1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢንተርኔት አጠቃቀምና አስተዳደር-(አመራር)

ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2006

ኢንተርኔት ፤ በአሁኑ ዘመን ችላ የማይባል የዕለታዊ ህይወት አንድ አካል ነው ከተባለ፣ አባባሉ ሢሦውን የዓለም ሕዝብ ብቻ ነው የሚመለከተው። አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባቀረበው መረጃ መሠረት የኢንተርኔት ተጠቃሚ

https://p.dw.com/p/1BaG9
ምስል AP

አይደለም። አብዛኛው የዓለም ሕዝብ፤ በዚህ ዘመናዊ የትምህርትና መረጃ አገልግሎት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማብቃት አስተዳደሩም መሻሻል ይኖርበታል በማለት ሲወተውቱ የቆዩ ባለሙያዎች ፣ ከመጋቢት 15-18,2006 ዓ ም ሲንጋፑር ውስጥ ባካሄዱት ዐቢይ ጉባዔ፤ የኢንተርኔት አስተዳደር በአንድ መንግሥትም ሆነ ድርጅት የበላይነት መሆኑ ቀርቶ ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታት ሁሉ፣ የጋራ ውክልና ባለው ማኅበርም ሆነ ድርጅት ሥር እንዲመራ መስማማታቸው ታውቋል። ይህ ሊሆን የቻለው 15 ዓመታት ያህል፤ አያሌ መንግሥታት ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚቴ፤ እንዲሁም ፣ የሲብሉ ማሕበረሰብ ተወካይ ቡድኖች ፣ ዩናይትድ ስቴትስን፤ የኢንተርኔቱን አስተዳደር የበላይ ተቆጣጣሪነት ትተው ዘንድ ሲወተውቱ መቆየታቸው የሚታበል አይደለም።

Portraät - ICANN Präsident Fadi Chehade
ምስል Getty Images

ዩናይትድ ስቴትስ የበላይ ኀላፊ ነኝ ማለቷን እርግፍ አድርጋ እንድትተው ከቀረቡላት ጥያቄዎች መካከል ፣ የኢንተርኔት መግቢያ ቁልፎች የሆኑት ምልክቶች---#Link, : https: , //www.icann.org/Internet Corporation for Assigned Names and Numbers(ICANN)#,የመሳሰሉትን በአስገዳጅነት እንዳታስቀምጥ ነው። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በዚህ ረገድ የኢንተርኔቱን ቁልፍ የሚቆጣጠረው የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ሚንስቴር እንደነበረ የሚታበል አይደለም። ያለ ዩናይትድ ስቴትሱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን (NTIA) በንግድ ሚንስቴር ሥር ነው፣ ያለሱ ፈቃድ በኢንተርኔት ተግባራትን ማከናዋን የማይታሰብ ነበር።

ይሁን እንጂ እ ጎ አ በ 2003 ጀኔቭ ከዚያም በ2ኛው ዓመት ቱኒስ ውስጥ በተካሄደው የዓለም የመረጃ ጉዳዮች ጉባዔ፤ የኢንተርኔት አስተዳደር ዓለም አቀፍ ውክልና ባለው ቡድን ጥላ -ከለላ ሥር ይውል ዘንድ ፤ጥያቄው ጎላ ብሎ መቅረቡ አይዘነጋም።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የሆነው ሆኖ፤ መጋቢት 6,2006 ዓ ም፤ የኢንተርኔት መክፈቻ ቁልፍ ስሞችንና በመረቡ የነበረውን የበላይ ኀላፊነት እንደሚሠርዝ ማስታወቁ የኢንተርኔት ተጠቃሚውን ዓለም እንዳስደመመ ነበረ የተገለጠው። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከፍተኛ የሚሰኙትን የኢንተርኔት ቁልፍ ስሞች፤፣ ለምሳሌ .com, .net , እና .org እንዲቆዩ አጽድቋል። በሌላም በኩል፤ .ir ኢራን , .ru, ሩሲያ፣ እንዲሁም .cn ቻይና ፤ ስለአነዚህ አገሮች በመሪ የኢንተርኔት ቁልፍ ስም መዝግቦ ማስቀመጡን አንዳንድ ሃገራትን በጣም ነው ያስቆጣው። የእስያ የሰላማዊው ውቅያኖስ አካባቢ የመረጃ መረብ ማዕከል (APNIC)ዋና ሥራ አስኪያጅ ፖል ዊልሰን እንዳሉት፤ ከፖለቲካ ተጨባጭ መነሻ፤ የሀገር የአህጽሮት ስም ፤ የዚያው የሚመለከተው ሀገር ነው ብለው አንዳንድ አገሮች አጥብቀው ያምናሉ። ይህን እንዲያውም ከብሔራዊ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ኩራት ጋር ነው አያይዘው የሚመለከቱት።

Die Herren des Internet
ምስል AP

የዩናይትድ መንግሥት፣ የኢንትርኔትን ቴክኒካዊ አሠራርም ሆነ አመራር፤ በዛ ያሉ ዓለምአቀፍ ውክልና ያላቸው ወገኖች፤ የመረጃ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች፤ የንግድ አካላት መንግሥታት የሲቭሉ ማኅበረሰብ ቡድኖችና የአካዳሚ ባለሙያዎች እንዲረከቡ ከወዲያናው ሰሞን ሲንጋፑር ውስጥ ለ 4 ቀናት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ተስማምታለች።በተሰጠው ኮንትራት መሠረት ፣ የውሉ ጊዜ እ ጎ አ በ መስከረም ወር 2015 ዓ ም ከማክተሙ በፊት ፤ አሁን ፣ መሪ የኢንተርኔት ቁልፍ ስሞችን በመቆጣጠር ላይ የሚገኘውበዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ለትርፍ እንደማይሠራ የተነገረለት ድርጅት «ኢንተርኔት ኮርፖሬሽን ፎር አሳይንድ ኔምስ ኤንድ ነምበርስ» ICANN ፤ እንደ ጉባዔው አዘጋጂዎች አገላለጽ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፤ በአንድ ድርጊት ፤ ማለት ፤ ቀድሞ የአገሪቱ ብሔራዊ የስለላ ድርጅት ሠራተኛ የነበረው ኤድወርድ ስነውደን ፤ ያገሩ መንግሥት በብዙ የስለላ ድርጊቶች ላይ ተጠምዶ እንደነበረ በማጋለጡ ፣ በዚህ ሳቢያ ብቻ ተገፋፍታ አይደለም።

የተጠቀሰው ድርጅት ኀላፊነት ሲያከትም፤ አዲስ ዓለም አቀፍ አመራር ይሆናል ከዚያ በኋላ ተግባሩን የሚያከናውን። የ ICANN ዋና ሥራ አስኪያጅ ፋዲ ቸኻድ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔ የኢንተርኔት አስተዳደር ከፖለቲካ ነጻ እንዲሆን የሚያበቃ ነው ይላሉ። ወደፊት የኢንተርኔት መረብን አመራር በተመለከተ በዚህ ወር ውስጥ በሳዖ ፓውሎ ብራዚል «Net Mundial» በሚል መሪ ቃል ሰፋ ያለ ጉባዔ ተዘጋጅቶ እንደሚመከርበትም ቸኻድ ጠቁመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ኮምፒዩተሮች በኢንተርኔት መረብ መረጃ ሁሉ እንዲተላለፍ የሚያደርጉበት የኢንተርኔት ፕሮቶኮል 4ኛው ምዕራፍ (IPv4) በመጣበቡ ፣ Ipv6 እንዲተካው በመደረግ ላይ ነው። Ipv4 እ ጎ አ ከ ሰኔ ወር 2004 ዓ ም አንስቶ ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ በኢንተርኔት ሰነዶችን መመዝገብ የሚችልበት ቦታ በ 4,3 ቢሊዮን የተወሰነ መሆኑ ነው የተመለከተው። IPv6 በአንጻሩ በትሪሊዮን የሚቆጠር የቁጥርና የአድራሻ ቦታ እንዳለው ተነግሮለታል።

ገደብ በማይኖረው IPv6 በኢንተርኔት መረብ ስፍር ቁጥር የሌለው ስም፣ ቁጥርና የመሳሰለውን ለማስተላለፍም ሆነ ለማሥፈር የተለመደው ተግባር ያለሳንክ እንደሚቀጥል ነው የሚነገረው። ይሁንና አሁንም በብዙ ሃገራት አነጋጋሪም ሆነ አሳሳቢ ሆኖ የታየው፤ የግለሰቦች የመረጃ ሰነድ አጠባበቅ ዋስትና ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ያህል በጀርመን ሀገር፤ ጉዳዩ በፌደራል ክፍላተ ሀገርና በፌደራሉ መንግሥት በጥሞና እየተመከረበት ያለ ጉዳይ ነው። የግለሰብ መብት፣ የግለሰቦች የግል ሰነድ ፤ ጀርመን ውስጥ ዐቢይ ትርጉም ነው የሚሰጠው። የኢንተርኔት አገልግሎት ገና ሳይጀመር ኮምፒዩተር ብቻ ብቅ ባለበት ዘመን ፤ እ ጎ አ በ 1970 ኛዎቹ መግቢያ ላይ፣ የግለሰቦች የመረጃ ሰነዶች አላግባብ ከማይፈለግ ወገን እጅ እንዳይገቡ የሚቆጣጠር ይፋ መ/ቤት ተቋቁሞ እንደነበረ ታውቋል።

በአሠሪና በሠራተኛ መካከል ፤ በሀኪምና በታካሚ ፤ በአከራይና ተከራይ፤ብሎም በአዲስ ፍቅረኞች መካከል የሚደረጉ፤ የጽሑፍ፤ የድምጽ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ምስል መልእክት፣ ይህና የመሳሰለው ከማይፈለግ ሰው እጅ መግባት ብቻ ሳይሆን ለንግድ የሚውልበት ሁኔታ ቢፈጠር የቱን ያህል ብርቱ የግለሰብ መብት መደፈር መሆኑን መገንዘብ አዳጋች አይደለም። በሌላ በኩል የተሳሳተ መረጃ የሚቀርብበት ሁኔታም ስላለ ፣ ባልሠሩት ሥራ ቅጣትም ሆነ የመሳሰለ ሁኔታ ስለሚያጋጥም አስቀድሞ መከለካያውን ማበጀት ይገባል ፤ ከሰሜን ጀርመን ኢምከ ዞመር የተባሉት ወይዘሮ እንደሚመክሩት።

«ብዙ ጊዜ ነው ስለሰዎች የተሳሳተ መረጃ ፤ በኢንተርኔት የመረጃ ሰነድ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው። በተጨማሪም ከመረጃው በመነሳት የተሳሳተ አተረጓጎምም የሚሰጥበት ሁኔታ ይኖራል። ታዲያ በእንዲህ ሁኔታ ፣ በተሳሳተ መረጃ አሰጣጥ በኮምፒዩተር ፕሮግራም የቀረበን ሰነድ መሠረት አድርጎ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ ፤ በግለሰቦች ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ መገመቱ አይከብድም።»

Russland Internet VKontakte Hauptsitz in Sankt Petersburg
ምስል Olga Maltseva/AFP/Getty Images

በሐምበርግ፤ የግል መረጃ ሰነዶች ጥበቃ ጉዳይ ኀላፊ ዮሐንስ ካስፐር እንዳሉት፤ ታላላቆቹ ዓለም አቀፍ መረጃ ሰብሳቢዎች፤ ለምሳሌ «ፌስቡክ» ወይም «ጉግል»፣ አንድነት የማይንጸባረቅባቸውን የህግጋት አንቀጾች በመጠቀም አብዛኛውን ጊዜም ለዘብተኛ አቋም አላት ከምትባለው ከአየርላንድ በኩል ነው የሚንቀሳቀሱት።በመሆኑም በአየርላንድ የሚገኙ ተባባሪዎቻችንን በማበረታታት ፤ የግለሰቦችን መረጃ የመጠበቅ መብት የሚያስከብር የተጠናከረ አውሮፓ አቀፍ ደንብ ይኖር ዘንድ አብረው እንዲታገሉ እንጋብዛቸዋለን ነው ያሉት። የአውሮፓው ሕብረት የግል ሰነድ ጥበቃ ደንብ ቢዘገይ- ቢዘገይ እ ጎ አ

በ 2016 ተግባራዊ እንደሚሆን ተስፋ ተደርጓል። አንዳንድ ዓለም አቀፍ የግል ሰነድ ሰላዮች ተግባር የሚገታው የማሕበራዊ መገናኛ ብዙኀን አሠራርም ፤ በሰነድ አጠባበቅ ረገድ የግለሰቦችን የማይገፈፍ መብት ሲያከብሩ መሆኑን ዮሐንስ ካስፐር ይገልጻሉ።

Ukraine Internet Partei Star Wars Charaktere
ምስል Reuters

«ቁም ነገሩ፤ የግል ሰነድ አጠባበቅ፤ ተገቢውን ክብደት የሚያገኘው፤ የግል ሰነድ አጠባበቅን መሠረታዊ መብት ፤ ሁሌ፤ በተናጠል ከየሃገራቱ የዜጎችን መብት የማክበር ግዴታ ጋር ብቻ እያቆራኘን በማየት ሳይሆን፤ ሰብአዊ ዓለምአቀፍ ነጻ የመገናኛ መብት መሆኑን ተገንዝበን ስንንቀሳቀስ ነው።

ይህን ስናደርግም ብቻ ነው በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለውን ፤ ማለትም፣ የስለላ አገልግሎት ሠራተኞች፤ በውጭ ሃገራት እየሰለሉና መረጃዎችን እየሰበሰቡ ከሌሎች የስለላ ድርጅቶች ጋር ሰነዶች የሚለዋወጡበትን ድርጊት መግታት የምንችለው። ይህ ግልጽ ሆኖ መቅረብ አለበት። የስለላ ድርጅቶች፤ ህጉ በሚፈቅድላቸው ዘርፍ ብቻ እንዲያተኩሩ የምናደርጋቸው እናው ነን። የሰዎችን ሰብአዊ መብት፤ ሐሳብ የመለዋወጥ መብት እንዲያከብሩ የምናስተምራቸውም እኛው ነን።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ