1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ጃዝ በዓለም አቀፉ መድረክ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 11 2007

የኢትዮጵያ የጃዝ የሙዚቃ ስልት በአንጋፋዉ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ የዓለምን የሙዚቃ መድረክ ከረገጠ በኋላ ተወዳጅነቱ እየሰፋ መምጣቱ ይታወቃል። እንደ ባህል ሙዚቃችን ሁሉ መለያችንን የሆነዉ ኢትዮ-ጃዝ የዓለምን የሙዚቃ አፍቃሪዎች ይበልጥ እየማረከ መሆኑም ተነግሮለታል፤ በርካታ ጃዝ አፍቃሪ ኢትዮጵያዉያን ሙዚቀኞችም ብቅ ብቅ እያሉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1FPgS
Äthiopien Jazz Musiker Getatchew Mekurya
እዉቁ የሳክስፎን ተጫዋች አቶ ጌታቸዉ መኩርያምስል Mario Di Bari

የኢትዮ-ጃዝ በዓለም አቀፉ መድረክ

«በተለያዩ አካባቢዎች በዩኔስኮ አዘጋጅነት የሚከበረዉ ዓለማቀፉ የጃዝ ቀን፤ በተለይ በማዕከላዊነት የምናከብረዉ ልዩ እና ታላቅ ጉዳዮች በሚከናወኑበት ሥፍራ ነዉ፤ እኔ እንደማስበዉ ደግሞ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ይህን ልዩ በዓል በመዓከላዊነት የማስተናገድ እድል ማግኘት ይኖርባታል»
ሲሉ ዓለም ዓቀፉ የጃዝ ቀን ዘንድሮ በአፍሪቃ ሕብረት መዲና በአዲስ አበባ እንዲከበር ያላቸዉን ፍላጎት የገለፁት ፤ የ«UNESCO» ማለት የተመ የትምሕርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት የአዲስ አበባዉ ቅርንጫፍ ዳይሪክተር ፊርሚን ማቶኮ ነበሩ ። በየዓመቱ የሚከበረዉ ዓለማቀፉ የጃዝ ቀን ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ተካሂዶአል።

Äthiopien Jazz Musiker Munit Mesfin
ሙዚቀኛ ሙኒት መስፍንምስል Mario Di Bari

በተለያዩ ሃገራት በጃዝ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ በደማቅ ሥነ-ስርዓት የሚከበረዉ የጃዝ ቀን አዲስ አበባ ዉስጥ ሲከበር ዘንድሮ የመጀመሪያዉ ነዉ። ድግሱን በጋራ ያዘጋጁት የተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፤ የሳይንስና የባሕል ድርጅት «UNESCO» ከአዲስ አበባዉ አልያንስ ፍራንሲስ ጋር በመተባበር ነዉ።

የጃዝ ሙዚቃ በማኅበረሰቦች ዘንድ ያለዉን ከፍተኛ ተወዳጅነትን በመጠቀም ማኅበረሰቦችን ለማስተሳሰር ብሎም ሰላምንና የጋራ ሥራን ለማጠናከር፤ ሲባል በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ,ም «UNESCO» ፓሪስ ላይ ዓመታዊዉን ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት ዓመታዊ የጃዝ ቀን ሲባል እንዲከበር መወሰኑ ይታወቃል። ከጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ሃገሮች ቀኑ በጃዝ ሙዚቃ አፍቃሪዎችና ሙዚቀኞች ዘንድ ይከበራል። ዘንድሮ ዓለም አቀፉን የጃዝ ሙዚቃ ቀን አዲስ አበባ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲዘጋጅ ሃሳብ በማቅረብና በማቀናበር ጥረት የጀመረችዉ የጃዝ ሙዚቃ አቀንቃኝዋ ሙኒት መስፍን ይህን ዝግጅት ለማቀናበርና ለመጀመር ያሰብኩት በአለፈዉ ዓመት ነዉ።

«የተመ የትምሕርት፤የሳይንስና የባሕል ድርጅት «UNESCO» በጎርጎረሳዉያኑ በየዓመቱ አፕሪል ሰላሳ የጃዝ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ወስኖአል። በዚህ ቀን እኛ ኢትዮጵያዉያን የሙዚቃ ባለሞያዎች የጃዝ ሙዚቃ አቀንቃኞችና አቀናባሪኞች የጃዝ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ዝግጅት አሰናድተዉ ስለ ጃዝ ሙዚቃ አመጣጥ ስለተለያዩ የጃዝ ቅኝቶች፤ ስለሙዚቃ አቀናባሪዎቹ እና ስለ አቀንቃኞቹ ታሪክ የምናወራበት የምንማማርበት ብሎም ጃዝን ሞቅ ባለ ሁኔታ አስተጋብተን የምንደሰትበት ቀን ይሆናል ብለን ጀምረናል። ባለፈዉ ዓመት በአዘጋጀነዉ አንድ የሙዚቃ ድግሳችን ላይ ከዩኔስኮ የመጡ የዘጋቢ ፊልም ቀራጮች ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ሕብረት ማዕከል በመሆንዋ የዲፕሎማቶች መኖርያ እንዲሁም የተለያዩ የዉጭ ሃገር ተቋማት በመኖራቸዉ የኢትዮ ጃዝም ኢትዮጵያ ዉስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እየሆነ በመምጣቱ በየዓመቱ የሚከበረዉን የጃዝ ቀን የዚህን ዓመት ድግስ በመዓከላዊነት አዲስ አበባ ላይ ቢዘጋጅ ምን አይነት ጥቅም ይኖረዋል ለሙዚቀኞቹ ለኅብረተሰቡ ብሎም ለሃገሪቱስ በሚል አንድ ቃለ ምልልስ ከ «UNESCO» ጋር አድርጌ ነበር። ከዝያ ጊዜ ጀምሮ ነዉ ይህን ቀን እኛ ኢትዮጲያ ያለንም የጃዝ ሙዚቃ አፍቃሪዎችና ሙዚቀኞች እንድናከብረዉ ስል ሃሳብ አቅርቤ ለመጀመር የበቃነዉ።»

አዲስ አበባ ላይ የነበረዉ ዝግጅት እጅግ ሰፊ የተባለ ባይሆንም የተዋጣለት እንደነበር ሙዚቀኛ ሙኒት ገልፃለች። ከሁለት ዓመት በፊት ጃዝ አኩስቲክ ከተሰኘ ወጣት የሙዚቃ ባንድ ጋር የጃዝ የሙዚቃ ድግሱን በጀርመን በተለያዩ ከተሞች ያቀረበዉ እዉቁ ጎልማሳ የጊታር ተጫዋችና የሙዚቃ አስተማሪ ግሩም መዝሙር የጃዝ ሙዚቃ በኢትዮጵያ እየዳበረ መምጣቱን ገልጾአል።

Äthiopien Jazz Musiker The Jazzmaris Band
ጀርመናዉያኑ ዮርግ ኦላፍ እንዲሁም ሁኖክና ናቲ በጃዝማሪ ባንድ-አዲስ አበባምስል Mario Di Bari


« ኢትዮ ጃዝ ረጅም የሆነ የራሱ ታሪክ አለዉ። ኢትዮ ጃዝ በ 1950 ዎቹና 60ዎቹ የነበረ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮ-ጃዝ በመባል ጃዝና የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅላጼ ተቀላቅሎ የሚደመጥበት አይነት ሙዚቃ መሆኑ የታወቀ ነዉ። ይህ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃም እጅግ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቶአል። ይህ የሙዚቃ ስልት የኛ የኢትዮጵያዉያን አንዱ መለያችንም እየሆነ መጥቶአል። በሃገርም ዉስጥ ያሉ በዉጭም ያሉ ሰዎች የሚወዱት ዓይነት የሙዚቃ ስልት እንደሆነ በደንብ የታወቀ ነዉ። ጥንትም፤ ከዝያም ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ፤ ኢትዮጵያም ዉስጥ ሆነ ዉጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ሙዚቀኞች እያዳበሩት የመጡት አንዱ የሙዚቃ ስልታችን ሆንዋል። እንደ ኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ሁሉ ኢትዮ- ጃዝም አንዱ መለያችን ሆንዋል»


የዓለም ዓቀፉን የጃዝ ቀን በአዲስ አበባ ላይ በመዓከላዊነት ላይ እንዲከበር ከአሁኑ ጥረት ላይ የሚገኙት ሙዚቀኞች አዲስ አበባ በመጀመርያ የአፍሪቃ ማዕከላዊ ከተማ በመሆንዋ ሌላዉ የዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ መሆኑን ሙዚቀኛ ሙኒት መስፍን ገልፃለች።

Äthiopien Jazz Musiker Mulatu Astatke
የሙዚቃ ባለሞያና መምህሩ ግሩም መዝሙርምስል Mario Di Bari

ሙዚቀኛ ሙኒት ጃዝ ሙዚቃ በራሱ ጥቁር ሕዝቦች ፍላጎታቸዉን ሕመማቸዉን የሚገልፁበት መገልገያ መሳርያቸዉ ሆኖ መጀመሩንና የተለያየ የጃዝ ሙዚቃ ስልት እንዳለ በመተንተን ገልፃለች። እንደ ሙኒት «ጃዝ የተለመደ የሙዚቃ ስልት የራስ ፈጠራ የሚበዛበት፣ ስሜትን ይዞ ቅላፄዉ በጣም አስደሳች የሆነና ሰዉ ራሱን የሚገልፅበት እንደ ስሜት ከነገ ዛሬ የሚለያይ አይነት የሙዚቃ ስልት ነዉ። መድረክ ላይ ደስተኛ ሆነዉ ከወጡ ደስ የሚል የጃዝ ፈጠራን ማሳየት አልያም ማየት ይቻላል። » ስትል ተናግራለች።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የጃዝ ሙዚቃ እየሰፋና እየተወደደ ብሎም በምስራቅ አፍሪቃ የሙዚቃ መድረክ ታዋቂነትን እያገኘ መምጣቱን የሚናገረዉ የሙዚቃ መሳርያ ባለሞያዉ ግሩም መዝሙር በበኩሉ በጃዝ ሙዚቃ ዉስጥም የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ ቅኝት በመካተቱ የኢትዮጵያን የጃዝ ሙዚቃ ለየት ያለ ቃና እንዲኖረዉ ማድረጉን ገልፆአል።

« የኢትዮጵያ ጃዝ ኢትዮጵያዊ መልኩን አያጣም። ቅኝቱም ሆነ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያን ጨምሮ የባህል መሳርያዎች እንደ ክራር መሰንቆን ሁሉን ያካትታል። ከሌላዉ የዓለም ክፍል የኢትዮጵያን ጃዝ የሚለየዉ የራስችንን ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያና ቅኝቱን በማካተታችን ነዉ። ኢትዮ-ጃዝ በጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ እንዲሁም አሁን ደግሞ በአዲስ አኩስቲክ እንዲሁም በሌሎችም ሙዚቀኞች አማካኝነት ዓለማቀፉን መድረክ ተዋዉቋል እየተዋወቀም ነዉ። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ጃዝ በተለይ አሁን ተቀባይነት እያገኘ ነዉ። ይህ ሁኔታ አሁን አሁን ሌሎች የዓለም ሃገራት በምስራቅ አፍሪቃ የሚሰማዉን የሙዚቃ ቅኝት እንዲያደምጡ መጋበዙ ታይቶአል። ቀደም ሲል ግን ከምስራቁ ይልቅ የምዕራብ አፍሪቃ ሙዚቃ የበለጠ ተደማጭነት እንደነበረዉ እሙን ነዉ። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ምዕራብ አፍሪቃዉያኑ ሃገራት ሙዚቃዎቻቸዉን በትክክል በማቀናጀት ወደ ሌላዉ ሃገር እንዲደመጥ አድርገዉ በመዉሰዳቸዉ ነዉ። ይህ አሁን የጀመርነዉ የሙዚቃ ቅንብርና ሙዚቃን ይበልጥ የማስተዋወቅ ጅማሮ ወደፊት በደንብ አድማጭ እንዲኖረን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን እንድናገኝበት ዓለም አቀፍ መድረክ ወደ ሃገራችን ለመዘርጋት እንደሚያስችለን ምንም ጥርጥር የለኝም»

ሙዚቀኛ ሙኒት በበኩልዋ «የኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ መድረክ አልተሰለችም እንብዛምም አልተለመደም፤ ግን የሰሚዉ ቁጥር እየተበራከተ በመምጣቱ ይህን መድረክ ተጠቅመን የዓለምን የጃዝ ሙዚቃ ዓመታዊ ክብረ በዓል አገራችን ላይ በማዕከል እንዲከበር ለማድረግ የሚያግደን ነገር የለም» ስትል ተናግራለች።

የዓለም አቀፍን የጃዝ ቀንና የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃን በተመለከተ ኢትዮጵያዉያኑ ወጣት ሙዚቀኞች የጀመሩት ሥራ ይበል የሚያሰኝ ይመስለናል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።



አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Äthiopien Jazz Musiker Girum Mezmur
የኢትዮ ጃዝ አባት አንጋፋዉ ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄምስል Mario Di Bari