1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ጥምር ጦር ምሥረታ እቅድ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 1 2007

በሩስያና በአዉሮጳ ሕብረት መካከል ዉጥረት ባለበት በአሁኑ ወቅት የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ዩንከር፣ አዉሮጳ አቀፍ ጦር ሠራዊት እንዲቋቋም ሐሳብ ማቅረባቸው በአዉሮጳ ሃገራት ፖለቲከኞች ዘንድ ከፍተኛ ዉይይትን ቀስቅሶአል።

https://p.dw.com/p/1EoCk
Deutsch-Französische Brigade
ምስል picture-alliance/AP Photo/W. Rothermel

ዩንከር «ዲ ቬልት » ለተሰኘዉ ጋዜጣ ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ እንደገለፁት የሚመሰረተዉ ጥምር ጦር፤ ወድያዉ ለስምሪት የሚላክ ስይሆን፤ ለጋራና ደሕንነቱ ለተጠበቀ አዉሮጳ የዉስጥና የዉጭ ፖለቲካ የሚቆም፤ አዉሮጳ በዓለም ያላትን ኃላፊነት የሚያረጋገጥ ነዉ ብለዋል። የጀርመንዋ መከላከያ ሚኒስትር ኡርዙላ ፎን ደርላየን የዩንከርን ሐሳብ ሲደግፉ፤ እንግሊዝን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ፖለቲከኞች ሃሳቡን በጥርጣሪ ነዉ የተመለከቱት።

Bosnien EUFOR
ምስል picture-alliance/AP Photo/Hidajet Delic


በዩክሬይን ሳቢያ አዉሮጳ ከሩሲያ ጋር ዉጥረት በገባበት በአሁኑ ወቅት የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ዩንከር፣ አውሮጳ አቀፍ ጦር ሠራዊት እንዲቋቋም የሚል ሐሳብ ማቅረባቸው በዩክሬይኑ ዉጥረት፤ አዉሮጳ የሩስያን አቅዋም እጅግ አደገኛ ሆኖ በማግኘቱ ነዉ። እንደ ዩንከር የአዉሮጳ ጥምር ጦር መመስረት አዉሮጳ እራስዋን ለመከላከል እና ሉዓላዊነትዋን ለመጠበቅ አቅም እንዳላት ለሩስያ ማመላከቻም እንደሆነ ነዉ የገለፁት።
የጀርመን ጥምር መንግሥት የአዉሮጳ ጥምር ጦር ምሥረታን በተመለከተ ያሳለፈዉ ዉሳኔ ባይኖርም ባለፈዉ ጊዜ በጀርመን በተካሄደ የምክር ቤት አባላት ምርጫ በተለይ የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ በጀርመንኛው ምህፃር «SPD» የአዉሮጳ ጥምር ጦር ሠራዊት እንዲቋቋም ያቀረበው ሐሳብ በጥምሩ መንግሥት ዉል ላይም ለመካተት በቅቶአል። የክርስቲያን ዲሞክራሲያዊ ሕብረት«CDU» ፓርቲ መሪ የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልና የመከላከያ ሚንስትርዋ ኡርዙላ ፎን ደርላየን የአዉሮጳ ጥምር ጦር ምስረታንና የትብብር ሥራን ይደግፋሉ። የጀርመንዋ መከላከያ ሚኒስትር ኡርዙላ ፎን ደርላየን አዉሮጳ አቀፍ ጦር ሠራዊት ምስረታን ጥሩ ነዉ ያሉት።
« በዓለም ላይ የሰዉን ልጆች መብትና ብሎም ሰላምን ለማስከበር ቆርጠን መነሳታችንን በግልፅ ለማሳየት አንድ ጠንካራ አዉሮጳ አቀፍ ጦር መመስረቱ ጥሩ ነዉ። »
እንድያም ሆኖ የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም ሆኑ የመከላከያ ሚንስትርዋ ፎንደርላይን የጥምር ጦር ምሥረታ ሃሳቡ «የወደፊት እቅድ» ሲሉ ነዉ ያስቀመጡት። የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ዩንከር የአዉሮጳ አቀፍ ጦር ሠራዊት እንዲቋቋም የሚለዉን ሐሳባቸዉን ከተናገሩ በኋላ በአዉሮጳ ሃገራት በሚገኙ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለያዩ ዉይይቶችና ክርክሮችን ነዉ የቀሰቀሰዉ። የጀርመኑ የግራ ፈለግ ፓርቲ ተጠሪ ክርስቲነ ቡኽሆልትዝ በሰጡት አስተያየት፤
«አቶ ዩንከር፣ በሚገርም ሁኔታ፣ ሰላማዊ መፍትኄም ሆነ ውዝግብ የማብረዱን ተግባር ለመሞከር የተነሣሡት ከበስተጀርባ ሆነው ነው»።
ዣን ክሎድ ዩንከር የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ለመሆን የምረጡኝ ዘመቻ ባደረጉበት ወቅት አዉሮጳ አቀፍ ጦር ሠራዊት እንዲቋቋም የሚል ነጥብን ያነሱ እንደነበር የገለፀዉ የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ፤ ሐሳቡን የሚደግፉም የሚቃወሙም እንዳሉ ይገልፃል።
በአሁኑ ወቅት የአዉሮጳን ደሕንነት የሚያስጠብቅ ከ28ቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባል አገራት የተዉጣጣ ወደ 1,5 ሚሊዮን ጦር ሰራዊት ይገኛል። አዲስ ጦር ሠራዊት ማቋቋሙ እጥፍ የሰዉ ኃይል ብሎም አላስፈላጊ ወጭ እንደሆነ ነዉ የተገለፀዉ። በሌላ በኩል የአዉሮጳ ጥምር ጦር ሠራዊት ማቋቋሙ ለጋራ ኃይል እድገት እንዲሁም በጦር መሳርያ ግዥና አጠቃቀም ላይ የሚወጣውን ወጭ ስለሚቆጥብ ሐሳቡ ድጋፍን ያገኛል። በጥምር ጦሩ እያንዳንዱ ሃገራት በተለያየ ዘርፍ ልዩ ስልጠናን በማድረግ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማበርከትም እንደሚችሉ ተገልፆአል። በሌላ በኩል የአዉሮጳ ሃገራት ረዘም ካሉ ዓመታት ወዲህ በሰላም ስለሚኖሩ ብሔራዊ መከላከያ ጦር የማዋቀሩን ለብዙዎች ትርጉም የለሽ እንደሆነ ነው የተገለፀዉ። አዉሮጳ አቀፍ ጦር ሠራዊት ይቋቋም የሚለዉን ሐሳብ የሚደግፉ እንደሚሉት ጥምሩ ጦር ለአዉሮጳ ትስስርና ኃይል ዋና ምልክት ነው።
የጀርመንዋ የመከላከያ ሚንስትር ኡርዙላ ፎን ደርላየን የአዉሮጳ አቀፍ ጥምር ጦር ምስረታ ሐሳብ የወደፊት የረጅም ጊዜ እቅድ መሆኑን ነዉ የገለፁት፤

«የአዉሮጳ ጦር ሠራዊት፤ የረዥም ጊዜ ዓላማ ሲሆን ፣ ከ NATO ጋር የአንድ ሜዳልያ 2 ገጾች የመሆን እንጂ ፣ እንደኔ እምነት ከቶውንም የሚጻረር አይደለም። አዉሮጳውያን በ NATO ውስጥ አንድ ጠንካራ ዓምድ ሆነው መገኘታቸው ጠቃሚ ሲሆን፤ ራሱን NATO ን አስተማማኝ ለማድረግና የአዉሮጳውያን ድምፅ ጎልቶ እንዲሰማ ለማድረግም፤ የአዉሮጳ ጦር ኃይል መቋቋም የሚበጅ ነው።»
የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ዩንከር የአዉሮጳ ጥምር ጦር የማቋቋም ሐሳባቸዉን ይፋ እንዳደረጉ አዎንታዊ መልስን ያገኙት ከጀርመን እና ከፈረንሳይ መሆኑን ገልጿል።
በጀርመን የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል ፔተር ባርትልስ በበኩላቸው፤ አዉሮጳ አቀፍ ጥምር ጦር መመስረት ካለበት ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት ነዉ የገለፁት።
«አዉሮጳ አቀፍ ጥምር ጦር ወይም የጋራ መከላከያ ጦር መዋቀር ካለበት፤ በተረጋጋ ሁኔታ ቀስ በቀስ ነዉ መካሄድ ያለበት። ምክንያቱም የኔቶ ጦር የአዉሮጳዉ ብርጌድ ነዉና።
እንደ የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ዩንከር አስተሳሰብ፣ የአዉሮጳ ጥምር ጦር ሠራዊት ከኔቶ ጋር ተደጋጋፊ ይሆናል።

አዉሮጳ አቀፍ ጥምር ጦር ምስረታ ሐሳብን በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ፖለቲከኞች ተቃዉመዉታል። በተለይ እንግሊዝ ይህን ሐሳብ በመጀመርያ የተቃወመች ሀገር ናት።

ይህ በአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ዩንከር የቀረበ ሐሳብ ነገ ተነገወድያ ተፈፃሚ የሚሆን ባለመሆኑ መገናኛ ብዙሃንም እንብዛም ያተኮሩበት ርዕስ እንዳልሆነም ተገልፆአል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Deutschland Bundeswehr Übung
ምስል Getty Images/A. Koerner
Deutschland Niederlande Division Schnelle Kräfte
ምስል picture-alliance/dpa/F. Rumpenhorst