1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍጋኒስታን የስልጣን ፉክክር መጨረሻ

ሰኞ፣ መስከረም 12 2007

የአፍጋኒስታኑ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር አሽራፍ ጋኒና የቀድሞዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላህ አብዱላህ ምንም እንኳን ሁለቱ ተፎካካሪዎች ስለምርጫዉ ዉጤትና ስለወደፊት የስልጣን ክፍፍል ሲወዛገቡ ቢቆዩም በመጨረሻ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት ተስማምተዋል። ይህ ለአፍጋኒስታን የስልጣን ፉክክር መጨረሻ ይሆን ይሆን?

https://p.dw.com/p/1DH69
Einigung über Einheitsregierung in Afghanistan unterzeichnet 21.9.2014
ምስል AFP/Getty Images

በትናንቱ የስልጣን መጋራት ስምምነት መሰረት አሽራፍ ጋኒ የሀገሪቱን ካቢኔ ይመራል። በምርጫ ተፎካካሪያቸው የነበሩት አብዱላህ አብዱላህ ደግሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተብለው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ይይዛሉ። የአፍጋኒስታኗ ጋዜጠኛ ናጁባ አዩኒ ሁለቱ ተፎካካሪዎች በአዲሱ ብሔራዊ አንድነት መንግሥት ውስጥ የሚኖራቸው ስልጣን ብዙ ችግር ሊያስከትል ይችላል በሚል ሰግታለች።« ምክንያቱም ሁለት ሰዎች አንድ ቤት ሊመሩ አይችሉም። ይህ ፍፁም አይሰራምሉ። እና አሁን ሁለት ሰዎች አንድ ሀገር መምራት አለባቸው? በፍፁም። በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። እነዚህ ሁለት ሰዎች እና ጎራዎቻቸው በጣም የተለያየ አመለካከት ነው ያላቸው። እንዴት ብሎ ነው ይህ የሚሳካው? እጅግ አዳጋች ነው የሚሆነው።»

አብዱላህ አብዱላህ ባለፈው ሚያዚያ ወር የተካሄደውን የመጀመሪያ ዙር ምርጫ አሸንፈው ነበር፣ ነገር ግን አስፈላጊውን አብላጫ ድምፅ አላገኙም። በሰኔ ወር በተካሄደው የመለያ ምርጫም የቀድሞው የፋይናንስ ሚኒስትር እና ከውጭ ሀገር ወደ ሀገራቸው የተመለሱት አሽራፍ ጋኒ አሸናፊ ሆኑ። አብዱላም ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ውጤቱን እንደማይቀበሉ ባስታወቁበት ጊዜ ነበር ጠንካራው የስልጣን ሽኩቻ የተጀመረው።« የአፍጋኒስታን ህዝብ ፍላጎት አለመረጋጋቱ እንዲያበቃና ህጋዊ እና ተቀባይነት ያለው መንግሥት እንዲመሰረት ነው። ለዚህ ነው ይህ የተጭበረበረ ድምጽ እንዲጣራ የምፈልገው። ይህም ነው የህዝባችን ትክክለኛ ፍላጎት።»

የአፍጋኒስታንን የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር እንቅፋት ሲገጥመው ዮናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች እንደ ጀርመን ያሉ ሀገራት የሚሰጡትን ሰብዓዊ ርዳታ እንደሚያቋርጡ ዛቻ አሰሙ። የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም ባንክ ባልደረባ አሽራፍ ጋኒ ሀገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ለህዛባቸው በመንገር ባስቸኳይ የስልጣኑ ፉክክር እንዲያበቃ ተማፀኑ።

Archivbild Einigung über Einheitsregierung in Afghanistan unterzeichnet
ምስል picture-alliance/AP Photo

«ህዝባችን ድሀ ነው። የኛ ሰዎች ርዳታ ይሻሉ። ልማት ያስፈልገናል። ህዝባችን በየቀኑ እየሞተ ነው። የኃይል ርምጃ እና ጥገኝነታችንን ማቆም አለብን። ታታሪ እና ግልፅ የሆነ መንግሥት ያስፈልገናል። »ምንም እንኳን አሽራፍ ጋኒ እና አብዱላህ አብዱላህ በመጨረሻ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት ቢስማሙም በርካታ ምሁራን እንደሚሉት፤ በሁለቱ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት አዲሱን መንግሥት ስኬታማ ማድረጉ አጠያያቂ ነው። ያለፉት ወራት የስልጣን ፉክክር እንዳንፀበረቀው ከሁለቱ የአፍጋኒስታን ባለስልጣናት በስተጀርባ የኃይሉን ተግባር ሊቀጥሉ የሚችሉ የተለያዩ ቡድኖች ይገኛሉ። ይህን ልዩነት ደግሞ አሁንም እንደበፊቱ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሰው የታሊባን ቡድን ለቀጣይ የሀይል ርምጃ እንዳይጠቀምበት ያሰጋል። አሽራፍ ጋኒ የዛሬ ሳምንት በይፋ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መኃላ ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ