1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ኅብረት የምክር ቤት ቅድመ ምርጫ ዉጤት

ሰኞ፣ ግንቦት 18 2006

ጀርመንን ጨምሮ በአውሮጳ ኅብረት 21 አባል ሃገራት ውስጥ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ የተደረገዉ የምክር ቤት ምርጫ ቅድመ-ዉጤት መዘርዝር መዉጣት ጀምሮአል። መጀመሪያ ላይ ይፋ በሆነው ቅድመ-ዉጤት መዘርዝር መሰረት ወግ አጥባቂዎቹ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረትና የክርስትያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ « CDU/CSU» በ36.1 በመቶ እየመራ መሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/1C6eO
EU Parlamentswahl 25.05.2014 Deutschland Merkel
ምስል Reuters

የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ «SPD» በአንፃሩ 27.6 በመቶ ድምፅ እንዳገኘ ነዉ የተመለከተዉ።

በዚህም ጀርመን መራሂተ መንግሥት የሚመሩት የክርስቲያን ሲሞክራቲክ ኅብረትና የክርስትያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ « CDU/CSU» የአዉሮጳ ኅብረት ምክርቤት ምርጫን በመምራት ላይ ነዉ። አረንጓዴዉ ፓርቲ 10.9 በመቶ፤ የግራዎቹ ፓርቲ 7.8 በመቶ ድምፅ ሲያገኙ በአዉሮጳ ኅብረት ላይ ጥርጣሬ ያለዉ ፓርቲ AfD 6.5 በመቶ ድምፅ በማግኘት ግዜ በኅብረቱ ምክር ቤት ለመጀመርያ ግዜ መቀመጫ እንደሚያገኝ ተጠቅሶአል።ከ28ቱ የኅብረቱ አባል ሃገራት የሚገኘዉ አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ከምሽቱ አምስት ሠዓት ጠቅላላ ይፋ እንደሚደረግ ተመልክቷል።

EU Wahl Kandidat Jean-Claude Juncker Stimmabgabe 25. Mai
ምስል picture-alliance/dpa

ቅዳሜ በቼክ ሪፐብሊክ በተካሄደዉ የአዉሮጳ የምክር ቤት ምርጫ ላይ ድምፅ ለመስጠት የመጡ ነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር ፕራግ መዲና የሚገኘዉ መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል። ይኸዉ የአዉሮጳ የምክር ቤት ምርጫ፤ በሌትላንድ በማልታና በስሎቫክያም ተካሂዶ ነበር። አየርላንዶች የምክር ቤት ተወካዮቻቸውን አርብ ዕለት መርጠዋል። ባለፈዉ ሐሙስ በኔዘርላንድ እና በብሪታንያም የአዉሮጳዉ የምክር ቤት ምርጫ ተካሂዷል። የኅብረት አባል ሀገራቱ ከትናንት በስትያ ሐሙስ የጀመሩት የምክር ቤት ምርጫ ዉጤት ነገ ምሽት ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በአዉሮጳ ኅብረት የምክር ቤት ምርጫ ተሳትፎ ላይ ዋነኛዉን ቦታ ይዘዉ የሚገኙት ወግ አጥባቂዎችን እና ሶሻል ዲሞክራቶችን ጨምሮ ቀኝ አክራሪዎች እና በኅብረቱ ጥርጣሬ ያላቸዉ ፓርቲዎችም ይገኙበታል።

በምርጫው አራተኛ ቀን ዛሬ የዴንማርክ፣ የፖርቹጋል እና የስፔን ነዋሪዎችም ድምፅ ሲሰጡ ነዉ የዋሉት። ጀርመን ውስጥ ወደ 64 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች በምክር ቤቱ ለሚወክሏቸው 96 ተመራጮች ድምፅ ሲሰጡ ዉለዋል። የቅድመ-ምርጫ መጠይቆች እንደሚያመለክቱት የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ ኅብረት በአውሮጳ ምክር ቤት ከፍተኛ ድምፅ ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል ተብሏል። የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ እጎአ በ2009 ከተካሄደው ምርጫ በተሻለ ድምፅ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተገምቷል።በአውሮጳ ኅብረት ለምክር ቤት ምርጫ በ28ቱ የኅብረቱ አባል ሃገራት ውስጥ ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች መካከል የሚወክሏቸውን 751 የምክር ቤት አባላት ይመርጣሉ ተብሎ ተጠብቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የጀርመን ዜግነት የሌላቸው የውጭ ሃገራት ነዋሪዎችም በጀርመን የውጭ ሃገራት ውህደት የምክር ቤት አባላት ተወካዮቻቸውን በዛሬው ዕለት ሲመርጡ ውለዋል።

EU Parlamentswahl 25.05.2014 Deutschland SPD Schulz Berlin
ምስል Reuters

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶ ስለሺ