1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግስት ድረ-ገጾች

ረቡዕ፣ የካቲት 25 2007

መንግሥታት በኢንተርኔት አማካይነት ከዜጎቻቸዉጋር የሚደረግ ግንኙነት E-Government በመባል ይታወቃል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ክፍል ባደረገዉ ጥናት መሰረት ደቡብ ኮሪያ፤አውስትራሊያ፤ሲንጋፖር እና ፈረንሳይ ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀዳሚዉን ሥፍራ ይይዛሉ።

https://p.dw.com/p/1El4s
Symbolbild Offline
ምስል Fotolia/doomu

በአማርኛ፣ትግሪኛ፣ኦሮምኛ እና እንግሊዘኛ የተደራጀው የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ድረ-ገጽ 'http://www.epa.gov.et' የተሰኘ አድራሻ አለው። ድረ-ገጹ የተቋሙን አመሰራረት የሚገልጽ ሐተታ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በሐምሌ 25/2012 የተጻፈ የሐዘን መግለጫ አስፍሯል። የድረ-ገጹ ትግሪኛ ገጽ በአማርኛ የኦሮምኛው ገጽ ደግሞ የእንግሊዘኛ ሐተታዎች ሰፍረውበታል። የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የተመለከተ መረጃ ግን ማግኘት አይቻልም። በምስል ክምችት ቋቱ ውስጥ የፌዴራል ክልሎች ሰንደቅ አላማዎች እና የከረሙ ግን ደግሞ የደበዘዙና አቀራረባቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፎቶግራፎች ተደርድረዋል። የድረ-ገጹ የስራ ማውጫ እና የውይይት ገጾች ባዶ ናቸው። ተቋሙን ለማግኘት የተቀመጠው አድራሻ «Contact Us» የሚለዉ ክፍል አይሰራም።

ይህ ድረ-ገጽ የመንግስት ተቋማትን፤ሚኒስቴር መስሪያቤቶችን እና ቢሮዎችን ባቀፈው የኢትዮጵያ መንግስት ኦፊሴላዊ ድረ-ገጽ (Ethiopian Govewrnment Portal) ላይ ከተዘረዘሩት መካከል አንዱ ነው።

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የዓለምን የርስ በርስ ግንኙነት በእጅጉ የለወጠው የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ካመጣቸው ትሩፋቶች መካከል መንግስት ከዜጎች ጋር ያለውን ግንኙነት ይቀይራል የተባለለት E-Government ይጠቀሳል። ጽንሰ ሃሳቡ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በህዝብ አስተዳደር ውስጥ በመጠቀም የስራ ፍሰትን እና አገልግሎትን ማቀላጠፍ በመንግስት እና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማሳደግ ዜጎችን ማሳተፍ እና ማበረታታት ይቻላል የሚል መርህ አለው። ይህ ቴክኖሎጂ መንግስት ከመንግስት፤መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ እና መንግስት ከዜጎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ያሰፍናል የሚል ተስፋ ተጥሎበታልም።

Symbolbild Computerkriminalität
ምስል Michael Bocchieri/Getty Images

የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ካቀረባቸውና መንግስት ከሌሎች መንግስታት፤ተቋማትና ዜጎች ጋር ለሚኖረው ግንኙነት አዲስ መንገድ ከከፈቱት ትሩፋቶች መካከል ድረ-ገጽ (Web page) አንዱ ነው። አቶ ዮሴፍ አባተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ «የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሳይንቲፊክ ኮምፒውቲንግ» ማዕከል ኀላፊ ናቸው።

በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2014 ዓ.ም. የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ባደረገው እና መንግስታት በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰጡትን ግልጋሎት በፈተሸው ዘገባ (United Nations E-Government Survey 2014: E-Government for the Future We Want) መሰረት ኢትዮጵያ ከመካከለኛ ደረጃ ተቀምጣለች። ኢትዮጵያን ጨምሮ በዚህ ምድብ የተዘረዘሩት ሃገሮች ውስን የኢንተርኔት መሰረተ ልማት፤የሰለጠነ የሰው ሃይል ያለባቸው ሃገሮች ናቸው። በዘገባው ከ72ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው የኢትዮጵያ መንግስት በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማስፋፋት የተሻለ ተብሏል። ከ2011-2015 ባሉት አመታት 219 የኢንተተርኔት አገልግሎቶች ለመጀመር ብሄራዊ እቅድ መያዙን ያሰፈረው ዘገባው ግብርና ላይ መሰረት ያደረገውን ኢኮኖሚ በኢንፎርሜሽን ኮምዩንኬሽን ቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት አድንቋል። ሃገሪቱ በዘርፉ ስኬታማ ልትሆን እንደምትችልም ጥቆማ ሰጥቷል።በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን አቶ ዮሴፍ አባተ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት በዓለም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ተርታ የሚመደብ ነው።ባለፈው አመት ማኪንዜይ የተሰኘ ኩባንያ ባወጣው ዘገባ የስርጭት መጠኑ ከ2 በመቶ እንደማይበልጥ እና በሃገሪቱ 97.8 በመቶ ዜጎች ኢንተርኔት እንደማያገኙ ይፋ አድርጎ ነበር። ባለው የኢንተርኔት አገልግሎትም ቢሆን የመንግስት ሚኒስቴር እና ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ለዜጎች አገልግሎት የሚያቀርቡባቸው ድረ-ገጾች ይገኛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ኦሬጎን ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ እና ማህበረሰብ የዶክትሬት ተማሪ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ሃይለሚካኤል ድረ-ገጾቹ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውን ያስረዳሉ።

Google Logo Firmensitz in New York
ምስል picture-alliance/epa/A. Gombert

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው አቶ ዮሴፍ አባተም የኢትዮጵያ መንግስት የሚኒስቴር እና የባለስልጣን ቢሮዎች ድረ-ገጾች በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ይናገራሉ።

የመንግስት የሚኒስቴር እና የባለስልጣን መስሪያ ቤቶችን ዝርዝር እና አድራሻ በያዘው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን ድረ-ገጽ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አድራሻ ይገኛል። <http://www.ethiopar.net/>የተሰኘ አድራሻ የተሰጠው ይህ ድረ-ገጽ ስለ ኢትዮጵያ አጠቃላይ መረጃ፤ህገ-መንግስት፤ባህል፤ የመንግስት አወቃቀር እና የፖለቲካ ምህዳር መረጃ የያዙ ክፍሎች አሉት። የምክር ቤቱን እንቅስቃሴ፤ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ወይም ሊወያይባቸው እቅድ የያዘባቸው ጉዳዮችን የተመለከተ ምንም አይነት መረጃ ከዚህ ድረ-ገጽ አይገኝም። የድረ-ገጹ አደረጃጀት፤የቀለም አመራረጥ እና አቀራረብም ቢሆን የምክር ቤቱን ደረጃ የሚመጥን አይደለም። <http://www.hofethiopia.gov.et>በተሰኘ የድረ-ገጽ አድራሻ የሚገኘው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በበኩሉ በቅርብ የተከናወኑ ውስን ጉዳዮችን ቢዘረዝርም ደረጃው ግን ዝቅተኛ ነው። አቶ እንዳልካቸው ሃይለሚካኤል በተደጋጋሚ ከጎበኟቸው ድረ-ገጾች መካከል በአግባቡ የማይሰሩ መኖራቸውን ይናገራሉ።

አቶ ዮሴፍ አባተ ድረ-ገጾቹን የሚሰሩ እና የሚከታተሉ ባለሙያዎች የእውቀት ማነስ የችግሩ ዋንኛ ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ።

አቶ እንዳልካቸውም ሆኑ አቶ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ድረ-ገጾች በተንቀሳቃሽ ስልኮች መጠቀም በሚያስችል መንገድ ሊዘጋጁ እንደሚገባ ይስማማሉ። በተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካኝነት በኢትዮጵያ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ የሚገኙእና ማንኛውንም ቋንቋ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያንን ለማገልገል ቀላል ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ