1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ጦርነት፤ የኢትዮጵያዉያን ፍዳ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2007

በስደተኛ አቅሟ ያጠራቀመችዉን ጥሪት ለቦምብ ሚሳዬል አረር ገብራ ከአደን ዳግም ለተሰደደችዉ ኢትዮጵያዊት ጦርነቱ ከፋ፤ «የሚጠጣ ዉሐ ጠፋ፤ ወይም ተመረዘ»-ከሚለዉ ወሬ ያለፈ የጦርነቱ ሰበብ ምክንያት፤ የመርዙ ደረጃ፤ የመርዙ ምንነት፤ የመራዡ ማንነትም ግልፅ አይደለም።

https://p.dw.com/p/1FJyZ
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Jamali,

ኢትዮጵያዉን ስደተኞች ደቡብ አፍሪቃ ላይ እሳት ተለቀቀባቸዉ።ነደዱ-ሞቱ።ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ ሰምጠዉ አለቁ።ሊቢያ ላይ ታረዱ።እስራኤል ዉስጥ ዜጋም ሆነዉ ይዋረዱ-ይገለሉ-አሁን ደግሞ ይደበደባሉ።የመን ዉስጥ በባዘነ-ጥይት-ሚሳዬል ተገደሉ።

የተረፉት በምግብ፤ ዉሐ፤ መጠለያ እጦት እየተሰቃዩ እንበለ ተስፋ ቀን-ያሳላሉ።

ትናንት ከዱባይ የደረሰን ዜና እንደሚያመለክተዉ ሑቲ የሚባለዉን የየመን አማፂ ቡድንን ለማጥፋት የመንን በጦር አዉሮፕላን የሚደበድቡት የሱኒ አረብ መንግሥታት ክላስተር በተሰኘዉ ተቀጣጣይ ቦምብ ደሐይቱን አረባዊት ሀገር እያነፈሯት ነዉ።ተቀጣጣዩ ቦምብ ለጦርነት እንዳይዉል በ2008 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በተፈረመዉ ዓለም አቀፍ ሥምምነት መሠረት ታግዷል።

Human Rights Watch Streubomben Jemen
ምስል HRW/Privat

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሁዩማን ራይትስ ወች ትናት እንዳስታወቀዉ ግን ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአረብ ሃገራት ጦር የመንን በዚያ መርዛማ ተቀጣጣይ ተስፈንጣሪ ቦምብ እየደበደበ ነዉi።በድርጅቱ ዘገባ መሠረት የመንን ለሚደበድቡት መንግሥታት አደገኛዉን ቦምብ ያስታጠቀችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።

ተቀጣጣዩ ቦምብ ለዉጊያ እንዳይዉል የሚያግደዉን ዓለም አቀፍ ሥምምነት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራትም፤ዩናይትድ ስቴትስም አልፈረሙም።ይሁንና የሁዩማን ራይትስ ዋች የጦር መሳሪያ ጉዳይ አጥኚ ስቲቫን ጉስ እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ ቦምቡን ለሌለ ሐገር እንዳትሸጥ የሚያግድ ሕግ አላት።አሜሪካ አለም አቀፉን አይደለም የራስዋንም ሕግ አላከበረችም።

«ዩናይትድ ስቴትስ እነዚሕ ቦምቦች ለሌላ ሐገር እንዳይሸጡ የሚያግድ ሕግ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ አላት።ይሕ ቦምቡ በተለይ በጣም የረቀቁት የቦምቡ ዓይነቶች አደገኛ መሆናቸዉን (አሜሪካኖች) እንደሚያዉቁ የሚያረጋግጥ ነዉ።ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ ለሳዲ አረቢያ እና የመንን የሚደበድበዉ ትብብር አባል ለሆነችዉ ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችም ቦምቡን ሸጣለች።የመን ላይ ቦምቡን የጣለዉ ከሁለቱ የየትኛዉ ሐገር ጦር እንደሆነ ግን እርግጠኛ አይደለንም።»

የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስቴር ባለሥልጣናት ቦምቡ ለጦርነት የሚዉለዉ በጣም በተወሰኑ እና ጥብቅ ጥንቃቄ በሚደረግበት አካባቢ እና ሁኔታ ብቻ ነዉ ይላሉ።ያን-ቦምብ የመንን ለሚደድቡት መንግሥታት መሸጣዉን ወይም ደብዳቢዎቹ ቦምቡን የመን ላይ መጣላቸዉን ግን የዋሽግተን ባለሥልጣናት አልካዱም።

Jemen Luftangriff auf Sanaa
ምስል Reuters/K. Abdullah

የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣንት ግን የመንን በክላስተር ቦምብ አልደበደብንም ባዮች ናቸዉ።የሑይማን ራይትስ ወች አጥኚ እንደሚሉት ግን የሪያዶች ማስተባበያ የተለመደ ቅጥፈት ነዉ።የመንን በአደገኛዉ ቦምብ መደብደባቸዉም ለሰላማዊ ሰዎች ደሕንነት ደንታ ቢስ መሆናቸዉን ጠቋሚ ነዉ።

«ሳዑዲ አረቢያ እነዚሕን መሳሪያዎች የሚያግደዉን ስምምነት ካልፈረሙት ሐገራት እንዷ ናት።ብዙ ሐገራት ስምምነቱን ፈርመዋል።ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች ብዙዎቹ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራት ግን አልፈረሙም።የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት በዚሕ ዘመቻ ቦምቡን አልጣልንም ማለታቸዉ ብዙ አያስገርምም።ቦምቡን መጣላቸዉ፤ በአጠቃላይ ዘመቻቸዉ ለሠላማዊ ሰዎች ደሕንነት ደንታ እንደሌላቸዉ ተጨማሪ ማረጋገጪያ ነዉ።»

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍሯንሷ ኦላንድ ደግሞ በነዳጅ ዘይት ለበለፀጉት ሐገራት ተጨማሪ ጦር መሳሪያ ለመሸጥ ትናት ዶሐ-ቀጥርን-ዛሬ ደግሞ ሪያድ-ሳዑዲ አረቢያን ጎብኝተዋል። ፈረንሳይ ለትንሺቱ አረባዊት ደሴት ለቀጠር ራፋሌ የተሰኘዉን ምርጥ የጦር አዉሮፕላን ለመሸጥ ተስማምታለች።

ኦሎንድ በሚገኙበት ድግስ በሚፈረመዉ ዉል መሠረት ቀጠር በሰባት ቢሊዮን ዶላር 24 ተዋጊ ጄቶችን ከፈረንሳይ ትገዛለች።ሰባት ቢሊዮን ዶላር።ለየመን ልማት ቢዉል በአምስት ዓመት ዉስጥ የደኸዉን የመናዊ ኑሮ በ25 በመቶ ያሻሽለዉ ነበር።ያዉ ነበር ነዉ።

Deutschland Demonstration gegen den Krieg im Jemen
ምስል DW

ግብፅም የዩናይትድ ስቴትስ ጦር መሳሪያ አልበቃ ብሏት የፈረንሳይን ዘመናይ ጄቶች ለመግዛት ተስማምታለች።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም ከዩናይትድ ስቴትስ በታጠቀችዉ ላይ የፈረንሳይን ለመጨመር እየተደራደረች ነዉ።ፈረንጅ ጦር መሳሪያ ይሸጣል።አረብ በገዛዉ ጦር መሳሪያ አረብን ይፈጃል።የተሻለ ኑሮ፤ ፍለጋ የተሰደደና የሚሰደደዉ ኢትዮጵያዊም በማያዉቀዉ ጦርነት ያልቃል።ያልሞተዉ የሰነዓዉ ወኪላችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንደሚለዉ ችግርን ሸሽቶ-ለሞት በሚያሰጋ መከራ ይማቅቃል።

በስደተኛ አቅሟ ያጠራቀመችዉን ጥሪት ለቦምብ ሚሳዬል አረር ገብራ ከአደን ዳግም ለተሰደደችዉ ኢትዮጵያዊት ጦርነቱ ከፋ፤ «የሚጠጣ ዉሐ ጠፋ፤ ወይም ተመረዘ»-ከሚለዉ ወሬ ያለፈ የጦርነቱ ሰበብ ምክንያት፤ የመርዙ ደረጃ፤ የመርዙ ምንነት፤ የመራዡ ማንነትም ግልፅ አይደለም።እንደ ጦርነቱ ሁሉ በዉሐ እጦቱ ከመሰቃየት ባለፍ ግልፅ እንዲሆን የምታስብ የምትመራመርበት አቅም፤ጊዜ፤ ምክንያትም የላትም።

ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን መደብደብ እንደጀመረ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣንት የመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ወደ ሐገራቸዉ ለመመለስ ወይም በያሉበት ለመርዳት መዘጋጀታቸዉን አስታዉቀዉ ነበር።እስካሁንም በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ወደ ሐገራቸዉ መመለሳቸዉን የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።እዚያዉ ሰነዓ የሚኖረዉ ግሩም እንደሚለዉ ግን ያየና የሰማዉ ተቃራኒዉን ነዉ ።

Jemen Luftangriff auf Sanaa
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Mohammed

የመኖች ግን ኢትዮጵያ ለመግባት ብዙ «አልተቸገሩም» ባይ ነዉ ግሩም።እሳቸዉ መንቀሳቀስ ካልቻሉት አንዷ ናቸዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን መደብደብ ከጀመረበት ካለፈዉ መጋቢት ጀምሮ ከአንድ ሺሕ ሰወስት መቶ በላይ ሠላማዊ ሰዉ ተገድሏል።በአስር ሺሕ የሚቆጠር ቆስሏል።ወደ አራት መቶ ሺሕ የተገመተ ሕዝብ አንድም ተሰዷል አለያም ተፈናቅሏል።ጦርነቱ ሰሞኑን ያየለዉ ደቡብ የመን ዉስጥ ነዉ።

የተፋላሚዎች የሐይል አሰላለፍ እንደ ጦርነቱ ሰበብ ምክንያት ሁሉ ግራ አጋቢ ነዉ።የቀድሞዉ ፕሬዝዳንት የዓሊ አብደላ ሳላሕ ታማኝ ጦር፤ ሐገራቸዉን ጥለዉ ከተሰደዱት ከፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ ደጋፊዎች ጋር ይዋጋል።ዓሊ አብደላ ሳላሕ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ዘመን ሐዲ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ።

በዓሊ አብደላ ሳላሕ ታማኞች የሚደገፈዉ የሁቲ ሚሊሺያ ባንድ በኩል ከአብድረቦ መንሱር ሐዲ ታማኞች ጋር በሌላ በኩል ከአልቃቂዳ ጋር ይዋጋል።ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር፤ የአልቃኢዳ ታጣቂዎችና የአብድረቦ መንሱር ታማኞች ከምድር የሚወጓቸዉን የዓሊ አብደላ ሳላሕ ታማኞችንና የሁቲ ሚሊሺያዎችን ከአየር ይደበድባል።

እስካሁን አሸናፊም ተሸናፊም የለም።ዛሬ ከአደን እንደተሰማዉ ደግሞ የሳዑዲ አረቢያ እግረኛ ወታደሮች አደን እየገቡ ነዉ።የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት እግረኛ ጦር ማዝመታቸዉን አላመኑም።የስደተኛዉ የየመን መንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ግን ቁጥሩ አነስተኛ ይሁን እንጂ የሳዑዲ አረቢያ እግረኛ ጦር አደን መግባቱ እርግጥ ነዉ።

ጋዜጠኛ ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንደሚለዉ የሳዑዲ አረቢያና የተባባሪዎችዋ መንግሥታት እግረኛ ጦር ዛሬ አደን መግባቱ ሐሰት፤እዉነትም ሊሆን፤ ላይሆንም ይችላል።የመንን በአዉሮፕላን የሚደበድቡት መንግሥታት የእግረኛ ጦር ዉጊያ መግጠማቸዉ ግን የማይቀር ነዉ።

Jemen Luftangriff auf dem Flughafen in Sanaa
ምስል Reuters/K. Abdullah

የስደተኛዉ የየመን መንግሥት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሪያድ ያሲን ባለፈዉ ሳምንት በሰጡት መግለጫ ግን እግረኛ ጦር ሥለመዝመት አለመዝመቱ የሰጡት ፍንጭ የለም።«ዘመቻ ወሳኙ ማዕበል» የተሰኘዉ የአዉሮፕላን ድብደባ ግን እይቆምም።

«ዘመቻ ወሳኙ ማዕበል አላቆመም።የዘመቻዉ መጠንንና የድብደባዉ ድግግሞሽ ግን ላጭር ጊዜ ቀንሷል።የእስካሁን የአየር ጥቃት (የሁቲዎችን) ወታደራዊ እንቅስቃሴ ገድቦታል።ከሁቲዎች ወይም ከሳላሕ ታማኞች የሆነ እንቅስቃሴ ከታየ ግን ድብደባዉ ከወትሮዉ ተጠናክሮ ይቀጥላል።»

አዲሱ የሳዑዲ አረቢያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አድል አል ጀባር ዛሬ እንዳሉት ግን በጦርነቱ ለተጎዱ የመናዉያን እርዳታ እስኪቀርብ ድረስ ጦራቸዉ የሚመራዉ የአዉሮፕላን ድብደባ ላጭር ጊዜ ይቆማል።አዉነት የትሆን የሆን-ሪያዶች ጋ፤ ወይስ ሪያድ ተሸሽገዉ የመንን እንመራለን የሚሉት? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ