1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«አይ ሲ ሲ» ዉሳኔና የፕሬዚዳንት ኦማር ኧል በሽር ድል

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2007

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት «አይ ሲ ሲ» በሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ኧል በሽር ላይ የጣለዉን የጦር ወንጀልነት ክስ ለተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/1E4Qp
Sudan Präsident Umar Hasan Ahmad al-Baschir
ምስል Reuters

ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በዳርፉር ሱዳን አመፅን ለማረቅ ሲባል በተፈጸመዉ የወንጀል ተግባር ሳብያ ፕሬዚደንት ኦማር ኧልበሽርን ከጎርጎረሳዉያኑ 2003 ዓ,ም ጀምሮ ለምርመራ ሲፈልጋቸዉ መቆየቱ ይታወቃል። የ «አይ ሲ ሲ» ን ዉሳኔ በተመለከተ፤ ዶይቼ ቬለ በሱዳን ዩንቨርስቲ መምህርና የሪፍት ቫሊ «ስምጥ ሸለቆ» ተቋም አባል ማጋዲ ኢል ጊዙሊን አነጋግሮአቸዉ ነበር።

Internationaler Strafgerichtshof mit Logo


ፕሬዝዳት ኧል-በሽር ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በተገኙበት እንዲያዙ ማዘዣ ከቆረጠላቸዉ በኋላ በአንዳድ አፍሪቃ ሃገራት ጉብኝት ቢያደርጉም ምዕራባዉያን መንግሥታት ኧል በሽር እንዲታሰሩ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸዉ ይታወቃል። በሰብዓዊነት ላይ ከፍተኛ ግፍ በመፈፀም ወንጀል ተከሰዉ በ «አይ ሲ ሲ» ሲታደኑ የቆዩት ፕሬዚዳንት አልበሽር የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት « በቂ ትብብር ባለማግኘቱ» «አቅሙንም ወደ ሌሎች አስቸኳይ ጉዳዮች ለማዞር» መምረጡን ገልፆአል። ይህ የ «አይ ሲ ሲ» ዉሳኔ ለሱዳን ህዝብ ምን ማለት ይሆን? በሱዳን ዩንቨርስቲ መምህርና የሪፍት ቫሊ «ስምጥ ሸለቆ» ተቋም አባል ማጋዲ ኢል ጊዙሊ እንደሚሉት በ«አይ ሲ ሲ» ቀጣይ እጣፈንታ ላይ ዉሳኔ ያስፈልጋል፤ «በመጀመርያ በጣም የሚገርመዉ ነገር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፈለገ ጉዳዩን በቸልታ ሊያልፈዉ ይችላል መባሉ ነዉ። እንደኔ እምነት የፀጥታዉ ምክር ቤት በ «አይ ሲ ሲ» ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ዉሳኔ እንዲያሳልፍ የሚጠይቅ ይሆናል። ከአሁን ቀደም ምንም አይነት ርምጃ ያልወሰደዉ የፀጥታዉ ምክር ቤት፤ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ይህን ጉዳይ ለማስተናገድ ዝግጁ አይመስልም። እንደኔ እምነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለዉ አማራጭ ያለም አይመስለኝም።»

በሱዳን ዩንቨርስቲ መምህርና በሪፍት ቫሊ ተቋም አባል እንደ ማጋዲ ኢል ጊዙሊ፤ ኢ ሰብዓዊ በሆነዉ ከፍተኛ ግጭት ተጎጂ እና ተጠቂ የሆነዉ የዳርፉር ህዝብም ፍትህ ከ «አይ ሲ ሲ» ካልመጣ ከማን ሊያገኝ እንደሚችል ጥያቄ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል። እስካሁን በሱዳን የሕግ-ስርዓት ፍትህን ማስፈን ማግኘት አልተቻለም። «አይ ሲ ሲ» በአማራጭነት የቀረበዉም ከሱዳን ሕግ ጎን ለጎን ይህን ፍትህ ያስገኛል በሚል ነበር። ግን ይህ እንዳልተቻለና ፍትህ ከየት ሊገኝ ይችላል የሚለዉ ጉዳይ አሁንም ጥያቄ ዉስጥ መሆኑን ጊዙሊ ገልፀዋል። «ከደቡብ አፍሪቃዉ፤ ከሩዋንዳዉ የዘር ጭፍጨፋ በኋላ ያለዉን ሁኔታ ስናስብ እንዲሁም «አይ ሲ ሲ» ክሱን ያነሳበትን የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያ ጉዳይን ስናይ በዳርፉር የፍትህ ፖለቲካ ምን ሊመስል እንደሚችል ጥያቄ የሚያጭር ሆኖ እናገኘዋለን»
የፀጥታዉ ምክር ቤት የ «አይ ሲ ሲ» አቃቤ ሕግ ጉዳዮን አለመሳካቱን ገልፆአል። ይህ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም ያሉት በሱዳን ዩንቨርስቲ መምህርና የሪፍት ቫሊ ተቋም አባል ማጋዲ ኢል ጊዙሊ በመቀጠል። « ይህ ዉሳኔ ይሆናል ብለን የምናስበዉም አይደለም። በዳርፉር ወንጀሉ ከተፈፀመ ብዙ ግዜ አልሆነዉም። የፕሬዚዳንት አልበሽር ዲፕሎማስያዊ የመንቀሳቀስ መብት ተወስኖአል። ቢሆንም ከ «አይ ሲ ሲ» በዚህ የፍርድ ዉሳኔና አቋም ኧል በሽር ብዙ ፖለቲካዊ ጥቅምን አግኝተዋል። ኧል በሽር የፀረ ቅኝ አገዛዝ አቊማቸዉን በተደጋጋሚ ሲያንፀባርቁ ይደመጣሉ። ዛሬ አልበሽር ይህን ተደጋጋሚ ንግግር ሲያደርጉ ለሚያዳምጣቸዉ ልክ በ1960 ዎቹ ብሔራዊ የነጻነት ትግል ዘመን ዉስጥ ያለ ያኽል ነዉ የሚሰማዉ»
የዛሪ 10 ቀን ግድም ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት «አይ ሲ ሲ» በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ላይ የቀረበው ክስ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲጠናቀቅ አለያም ክሱ እንዲሰረዝ መወሰኑ ይታወቃል።

Omar Hassan Ahmad al-Bashir Präsident Sudan Internationalen Strafgerichtshof Logo
ምስል picture-alliance/dpa/Montage DW

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ