1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት፣ ዩክሬይን እና ሩስያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 9 2007

የአውሮጳ ህብረት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በምሥራቅ ዩክሬይን ዓማፅያን አንፃር አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ተስማሙ። የህብረቱ ዲፕሎማቲክ ክፍል በዚህ በተያዘው የህዳር ወር መጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት አንድ የዩክሬይንን ዓማፅያን ዒላማ ያደረገ አዲስ ዝርዝር እንዲያቀርብ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/1DpKd
EU-Außenministerrat zur Ukraine Krise 17.11.2014 Steinmeier mit Hammond
ምስል picture-alliance/epa/O. Hoslet

አዲሱ ማዕቀብ ሩስያን አለመንካቱ የዩክሬይንን ባለሥልጣናትን ቅር አሰኝቶዋል። የዶይቸ ቬለ ባርባራ ቪዝል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹን እንደዘገበችው፣ ለውዝግቡ መፍትሔ ለማፈላለግ እንዲቻል፣ ከአዲሱ ማዕቀብ ጎን ለጎን ከሩስያ ጋር ውይይት የማካሄዱ ጥረት መቀጠል አለበት።

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ተፅዕኗቸውን በዩክሬይን ለማሳረፍ እየተከተሉት ባለው የውጭ ፖሊሲ ላይ ጠንካራ ወቀሳ በመሰንዘር፣ በሰበቡ የዩክሬይን ውዝግብ ወደሌሎች ያካባቢው ሀገራት እንዳይስፋፋ ማስጋቱን ሰሞኑን በሲድኒ ኦውስትሬሊያ ባሰሙት ንግግር አስጠንቅቀዋል። በሌላ በኩል የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ተቀናቃኞቹ የዩክሬይን ቡድኖች በሚንስክ የደረሱትን የተኩስ አቁም ደንብ እንዲያከብሩ በማሳሰብ የዩክሬይንን ውዝግብ እንዳይባባስ በርግጥ የሚቻለው ሁሉ መሞከሩን የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር አጠያይቀዋል።

Belgien EU Außenministertreffen in Brüssel Federica Mogherini
ምስል picture-alliance/dpa/O. Hoslet

« እየተባባሰ የመጣውን የዩክሬይን ውዝግብ በተመለከተ በሞስኮ ላይ ግፊታችንን ለማጠናከር የሚያስችሉን ቀደም ባሉ ጊዚያት ከደረስናቸው ውሳኔዎች፣ ማለትም፣ ተጨማሪ ማዕቀብ ከመጣል የተሻሉ ሌሎች አማራጮች መኖራቸውን መፈተሽ ይኖርብናል። »

እርግጥ፣ ሽታይንማየር እንዳመለከቱት፣ የሩስያን ኤኮኖሚ ሲመለከቱት ማዕቀቡ ካለ ውጤት እንዳልቀረ መገንዘብ ይቻላል። ሆኖም፣ አውሮጳውያኑን ሚንስትሮች በትናንት በብራስልስ ስብሰባቸው ይህንኑ መንገድ ከመከተል ተቆጥበዋል። ሚንስትሮቹ ምሥራቅ ዩክሬይንን ለመገንጠል የሚታገሉ የአንዳንድ መፍቀሬ ሩስያ ዓማፅያን ንብረት በሚንቀሳቀስበት እና በዝውውር መብታቸው ላይ ዕገዳ ለማድረግ ብቻ ነበር የተስማሙት። አዲሷ የአውሮጳ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞጌሪኒ እንዳስረዱት፣ ማዕቀብ ብቻውን ለውዝግቡ መፍትሔ ስለማያስገኝ፣ አውሮጳውያኑ ከሞስኮ ጋር ከመነጋገር የወደኋላ ሊሉ አይገባም፤ በዩክሬይን የተጀመረውን ተሀድሶም መደገፍ ሌላው ህብረቱ ሊከተለው የሚገባ አማራጭ መሆን አለበት።

« ይኸው አማራጭ የአውሮጳን ህብረት የዩክሬይን ባለሥልጣናት የሲቭሉን ደህንነት የሚጠብቀውን ተቋማቸውን እንደገና ለማዋቀር የጀመሩትን ተሀድሶ እንዲያግዝ ያስችለዋል። ይኸው ርዳታ እአአ የፊታችን ታህሳስ አንድ ቀን ይጀምራል።»

ዩክሬይን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፓቭሎ ክሊምኪን ሀገራቸውን እያናጋች ባለችው በሩስያ አኳያ ህብረቱ ጠንካራ የማዕቀብ ውሳኔ በመውሰድ ግልጹን ጠንካራ መልዕክት እንዲያስተላልፍ ነበር የጠየቁት።

በምሥራቅ ዩክሬይን በዓማፅያኑ እና በመንግሥቱ መካከል የተኩስ አቁም ቢደረስም እስካሁን የ4,100 ሰዎች ሕይወት ያጠፋው ጦርነት ሰሞኑን እንደገና የቀጠለበት ድርጊት፣ እንዲሁም፣ ሩስያ ወዳካባቢው ወታደሮችዋን እና ላማፅያኑ አሁንም የጦር መሳሪያ ልካለች በሚል የቀረበውን ወቀሳ በዩክሬይን እና በሩስያ መካከል ያለውን ውጥረት አካሮታል።

ባርባራ ቪዝል

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ