1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤቦላ ተሕዋሲ ጉዳትና ሥጋት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2006

ለአፍሪቃ ሕብረት፤ ለአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ኮሚሽን ወዘተ እየተባለ በርካታ አፍሪቃዉን የሚመላለሱ፤ የሚስተናገዱባት ኢትዮጵያ እስካሁን የወሰደችዉ የጥንቃቄ እርማጃ ሥለመኖር-አለመኖሩ በይፋ የሰመነዉ የለም። ኬንያ ግን ወደ ሐገሯ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ጀምራለች።

https://p.dw.com/p/1CmW8
ምስል picture-alliance/dpa

ምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት የተዛመተዉ የኤቦላ ተሕዋሲ የገደለና የለከፋቸዉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነዉ።መድሐኒት ያልተገኘለት ተሕዋሲ ጊኒ ዉስጥ ሰዉ መልከፉ ከታወቀበት ካለፈዉ መጋቢት ጀምሮ ከሥድስት መቶ ሰባ የሚበልጡ የጊኒ፤ የላቤሪያ እና የሴራሊዮን ዜጎችን ገድሏል።የገዳዩን ተሕዋሲ ሥርጭት ለመከላከል የአካባቢዉ መንግሥታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነዉ።አንዳንድ አየር መንግዶች በተለይ ወደ ሠወስቱ ሐገራት የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጠዋል።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አጠናቅሯል።

አሳሳች፤ ፈጣን፤ ጨካኝ-ነዉ አይምሬ።ኤቦላ።እንደ ወባ ያተኩሳል፤ያልባል፤ ደሞ ብርድ ብርድ እያለ ሰደቻ ያስመታል።እንደ ሆድ ሕመም ያስቀምጣል፤ያቅለሸልሻል፤ ይለብቃል።ተለካፊዉ ወባ፤ድርቀት፤የምግብ መጣላት ነዉ-ብሎ በቅጠሉም-በሥሩም በኪኒኑም ሲያዘግም ጨካኙ ተሕዋሲ ከተለካፊዉ ሰዉ አፍ፤አፍንጫ፤ ጆሮ--ብቻ በሁሉም የሰዉነት ቀዳዳዎች ደም ያዣል።

የላይቤሪያዊዉ የገንዘብ ሚንስቴር ትልቅ ሹም ፓትሪክ ሳዉዬር ዓላማ ሌጎስ ደርሰዉ ከአካባቢዉ ሐገራት አቻዎቻቸዉ ጋር ሥለ ወጪ-ገቢ ንግድ ለመነጋገር ነበር።ከሞንሮቪያ ሎሜ ቶጎ እስኪደርሱ እንደ ሁል ጊዜዉ በሱፍ ከራባታቸዉ እንደዘነጡ፤ከባልደረቦቻቸዉ ጋር እንደተሳሳቁ ነበር። ከሎሜ-አዉሮፕላን ማረፊያ ስንነሳ» አሉ የሳዉዬር-ባልደረባ «ወበቀኝ አለኝ»።አዉሮፕላኑ ይበራል።ኤቦላም ግዳይ ሊጥል ይጣደፋል።

ከሎሜ-ሌጎስ የአንድ ሰዓት በረራ ነዉ።የላይቤሪያ ባለሥልጣንን ያሳፈረዉ አዉሮፕላን ሌጎስ እንዳረፈ የሌጎስ ሐኪሞች-ሰዉዬዉን አጣድፈዉ ሐኪም ቤት ዶሏቸዉ።ሐኪሞቹ ፈጥነዋል።ግን ኤቦላ ቀደማቸዉ።ላይቤሪያ ባለስልጣኗን ጨምሮ-ኤቦላ 136 ዜጎችዋን ከቀማባት በኋላ ከአጎራባቾቻ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር ዘጋች።

Arzt Sheik Umar Khan aus Sierra Leone an Ebola gestorben
ምስል Reuters

«ይሕና ሌሎች የላይቤሪያ መንግሥት የወሳዳቸዉ እርምጃዎች፤ የሐገሪቱ ሕዝብ ሥለ ገዳዩ የኤቦላ ተሕዋሲ ያለዉን ግንዛቤ ለማዳበርና ሥርጭቱን ለመቀነሥ ይረዳል ብለዉ ብዙዎች ያምናሉ።»

ይላል ላይቤሪያዊዉ ጋዜጠኛ ጁሊየስ ካኑባሕ።የላይቤሪያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ግጥሚያዎችን ሠርዟል።ሌጎስ ላይ የሞቱትን ላይቤሪያዊ ባለሥልጣን አሳፍሮ የነበረዉ የምዕራብ አፍሪቃ አየር መንገድ ASKY ---እና ወደ ላይቤሪያ፤ ሴራሊዮን፤ጊኒ የሚደረጉ በረራዎችን ሠርዟል።አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ነዉ የሚሠራዉ።

ለአፍሪቃ ሕብረት፤ ለአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ኮሚሽን ወዘተ እየተባለ በርካታ አፍሪቃዉን የሚመላለሱ፤ የሚስተናገዱባት ኢትዮጵያ እስካሁን የወሰደችዉ የጥንቃቄ እርማጃ ሥለመኖር-አለመኖሩ በይፋ የሰማነዉ የለም። ኬንያ ግን ወደ ሐገሯ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ጀምራለች።

የኬንያ የሕክምና ጥናት ተቋም ሐላፊ ዶክተር መሐመድ ከራማ እንደሚሉት ኤቦላ ከተዛመተባቸዉ ሐገራት ወደ ኬንያ የሚገቡ መንገደኞችን የጤና ይዞታ የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች በየመዳራሻ ኬላዎች ተሠማርተዋል።

«የኤቦላ በሽታን ለማወቅ ቀላሉ ምርመራ የሠዉነትን የሙቀት መጠን መላካት ነዉ።ይሕ ፈጣኑ ምርመራ ነዉ።ተመርማሪ ከተጠረጠረ አስፈላጊዉ እርምጃ ፈጥኖ ይወሠዳል።የአየርና ማረፊያና ወደቦቻችን ምርመራዉን ማድረግ የሚችሉ ባለሙያዎች አሏቸዉ።አነሱ አስፈላጊዉን ምርመራና ጥንቃቄ ያደርጋሉ።»

ያን ገዳይ ተሕዋሲ ከሼክ ኡመር ካሕን እኩል የሚያዉቀዉ፤የተጠነቀቀዉ ወይም ሊጠነቀቀዉ የሚገባ አፍሪቃዊ እስካሁን የለም።ሐኪም ነበሩ።ዶክተር።የሴራሊዮን የኤቦላ ተሕዋሲ ተለካፊዎች መታከሚያ ማዕከል ሐላፊ።በሽተኞችን ለማዳን ከኤቦላ ጋር ሲተናነቁ-አይምሬዉ ለከፈ-ገደላቸዉም።

ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ የኤቦላ በሽተኞችን ያክሙ የነበሩ አሜሪካዊ ዶክተርም በጠና ታመዋል።ከአሜሪካዊዉ ሐኪም ጋር ይሰሩ የበሩ ሌላ ካናዳዊ ሐኪም ለጥንቃቄ ተብሎ ካራንቲን ገብተዋል።

Ebola in Liberia
ምስል picture-alliance/dpa

እስካሁን በሽታዉ ሥድስት መቶ ሰባ ሁለት ሰዉ ገድሏል።የለከፈዉ አንድ ሁለት መቶ።ለፍርሐት ሥጋቱ ንረት ግን በርግጥ መለኪያ የለም።

« በእዉነቱ በጣም መጥፎ ስሜት ነዉ ያለኝ።አፈራለሁ።በጣም ነዉ ያሰጋኝ።ከሌጎስ ዉጪ ያሉ ወላጆቼም እየደወሉ ለኔ መስጋታቸዉን እየገለጡልኝ ነዉ።ከሁኔታዉ እንዴት መጠንቀቅ እንዳለብኝ ይመክሩኛል።»

ሰዉዬዉ ይቀጥሉ፤-«ከንባቤ እንደተረዳሁት በሽታዉ የለከፈዉ መዳኛ የለዉም።ሥርጭቱን ለመቆጣጠር የጤና ሚንስቴር አስፈላጊዉን ጥንቃቄ ያደርጋል ከሚል ተስፋ በስተቀር ሌላ ተስፋ የለኝም።አሳሳቢ ነዉ።»

ያሳስባል።በአካል ንክኪ በቀላሉ ይተላለፋል።ድሐኒት የለዉም።ኤቦላ።የዓለም ጤና ድርጅት «ተጠንቀቁ» ከማለት ባለፍ-አቅመ ቢስ ነዉ።

ነጋሽ መሀመድ

አርያም ተክሌ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ