቱ ይታወቃል። ዩኤስ አሜሪካ አካባቢዉ ላይ የሚገኙትን እስላማዊ አክራሪዎች ለማባረር የአየር ድብደባዋን እንደምትቀጥል ተገልፆአል።

በሌላ በኩል ሊባኖስ ዉስጥ IS በመባል የሚታወቀዉ አክራሪዉ እስላማዊ ቡድን አፍኖ የወሰደዉን ሊባኖሳዊ ወታደር አንገት መቀላቱን የሚያሳይ ቪዲዮ መሰራጨቱ ተዘገበ።

Irak Schiitische Badr Brigade Miliz im Kampf gegen IS
የ አይ ኤስ ተዋጊዎችምስል Reuters/A. Jadallah

ይህን ተከትሎ የሊባኖስ የጦር ኃይል ሁኔታዉን እንደሚጣራ ተመልክቷል። ጀሃዲስቶቹ ባለፈዉ ሳምንታት የዩኤስ አሜሪካዉን ጋዜጠኛ አንገት መቅላታቸዉ ከታወቀ በኋላ ይህ ወንጀል «የከፍተኛ ጥላቻና የፈሪ ድርጊት» ሲል የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት በአንድ ድምፅ ማዉገዙ ይታወቃል። ምክር ቤቱ ከዚህም ሌላ ይህ ቡድን መጥፋት ይኖርበታል ሲል ማስታወቁ ይታወሳል። ትናንት ቅዳሜ የሶርያ መንግሥት በሀገሪቱ የጀሃዲስቶች መሰልጠኛ ቦታንና ቅጣት የሚያስተላልፉበትን የፍርድ ቦታ በአየር መደብደቡን በሃገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ገልፀዋል። በዚሁ የአየር ድብደባ በርካታ ሲቢሎችም መሞታቸዉ ነዉ የተገለፀዉ። አክራሪ ቡድኑ በሶርያዉ ፕሬዚዳንት ባሽር አልአሳድ ላይ የጀመረዉ የተቃዉሞ ንቅናቄ እየተጠናከረ መምጣቱም ተመልክቶአል። በሶርያ ዉስጥ በሚንቀሳቀሰዉ የጀሃዲስቶች ቡድን ዉስጥ አንድ በበርሊን ነዋሪ የነበረ የራፕ ሙዚቃ አንቃኝ እንደተገኘ የጀርመን ህገ-መንግሥት መጠበቅያ ቢሮ አስታዉቋል። ከጀርመናዊ እናቱ እና ከጋናዊ አባቱ የተወለደውና «ዴሶ ዶግ » በሚል መጠርያ ይታወቅ የነበረው ሙዚቀኛ በአሁኑ ጊዜ «ጀርመኑ አቡ ታላ» በሚል መጠርያ እንደሚታወቅም ተያይዞ ተዘግቧል።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ