1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ሀገራት የሙዚቃ ዉድድር

ዓርብ፣ ግንቦት 15 2006

ባለፉት ሳምንታት ለ 59ኛ ግዜ የተካሄደዉ፤ የአዉሮጳ ሀገሮች የሙዚቃ ዉድድር መድረክ፤ ደማቅ በሆነ የሙዚቃ ዉድድር የኦስትርያዉ ከያኒ 290 ነጥብን በማግኘት፤ እስከ ዛሪ በዉድድሩ ከተመዘገቡ የአሸናፊነት ነጥብ በአብላጫነት፤ የአራተኛ ደረጃን መያዙ ተነግሮለታል።

https://p.dw.com/p/1C4ZN
Eurovision Song Contest 2014
ምስል picture-alliance/dpa

የአዉሮጳ ሀገሮች የሙዚቃ ዉድድር« ኦይሮቪዥን ሶንግ ኮንቴክስት» የሩብ እና የግማሽ ፍፃሜ ማጣርያ ዉድድር፤ ከተደረገ በኃላ ግንቦት ሁለት ቀን ቅዳሜ ምሽት 26 የተለያዩ አዉሮጳ ሀገራት፤ የተወዳደሩበት፤ በዓለም የተለያዩ ሀገሮች በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት የተከታተሉት ዉድድር እጅግ ደማቅ ነበር። ዘንድሮ ለ 59 ዘጠነኛ ግዜ የተዘጋጀዉን ዉድድር አሸናፊ ኦስትርያ ስትሆን፤ ኦስትርያ በጎርጎረሳዉያኑ 1966 ዓ,ም፤ ከዛሬ 48 ዓመት በፊት፤ በዚሁ በአዉሮጳ ሀገሮች የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ፤ለመጀመርያ ግዜ አሸናፊ የነበረች ይታወቃል።

Conchita Wurst gewinnt Eurovision Song Contest 2014
የኦስትርያዉ አሸናፊምስል picture-alliance/dpa

«ኮንቺታ ቮርስት» በሚል የመድረክ ስሙ የሚጠራዉ፤ የ25 ዓመቱ ኦስትርያዊ፤ ቶም ኖይቪርት አሸናፊ ያደረገዉን ሙዚቃዉን ለማቀንቀን መድረክ ላይ የቀረበዉ፤ ረጅም ፀጉሩን በጀርባዉ ላይ ለቆ፤ ሙሉ ፂሙን አሳድጎ እና፤ እስከ እግር ጥፍሩ የሚደርስ ግሩም ረጅም ቀሚስን አጥልቆ ነበር። በርግጥ ባቀረበዉ ሙዚቃ በርካታ ነጥቦችን አግኝቶ፤ የዘንድሮዉ ዉድድር አሸናፊ ቢሆንም፤ ብዙዎች በአለባበሱ እና በመድረክ አቀራረቡ ነቀፊታን ጥለዉበታል። የኦስትርያዉ ከያኒ በርካታ ነቀፌታ ቢጣልበትም፤ በአንፃሩ አንድ ሰዉ የሰዉን መብት እስካልነካ እና ጉዳት እስካላደረሰ ድረስ፤ በዚች ምድር ላይ እንደፈለገዉ መሆን ይችላል፤ ሲሉ በርካታ ምዕራባዉያን ሀገሮች ደግፈዉታል። ከዩኤስ አሜሪካም እንዲሁ አንዳንድ ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎች በመድረክ አቀራረቡ አወድሰዉታል። በመድረክ መጠርያ «ኮንችታ ቮርስት» እንደ አለባበስዋ ሁሉ በሴት ነበር የምትጠራዉ፤ የሩስያ ደጋፊዎችና ሩስያ ትዉልድ እንዳይቀጥል፤ በትዉልድ ላይ የሚደረግ ኢ-ሰብዓዊ ስነ-ምግባር ያልያዘ ስትል፤ የኦስትርያዉን ከያኒ ነቅፋለች። እንዲያም ሆኖ በአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር ላይ በተለይ ከፍተኛ ነጥብ ያገኙትና ሙዚቃቸዉ የተወደደላቸዉ የኔዘርላንድ እና የስዊድን ከያኒዎችን በነጥብ በመብለጥ የሴት ቀሚስ ለብሶ መድረክ የቀረበዉ፤ የኦስትርያ ከያኒ አሸናፊ ሆንዋል። አሸናፊዉ ማን እንደሆነ እንታወቀ እና፤ የመድረኩ አስተናጋጅ እንኳን ደስ አለሽ፤ ኮንቺታ ለዚህ ክስተት፤ አሁን ልትናገር የምትችልበት አንደበት ይኖርሃል ተብሎ ሲጠየቅ፤ «የዛሬዉ ምሽት መታሰብያነቱ ሰላም እና ነፃነት እንዲመጣ ለሚያምኙ ሁሉ ነዉ» ሲል ነበር መልስ የሰጠዉ።

የአዉሮጳ ሀገሮች የሙዚቃ ዉድድር መድረክ አሸናፊ ወደ ሰማንያ ሽህ ይሮ እንደሚያገኝ ሲገለጽ በሌላ በኩል አሸናፊዉ የተለያዩ የአዉሮጻ ሀገሮች የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎችን በማቅረብ በተለያዩ የብዙሃን መገናኛዎች በመቅረብ እና ቃለ መጠይ በማድረግ እንዲሁም ራስን በማስተዋወቅ የሙዚቃ ስራቸዉን በመሸጥ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያገኙ ተገልጾአል። የኦስትርያዉ ከያኒም በመጀመርያ ወደ ጀርመን በመጋበዝ፤ በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣብያዎች በቅረብ ራሱን አስተዋዉቋል፤ በስሙ የምግብ ሸቀጥ ምልክት እስከ መሆን ደርሶአል። «ይሮቪዥን ሶንግ ኮንቴክስት» የተሰኘዉ በየዓመቱ በአንድ አሸናፊ ሀገር የሚካሄደዉ የአዉሮጳዉ ሙዚቃ ዉድድር መድረክ፤ አዉሮጳዉያን የዕርስ በርስ ጦርነትን አቁመዉ ለጋራ መተሳሰር እና መግባባት እንዲሁም በመደጋገፍ የጀመሩት ያጋራ መድረክ እንደሆነ፤ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የአዉሮጳዉ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ፤ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀ፤ በአስራ ሁለተኛ ዓመቱ፤ እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር 1956 ዓ,ም፤ «የአዉሮጳ የራድዮ ስርጭት ማህበር» ለመጀመርያ ግዜ ያቋቋመዉ፤ የሙዚቃ ዉድድር እንደሆነም ተዘግቦአል። ነገሩ የአዉሮጳዉያን የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ተሰኘ እንጂ፤ አዉሮጳ ድንበር ክልል ዉስጥ የማይገኙ፤ የራድዮ ማህበሩ አባል ሀገሮች ሁሉ የሚሳተፉበት ነዉ። የማህበሩ አባላት ደግሞ እስራኤልን፤ የእስያ ሀገሮችን ብሎም የሰሜን አፍሪቃ ሀገራትንም ሁሉ ያጠቃልል። እስከ ዛሪ በዚህ ዉድድር፤ ከአፍሪቃ ሞሮኮ እንደ ጎርጎረሳዊዉ አቆጣጠር በ1980 ዓ.ም፤ በዚህ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ተሳትፋለች። በአዉሮጳዉ የራድዩ ስርጭት ማህበር ዉስጥ፤ አባል የሆኑና፤ በዚህ የሙዚቃ ዉድድር እስከ ዛሪ ያልተሳተፉ ሀገሮች ደግሞ፤ አልጀርያ፤ ቱኒዚያ፤ ሊቢያ፤ ግብጽ፤ ዮርዳኖስ እና ሊባኖን ይገኙበታል። የአዉሮጳ የራድዩ ስርጭት ማኅበር አባላት በአጠቃላይ ሰባ አምስት ሲሆኑ፤ ሃምሳ ስድስቱ አዉሮጳ ዉስጥ የሚገኙ ናቸዉ። ቀሪዎቹ አስራ ዘጠኝ ሀገራት ደግሞ ሰሜን አፍሪቃ እና እስያ ዉስጥ የሚገኙ ሀገሮች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ዘንድሮ ለ 59ኛ ግዜ የተካሄደዉ የአዉሮጻዉ የሙዚቃ ዉድድር አዘጋጅ የሆነችዉ ዴንማርክ፤ ባለፈዉ የአዉሮጳዉያኑ ዓመት ስዊድን ከተማ ማሌሞ ላይ የተዘጋጀዉ ዉድድር አሸናፊ በመሆንዋ ነበር ፤ ዘንድሮ አዘጋጅ ለመሆን የበቃችዉ።

Conchita Wurst gewinnt Eurovision Song Contest 2014
የኦስትርያዉ አሸናፊምስል Reuters

ያደመጣችኋቸዉ «ቶልማቺቭ ሲስተርስ» የተሰኙት ሁለት አንድ አይነት ልብስና አንድ አይነት ፀጉር ስራ ተሰርተዉ መንትያ መስለዉ የቀረቡት የሩስያ ከያኒዎች ነበሩ ። በዉድድሩ ሩስያ ሰባተኛ ደረጃን አግኝታለች። በዘንድሮዉ የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር ላይ የማኅበሩ አባል ሀገራት የሆኑት ሞንቴኔግሮ እና ሳን ማሪኖ የማጣርያ ዉድድርን አልፈዉ ለፍጻሜ ዉድድሩ ለመጀመርያ ግዜ መሳተፋቸዉ ተገልፆአል። ከኔዘርላንድ የመጡት ከያኒዎች በዉድድር መድረኩ ላይ ባቀረቡት ሙዚቃ እጅግ ከፍተኛ አድናቆትና ዉጤትን ቢያመጡም፤ የመጀመርያዉ ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን በቂ ነጥብ አላገኙም።

«ይሮቪዥን ሶንግ ኮንቴክስት» በተሰኘዉ በዘንድሮዉ አዉሮጳ ሀገራት የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ላይ፤ ሀገራት ለዉድድር ይዘዉ የሚቀርቡት ሙዚቃ፤ ከሶስት ደቂቃ ያልበለጠ መሆን ይኖርበታል። በዘንድሮዉ ዉድድር ኦስትርያ፤ ኔዘርላንድ፤ስዊድን ከአንድኛ እስከ ሶስተኛ ነጥብን ሲያገኙ፤ ጀርመን በዉድድሩ 18 ኛ ደረጃን ነዉ ያገኘችዉ። በዉድድሩ፤ ለግማሽ እና ለሩብ ፍፃሜ አልፈዉ ለደረጃ በዉድድሩ ከቀረቡት ሃያ ስድስት ሀገራት መካከል ፈረንሳይ፤ የመጨረሻዉን ማለትም የሃያ ስድስተኛን ቦታ ነበር ያገኘችዉ ። ኤሊዛ የሚል የቡድን ሥም ያላቸዉ ጀርመንን ወክለዉ የቀረቡት ሶስት ወጣት ሴቶች ምንም እንኳ በዉድድሩ 18 ኛ ነጥብን ይዘዉ ከኮፐን ሃገን ይመለሱ እንጂ፤ በጀርመን ሃገር ሙዚቃቸዉ ተወዳጅነትን አትርፎአል።

Eurovision Song Contest 2014 Russland
የሩስያ ተወዳዳሪዎችምስል picture-alliance/dpa

ጀርመን የአዉሮጳዉ የሙዚቃ ዉድድር ማለትም የ «ይሮቪዥን ሶንግ ኮንቴክስት» ከተጀመረበት ከጎርጎረሳዉያኑ 1956 ዓ,ም ጀምሮ፤ በየዓመቱ ለፍጻሜ ዉድድር የቀረበች ሲሆን፤ በነዚህ የዉድድር ዓመታት ዉስጥ፤ 18 ሀገራት በተሳተፉበት በጎርጎረሳዉያኑ 1982 ዓ,ም፤ 161 ነጥብን በማምጣት፤ እንዲሁም በቅርቡ በጎርጎረሳዊዉ 2010 ዓ,ም፤ ኖርዊ ኦስሎ መዲና ላይ በተካሄደዉና፤ 25 ሀገራት ለነጥብ ዉድድር በቀረቡበት፤ የሙዚቃ ድግስ ላይ፤ አንደኛ መዉጣትዋ ይታወሳል።

ይህ ግዙፍ የሙዚቃ የዉድድር መድረክ፤ በቀጥታ የቴሌቭዥን ሥርጭት በበርካታ አዉሮጳ፤ እስያ እንዲሁም ሩቅ ምስራቅ ሀገራት የሚተላለፍ ሲሆን፤ ተወዳዳሬዎቹ ሀገራት ሙዚቃቸዉን ካቀረቡ በኃላ፤ የየሀገራቱ ተወካዮች፤ ከየሀገራቸዉ ዉድድሩ ወደ ተዘጋጀበት ሀገር፤በመደወል ለሶስት ሀገራት ነጥብ ከሰጡ በኃላ ነዉ የዉድድሩ አሸናፊ የሚለየዉ። ስልክ ደዉለዉ ለኛ ጥሩ ያሉትን ሙዚቃ ሲመርጡ ታድያ፤ የምዕራብ አዉሮጳ ሀገራትም ሆነ የምሥራቅ አዉሮጳ ሀገራት፤ ለየጎረቤት ሀገራት፤ አልያም አጋር ላሉት ሀገር ነጥብ የመስጠቱ እና የመጠቃቀሙ ሁኔታ፤ በዝቶ ባይታይም ይስተዋላል። መድረኩ ከመጠቃቀም ባሻገር የፖለቲካ መድረክም እየሆነ መምጣቱን፤ አንዳንድ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ባለፈዉ በቀረበዉ ዝግጅት ላይ የሴት ልብስን ለብሶ፤ ፀጉሩን ጀርባዉ ላይ ለቆና ጢሙን አሳድጎ መድረክ ወጥቶ ያቀነቀነዉ ሙዚቀኛ፤ «ግብረሰዶማዊነት ከሰው ልጆች ተፈጥሮ ውጭ» ስትል በጥብቅ ለምትቃወመዉ ሩስያ እና መሰሎችዋ፤ ግብረሰዶም ደጋፊዎች አቋማቸዉን ያሳዩበት መድረክ ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሰጡ ጥቂቶች አይደሉም።

በጎርጎረሳዉያኑ 1956 አ.ም ለመጀመርያ ግዜ በኦስትርያ ሉጋኖ ዉስጥ የተካሄደዉ ይህ የአዉሮጻ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ በዓለም ዙርያ ተወዳጅ የሆኑ ሙዚቀኞችን አፍርቶአል። ታዋቂዋ የፖፕ የሙዚቃ ተጫዋች ሴሊን ዲዮን የአዉሮጳዉ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ለሰላሳ ሶስተኛ ግዜ ባቀረበዉ የዉድድር ስዊዘርላንድን ወክላ ዉድድሩ ላይ ባቀረበችዉ የፈረንሳይኛ ሙዚቃ ታዋቂነትን አትርፋ በዓለም የሙዚቃ መድረክ ኮከብ ለመሆን መብቃትዋ ይታወቃል። « አባ » በመባል የሚታወቁት የስዊድን የፖፕ ሙዚቃ ባንድ አባላትም፤ በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ1974 ዓ.ም፤ «ዋተር ሉ» የተሰኘዉን ሙዚቃጨዉን ይዘዉ በዉድድሩ መድረክ ከቀረቡ በኃላ፤ በታዋቂነት ዓለም እንዲገቡና እንዲወደዱ፤ ብሎም 380 ሚሊዮን አልብምን በመሸጥ በፖፕ ሙዚቃ ዓለም በዓለማችን የመጀመርያዎቹ ለመሆን በቅተዋል።

Elaiza / ESC / Vorentscheid
የጀርመን ተወዳዳሪዎችምስል picture-alliance/dpa

26 ሀገራት የተሳተፉበትን የዘንድሮዉን የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ በጥቂቱ የቃኘንበት መሰናዶ እስከዚሁ ነበር። በሚቀጥለዉ ዓመት አዘጋጅ የሆነችዉ የዘንድሮ ዉድድር አሸናፊ ሀገር ኦስትርያ ላይ የሚካሄደዉን 60ኛዉን የአዉሮጳ ሀገራት የሙዚቃ ዉድድር ለማየት ያብቃን። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ