1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የምግብ ዋስትና መታሰቢያና «ድብቅ ረሃብ»

ረቡዕ፣ ጥቅምት 5 2007

በዓለም ዙሪያ ፣ የዓለም የምግብ ዋስትና ዕለት ታስቦ ይውላል። በኢትዮጵያም በዋዜማው ይታሰባል። ጥቅምት 6 ወይም (Oct 16) የሚታሰበው ፤ በመጪው 2015 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 70 ዓመት የሚደፍነውን ፣ የተባበሩት መንግሥታትን የምግብና የግብርና ድርጅት ምሥረታ መንስዔ በማድረግ ነው።

https://p.dw.com/p/1DVzf
Südafrika Landwirtschaft in Mtunzini
ምስል DW/Subry Govender

ዕለቱን፣ የሆነው ሆኖ ፣ ለምግብ ዋስትና የቆሙ ፣ የዓለም የምግብ መርኀ ግብር ፣ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ተቋምና ፣ ሌሎችም ለምሳሌም ያህል የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የረሃብ መከላከያ፤ የእርዳታ ድርጅት (ቬልትሁንገርሂልፈ)ን የመሳሰሉ ሁሉ በጥሞና ያስቡታል። የዘንድሮው መታሰቢያ በዓል ልዩ ትኩረት የሰጠው አነስተኛ የመሬት ይዞታ ላላቸው አርሶ-አደሮች ነው። በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት ፣ የኢትዮጵያ መርኀ ግብር ተጠሪ አቶ ሐሰን ዓሊ--

Reissäcke FLASH-GALRRIE
ምስል MISEREOR/Achim Pohl

ብዙ አዳጊ አገሮች፣ ከምግብ ዋስትና ጋር በተያያዘ 3 አስጨናቂ ሸክሞች በጫንቃቸው ላይ ማረፋቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወሳል። ፈተናዎቹም ሆኑ ሸክሞቹ፤ ፤ በቂ ምግብ አለማግኘት ወይም ረሃብ፤ የአልሚ ምግቦችና ቪታሚኖች እጥረት፣ እንዲሁም ለጤና ጠንቀኛ የሆነ ውፍረት ናቸው። ፈተናዎቹ ላቅ ያለ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚከሠቱበት ሁኔታም አለ። ለምሳሌ ያህል ከመጠን ባለፈ የሚወፍር ልጅም በሥውር ረሃብ የሚጠቃ ሊሆን ይችላል። ከትናንት በስቲያ የወጣው ዘገባ ፣ በዓለም ዙሪያ የረሃብተኞች ቁጥር በ 37 ሚሊዮን ገደማ ዝቅ ብሏል የሚል ነው። ይሁንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የየሃገራቱን ረሃብተኞች መጠን በሠንጠረዥ የሚያስረዳው በእንግሊዝኛ Global Hunger Index የጀርመኑ «ቬልትሁንገርሂልፈ» እና በዋሽንግተን የሚገኘው ዓለም አቀፉ የምግብ አያያዝ የምርምር ተቋም፤ 805 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ በምግብ እጦት የተጠቃ ሲሆን ከ 2 ቢሊዮን በላይ ህዝብም በቪታሚንና ማዕድናት ከፍተኛ እጥረት የተጎሣቆለ ነው ይላሉ። እንደ ጋና ታይላንድና ቪየትናም የመሳሰሉ ሃገራት ረሃብን በመታገል ተደናቂነትን ሲያተርፉ፤ ውዝግብ ባልተለያቸው ሃገራት በተለይ ለምሳሌ ያህል በመካከለኛው ምሥራቅና ፤ የኢቦላ ተኅዋሲ ሰለባዎች በሆኑኅ 3 የምዕራብ አፍሪቃ አገሮች ሁኔታው ፍጹም አሉ ታዊ ነው። ለምሳሌ ያህል ጋዛ!

በጋዛ ወሽመጣዊ ግዛት የሚላስ የሚቀመስ አልታጣም። የአገር ውስጥ ገበያ ፍራፍሬና ቅጠላቅጠል ይቀርባል። ይሁንና ብዙዎቹ ፍልስጤማውያን የሚመገቡት ዳቦ ነው። በጦርነት በእሥራኤል ድብደባ በወደመው ጋዛ ሕዝቡ ሌላ ምግብም ሆነ ለጤንነት ተስማሚ የሆነ አማራጭ የምግብ ዓይነት ለመግዛት ብዙዎቹ የገንዘብ አቅም የላቸውም። በይበልጥ የሚጎዱት ደግሞ ልጆችና ሕጻናት ናቸው። የልጆች ሃኪም ዶክተር አድናን ኧል ዋኼይዲ---

«በዛ ያለ ፤ በርካሽ ዋጋ የሚገኝ ምግብ መመገብ ፤ አለመታደል ነው፣ ጊዜያዊ ኃይል ሰጪ ቢሆንም አልሚነት የለውም። በተመጣጣኝ ምግብ እጦት መጎዳትን የሚያስከትለውም ይኸው ነው። ይም ሆነ ይህ ለሁሉም ሰበብ የሆነው ዋናው ጠንቅ ድህነት ነው።»

BdT Pakistan Welternährungstag Mädchen auf dem Markt in Lahore
ምስል AP

የተባበሩት መንግሥታት ፣ የዓለም የምግብ ድርጅት፣ ጋዛ ውስጥ ድህነት ላጠቃቸው ወይም እጅግ ለተጎሳቆሉ ወገኖች ፤ 90 በሚሆኑ የገበያ አዳራሾች ምግብ መግዛት የሚችሉበት ካርድ አድሏል። ይሁን እንጂ ፍርፍሬና ቅጠላ-ቅጠል አያገኙም። የጀርመኑ የዓለም የረሃብ መከላከያ ድርጅት (ቬልትሁንገርሂልፈ) እንደሚገምተው፣ በዓለም ዙሪያ ሢሶ የሚሆነው ሕዝብ ለጤና ተስማሚ ምግብ መግዛት የተሣነው ነው።የጀርመኑ ቬልትሁንገርሂልፈ ፕሬዚዳንት ፣ የቀድሞዋ የቦን ከተማ ከንቲባ ቤርብል ዲክማን --

«2 ቢሊዮን ሕዝብ ነው ለዚህ ጉዳት የተጋለጠው። ሆድ የሚሞላ ፣ ጊዜያዊ ኃይል ሰጪ ምግብ የሚመገቡት፣ ውሎ አድሮ በጤንነታቸው ላይ ሳንክ ያስከትልባቸዋል። ልጆች የተሟላ ጤናማ ዕድገት አይኖራቸውም ፤፣ ነፍሰ ጡሮች የሚወልዷቸው ልጆችም ደቃቆች ነው የሚሆኑት»።

በምግብ እጦትም ሆነ ተመጣጣኝ ምግብ ባለማግኘት በያመቱ ከሚሞቱት 3,1 ሚሊዮን ሕጻናት መካከል በግምት 1,1 ሚሊዮኑ በቪታሚኖችና አልሚ ምግቦች እጦት ነው ሕይወታቸው የሚያልፈው።በአዮዲን እጥረት ብቻ እንኳ፣ 18 ሚሊዮን ያህል ሕጻናት ናቸው፤ የአንጎል ጉዳት አጋጥሞአቸው የሚወለዱት። ዘገባው እንዳተተው፤ ይህ ሁኔታ በ ቡሩንዲና ኤርትራ በአስከፊ ሁኔታ መከሠቱንና ከሰሃራ ምድረ በዳ በስተደቡብ በሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ባጠቃላይ ችግሩ የሚያሳስብ ነው።

Welternährungstag 2011 Dossierbild 1
ምስል AP

ለዓለም ሕዝብ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ለማቅረብ፣ የተባበሩት መንግሥታት ፤ ባለፈው መስከረም 14,2007 በኒው ዮርክ በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ፤ የአየር ንብረትን ይዞታ ግምት ውስጥ የሚያስገባ ዓለም አቀፍ ጥምረት እንዲቋቋም ማብቃቱ አይዘነጋም። በጥምረቱ የሚገኙት ፣ መንግሥታት፤ የመንግሥታት ያልሆኑ ድርጅቶችና ታላላቅ ኩባንያዎች ናቸው። ይህ ጥምረት ፤ በሰፊው እህል እንዲመረት፤ ማርኩዝ አድርጎ የተነሣው ሳይንስንና ሥነ ቴክኒክን ነው። በመሆኑም ማሳን መንከባከብ፤ ደንን መጠበቅ፤ በየጊዜው በአንድ ማሳ ላይ የተለያዩ አዝርእትን መዝራት፤ ግብርናንና ከብት ርባታን ማቀናጀት፤ እንዲሁም የሚጠጣ ውሃ አጠባበቅ ናቸው።

FAO Welternährungstag in Äthiopien
ምስል UN Photo/Rick Bajornas

የአየር ጠባይንም ሆነ ንብረትን በጥናት ተመሥርቶ በመተንበዩ ረገድ ፣ የዩናይትድ ስቴትሱ የሕዋ ምርምር መ/ቤት (NASA) ጭምር በሳቴላይት እንደሚጠቁም ይታወቃል። ኢትዮጵያና ፤ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት( FAO)፣ በአየር ንብረት ይዞታ ላይ ስለሚያደርጉት ትኩረት፣ አሁንም አቶ ሐሰን ዓሊ---

ምግብን ዋስትና በተመለከተ የኢትዮጵያ አመዳደብም ሆነ ደረጃ ምን ይመስላል? ፓናማ ፤ ግብፅ ታይላንድ ፤ ጋና ሜክሲኮና ቪየትናም በምግብ ዋስትና ረገድ እመርታ ማሳየታቸውን የጀርመኑ ቬልትሁንገርሂልፈ ገልጿል ፤ ስለኢትዮጵያ ደረጃ በዚህ ረገድ የ ተ መ የምግብና ግብርና ድርጅት ምን ይላል?

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ