1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ታላቅ ረሐብ 30ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18 2007

በፖቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥ በነበረችው ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ የሞቱ ሰዎች ቁጥር አከራካሪ ነው። ቁጥሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ አንድ ሚሊዮን ያደርሰዋል።

https://p.dw.com/p/1DdSh
ምስል AP

የታላቋ ብሪታኒያ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቢቢሲ ዓለምን ያስደነገጠውን የኢትዮጵያ ዜና ካቀረበ ሰላሳ አመታት ተቆጠሩ። በዘመኑ ስልጣን ላይ የነበረው የደርግ መንግስት 10ኛውን የአብዮት በዓል ሊያከብር ሽር ጉድ በሚልበት በ1977 .. በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲታወቅ ፈቃደኛ አልነበረም። የዛሬ 30 ዓመት በቢቢሲ የተላለፈው የማይክል በርክ ዜና ለሶስት ተከታታይ አመታት የጠፋውን ዝናብ ተከትሎ የተፈጠረውን ረሃብ ለዓለም ይፋ አደረገ።

በፖቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥ በነበረችው ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ የሞቱ ሰዎች ቁጥር አከራካሪ ነው። ቁጥሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ አንድ ሚሊዮን ያደርሰዋል።

የማይክል በርክ ዜና ዓለምን ከማስደንገጥ ባሻገር መንግስታት፤ የእርዳታ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎችን የሚታደጉበትን መንገድ አመቻችቷል።ኢትዮጵያ ያንን አስከፊ ዘመን እነ ቦብ ጊልዶፍን በመሳሰሉ ግለሰቦች ባዘጋጇቸው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እና የግብረ ሰናይ ተቋማት ርብርብ በእርዳታ ተሻግራለች።

30 አመታት በኃላ ኢትዮጵያ በበርካታ ኢኮኖሚያዊ፤ፖለቲካዊ ማህበራዊ ለውጥ ውስጥ አልፋለች። ቢሆንም የድርቅና የረሃብ ስጋት ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። የችግሩ ስፋትና ጥልቀት የ1977ቱን ያክል አይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት በተወሰኑ የሃገሪቱ ክፍሎች ድርቅ መፈጠሩ አልቀረም። እ... 2008 እስከ 2012 ባሉት አመታት በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው ድርቅ በኢትዮጵያ ላይም ተጽዕኖ ማሳደሩን አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ይገልጻሉ።

Äthiopien unterernährtes Kind mit Mutter
ምስል picture alliance/dpa

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሃራ በታች ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ ሃገሮች አንዱ እንደሆነ ይነገራል።አሁንም ግብርና የኢኮኖሚው ዋንኛ መሰረት ሆኖ ቀጥሏል። ዶ/ር ፋንታሁን መንግስቱ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማዕከል ሃላፊ ናቸው። ዶ/ር ፋንታሁን የግብርናው ዘርፍ በከባቢ አየር ለውጥ የሚደርስበትን ተጽዕኖ ለመቀነስ የአከባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ግብርናን ለማሳደግ ከመንግስት ጎን ለጎን ከሚሰሩ ተቋማት መካከል መልካ ኢትዮጵያ አንዱ ነው። መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሆነው መልካ ኢትዮጵያ ሀገራዊ የሰብል ዝርያዎችን እና የግብርና እውቀትን በመጠበቅና በማሳደግ እና በመንከባከብ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል። የመልካ ኢትዮጵያ ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሚሊዮን በላይ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረው ስራ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ያምናሉ።

አለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ተቋም (International Food Policy Research Institute) ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ኢትዮጵያ አሁንም የረሃብ ስጋት ካለባቸው ሀገራት ጎራ ተመድባለች። የዓለም ረሃብ መለኪያ (Global Hunger Index) መሰረት ኢትዮጵያ ከ 76 ሃገሮች በ 70 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ለረሃብ ያላትን ተጋላጭነት ከዓመት ዓመት እየቀነሰች ብትመጣም አሁንም ሙሉ በሙሉ ነጻ አለመሆኗን ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማዕከል ሃላፊው ዶ/ር ፋንታሁን መንግስቱ ከ30 አመታት በፊት በተከሰተው ድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ስራዎች በመሰራታቸው ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ይናገራሉ። እንደ ዶ/ር ፋንታሁን መንግስቱ በአለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ስጋት አይስማሙም።

Äthiopien 1984
ምስል AP

በመንግስት፤መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ተመራማሪዎች የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ፤የከባቢ አየር ለውጥን ለመቀነስና ከዚህ ቀደም እንደ ተከሰቱት አይነት ድርቅና ረሃብ ዳግም እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚሰሯቸው ስራዎች መሰረት በገበሬው አቀባበል ላይ መሰረት ያደረገ ነው። የኢትዮጵያ ገበሬ በሚኖርበት አካባቢ፤በምርቶቹ እምነትና ፍልስፍናው ብዙ አይነት ነው። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከገበሬዎች ጋር የመስራት እድል የገጠማቸው ዶ/ር ሚሊዮን በላይ አዳዲስ አሰራሮች ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ