1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ምጣኔ ሀብት በ2015

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3 2007

በዓለማችን የተለያዩ ቦታዎች የእርስ በርስ ግጭት፣ ጦርነት፣ ያለመረጋጋት እና ወረርሽኝ ሰፍኗል። እንዲያም ሆኖ ግን ሊሰናበት ጥቂት ቀናት በቀሩት የጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓም ውስጥ የዓለም ምጣኔ ሀብት ሦስት በመቶ እንዳደገ ተነግሯል። የምጣኔ ሀብቱ ጭንቀት ይልቁንስ ወደ ዩሮ ዞን የንግድ ቃጣና መሸጋገሩ እንደማይቀር ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/1E2Gb
ምስል Fotolia/Fantasista

ዩሮ ዞን ደቃቃ እድገት እንደሚጠብቀው ከወዲሁ ተገምቷል። በጀርመን ግዙፉ የማዕከላዊ የጋራ ቁጠባ ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት ሽቴፋን ቢልማየር በአውሮጳ የሚጠበቀው የምጣኔ ሀብት እድገት አነስተኛ እንደሚሆን አልሸሸጉም።

«በዩሮ ዞን በሚቀጥለው ዓመት 0,8 በመቶ እድገት እንጠብቃለን።»

በእርግጥ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ በተከሰተባቸው ሃገራት ምጣኔ ሀብቱ ከነበረበት ድቀት ማገገም ጀምሯል። በአሁኑ ወቅት ግዙፉ የአውሮጳ ብሔራዊ ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ርብርቦሽ ከመንገዳገድ ተርፏል። RWI በተሰኘው የጥናት ተቋም ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሮላንድ ዶይርን በአንዳንድ የዩሮ ዞን ሃገራት ችግሩ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቀረፈ ጠቅሰዋል።

«የምጣኔ ሀብቱ ጠውላጋነት እየተባባሰ በሄደበት በጣሊያን ፍፁም አስቸጋሪ ነው። ለዚያ ደግሞ መዋቅራዊ ለውጡ ለዓመታት ከመጓተቱ ጋር በእጅጉ ይያያዛል። በፈንሣይ በእርግጥ ለረዥም ዓመት የነበሩትን ችግሮች መንግሥት በርካታ ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ሊቀርፍ ችሏል።»

ዋና ኢኮኖሚስት ሽቴፋን ቢልማየር
ዋና ኢኮኖሚስት ሽቴፋን ቢልማየርምስል Deutsche Zentral-Genossenschaftsbank

በአንዳንድ የዩሮ ዞን አባል ሃገራት ምጣኔ ሀብታዊ ሳንካ የተነሳ ጀርመን መሰቃየቷ አልቀረም ሲሉ ሮላንድ ዶይርን ተናግረዋል። በጀርመን ፌዴራል ባንክ ቅድመ-ግምት መሠረት የጀርመን ምጣኔ ሀብት በሚቀጥሉት ዓመታት ሊያድግ የሚችለው በአንድ በመቶ ብቻ ነው።

«በርካታ ኩባንያዎች ከእስያ በመውጣት ወደ አሜሪካ ያቀናሉ። እዚያም ምርታቸውን ዳግም ይጀምራሉ። ምክንያቱም በአሜሪካ ፉክክሩ እጅግ በጣም ቀላል ሆኖ ተቀይሯል።»

ቻይና ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ሳንካ ሲገጥማት ሕንድ ማደጓ ይቀጥላል ተብሏል። በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት ድርጅቶች 6,6 እድገት እንደሚያስመዘግቡ ተንታኞቹ ጠቁመዋል። ምጣኔ ሀብታቸው በከርሠ-ምድር ሀብት ላይ ጥገኛ የሆነ አንዳንድ የላቲን አሜሪካ ሃገራት የከርሠ-ምድር ሀብታቸው የገበያ ዋጋ ከፍ እና ዝቅ ባለ ቁጥር ተጽዕኖው እንደሚያርፍባቸው ተገልጿል።

ሩስያ በምዕራባውያን በተጣለባት ማዕቀብ የተነሳ እጎአ በ2015 የኢኮኖሚ እድገቷ ተግዳሮት እንደሚገጥመው ሽቴፋን ቢልማየር ጠቅሰዋል። የነዳጅ ድፍድፍን ጨምሮ የከርሠ ምድር ሀብት የገበያ ዋጋ መቀነስ እንደ ጀርመን ላሉ ሃገራት ምጣኔ ሀብት ያልታሰበ ሲሳይ ተደርጎ እንደሚቆጠርም የምጣኔ ሀብት ተንታኞቹ ተናግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ