1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩሮ መቀነስ ጠቃሚ ወይስ ጎጂ ነው?

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2007

ለአውሮፓ ገበያተኞች የዩሮ መቀነስ አስደሳች ዜና ሆኖ ሳለ ፤ አውሮፓ ተቀምጠው ከሌላው የአለማችን ክፍል ለሚሸምቱ ደግሞ ሁኔታው አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። የዩሮ መቀነስ ጠቃሚ ወይስ ጎጂ ይሆን?

https://p.dw.com/p/1EFle
Symbolbild Börse Kurs Dax Euro Griechenland 2014
ምስል picture alliance/Boris Roessler

የአብዛኞቹ የአውሮፓ ሃገራት መገበያያ የሆነው ዩሮ፤ ለረዥም አመታት ጠንካራ ገንዘብ ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና ቀስ በቀስ ገንዘቡ ከዩኤስ ዶላር ጋር እየተቀራረበ መምጣት ጀምሯል። ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ለምሳሌ የአንድ ዩሮ ዋጋ በዶላር 1, 39 የነበረ ሲሆን አሁን ወርዶ 1,19 ዶላር ገብቷል። ዩሮ በተለይ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ክፉኛ ዋጋ እያጣ መጥቷል። የአንድ ዩሮ ዋጋ ለመጨረሻ ጊዜ እንደዚህ አናሳ የነበረው ከዘጠኝ አመታት በፊት ነበር። የዩሮ ዋጋ መቀነስ ግን ብዙም አስገራሚ አይደለም። የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ሁኔታ እየተሻሻለ ሲሄድ የአውሮፓ የኢኮኖሚ እድገት ባለበት ይገኛል። እየሆነ ያለው በርካታ ምሁራን የተነበዩት ነው ይላሉ ፣ በጀርመን የዶይቸ ባንክ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ሽቴፈን ሽናይደር፤« በመካከለኛው የጊዜ ገደብ፤ ማለትም በሚቀጥሉት አመታት ባልደረቦቼ እንደውም ምንዛሪው ፤ እኩል እየሆነ ይሄዳል ብለው ያምናሉ።»

ይህ እውን ከሆነ አንድ ዩሮ ፤ በአንድ ዶላር ይቀየራል ማለት ነው። መስጋት ግን አስፈላጊ አይደለም ይላሉ ሽናይደር። እንደውም ምሁሩ ተስፋ ነው የሚታያቸው። የዩሮ መቀነስ ከአውሮፓ መገብየት ለሚፈልጉ ሰፊ እድል ይከፍታል። እንደ ጀርመን ያለች ለውጭ ገበያ አቅራቢ ሀገር ደግሞ ከዚህ ትርፋማ ልትሆን ትችላለች ይላሉ። በዚህም የተነሳ የአውሮፓ ኩባንያዎች ገንዘቧ እየቀነሰ ከመጣው ጃፓን ጋር ወደፊት መፎካከር ይችላሉ።

Krise Griechenland Symbolbild Euro Austritt
ምስል picture-alliance/dpa/Panagiotou

ጠንካራ ዩሮ የግድ ወሳኝ እንዳልሆነ የአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ፕሬዚዳንት ማሪዮ ግራዲም ባለፈው ሳምንት በጀርመንኛ ቋንቋ ለሚታተመው «ሀንድልስ ብላት» ጋዜጣ አመላክተዋል። እንደ እሳቸው ወሳኙ ነገር የዋጋ ማረጋጋት እና የኢኮኖሚው እድገት ነው። ይህንንም ለማረጋገጥ በርካታ ምሁራን የአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክ የሀገር እዳዎችን በብዛት ይገዛ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።

ሰሞኑን አነጋጋሪው ነገር በግሪክ ያለዉ የኤኮኖሚ ሁኔታ ነው። በእዳ ተዘፍቃ የቆየችው ግሪክ ቁጠባዋን ታቆም ይሆናል ብሎም ከዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚ አባል ሃገራት ትሰናበት ይሆናል የሚል ስጋት አለ። በግሪክ የሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ሊጠናቀቅ ሶስት ሳምንታት ቀርተውት ሳለ የግራ ፖለቲካ አራማጁ ፓርቲ በሀገሪቱ በተደረገ መጠይቅ የቀደምትነቱን ስፍራ ይዟል። ፓርቲው ካሸነፈ ፤ ሀገሪቱ ብድር ያገኘችበትን የቁጠባ ለውጦች ለመቀየር እና ብድር እንዲሰረዝላት ለመጠየቅ ይፈልጋል። ይህ ከሆነ ግሪክ ከሸርፉ አባልነት መውጣት አይቀርላትም የሚል ግምትም ከጀርመን መንግሥት በኩል እየተሰማ ነዉ ።

ከዩሮ የምንዛሬ ዋጋ የሚጎዱት ከአውሮፓ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚጓዙት አገር ጎብኚዎች ብቻ አይደሉም ፤ ወደፊት ከውጭ በዶላር ተገዝተው ወደ አውሮፓ የሚገቡ እቃዎች በሙሉ ውድ ሊሆኑ ይችላሉ። በዛ ላይ በዶላር የሚገዛው ነዳጅ ዘይት በአውሮፓ ነዳጅ ማደያዎች ዋጋ ሊጨምር ይችላል ይላሉ የፋይናንስ ገበያ ምሁር የሆኑት ክርስቶፍ ዝዌርማን። ዩሮ ከዚህ የበለጠ ሊወድቅ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።« ዩሮ ከሚፈለገው በላይ በአንድ ጊዜ ሲወድቅ እናይ ይሆናል። ከዛም ምናልባት በአንድ ጊዜ የአውሮፓ የዩሮ ቀውስ ሊነሳ ይችላል። »

Symbolbild EZB Europäische Zentralbank Frankfurt am Main
ምስል Getty Images

ለዚህም ምክንያታቸው ቀላል ነው። በዩሮ ወይም በአውሮፓ ላይ የህዝብ ዕምነት ማጣት ። እንደሳቸው የአውሮፓ ግዙፍ ኩባንያዎች የዩሮ ምንዛሬ 1,40 ዶላር ሆኖም በዓለም ገበያ ላይ ለመፎካከር አቅም አላቸው። ስለሆነም፤«የአውሮፓን የንግድ ሁኔታ ለማቃናት፤ ዋጋው የቀነሰ ዩሮ አያስፈልገንም።»ይላሉ፤ የፋይናንስ ገበያው ምሁር ክርስቶፍ ዝዌርማን።

ሂልከ ፊሸር / ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ