1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሩሻው ስምምነት እና የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ትፅቢት

ቅዳሜ፣ ጥር 16 2007

የደቡብ ሱዳን ገዢ ፓርቲ ፣ የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ፣ «ኤስ ፒ ኤል ኤም» ተቀናቃኝ አንጃዎች ባለፈው ረቡዕ የሥልጣን መጋራት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ይኸው በገዢ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ለማብቃት እንደሚረዳ የሀገሪቱ ሕዝብ ተስፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/1EPnr
Jubel nach Rückkehr von Salva Kiir
ምስል picture-alliance/dpa/Dhil

ይኸው በታንዛንያ ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ ሸምጋይነት በአሩሻ ታንዛንያ በተካሄደው ድርድር ሰሞኑን የተደረሰው ስምምነት የተከፋፈለውን የደቡብ ሱዳን ገዢ ፓርቲ አንድ ያደርጋል የሚል ተስፋ ፈንጥቋል። ከዚህ በተጨማሪም በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል የተጀመሩት ሌሎች ድርድሮችን ሂደት ወደፊት ሊያራምድ እንደሚችልም አደራዳሪዎች እና የሲቭሉ ማህበረሰብ ተስፋውን ገልጾዋል።
የአሩሻ፣ ታንዛንያው ስምምነት በደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ላይ ወሳኝ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል። የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ፣ «ኤስ ፒ ኤል ኤም» ተቀናቃኝ አንጃዎች እንደገና ባንድነት ለመስራት ተስማምተዋል።
ይኸው ዜና በርስበርሱ ጦርነት በተዳቀቀችው የደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ትልቅ ደስታ መፍጠሩን የደቡብ ሱዳን ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ሞይጋ ኮሮኮቱ ንዱሩ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።
« በተለያዩት የገዢው ፓርቲ፥ «ኤስ ፒ ኤል ኤም» አንጃዎች መካከል የተደረሰው ስምምነት በጁባ ትልቅ ደስታ አስከትሎዋል። ሕዝቡ ስምምነቱ ለደቡብ ሱዳን ውዝግብ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚያስችል ተጨማሪ ርምጃ እንዲሆን ይጠብቃል። »
ከረጅም የብረት ትግል በኋላ እአአ በ2011 ዓም ነፃነቷን ባገኘችው ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተቀናቃኞቹ ወገኖች ጎሳዎች መካከል ውጊያ የፈነዳው ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር የቀድሞ ምክትላቸውን ሪየክ ማቸርን መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሢረዋል በሚል በመውቀስ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ከሥልጣን ባባረሩበት ታህሳስ 2013 ዓም ነበር።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ወደ ሁለተኛ ዓመቱ የተሸጋገረውን የሀገራቸውን ውዝግብ በማብቃቱ ረገድ ከጎረቤት ታንዛንያ ድጋፍ መጠየቃቸውን የታንዛንያ ፕሬዚደንት ኪክዌቴ ቃል አቀባይ ሳልቫቶሪ ርዌዬማሙ እንዳስታወቁት አረጋግጠዋል።
« ኪር ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ እንዲረዱዋቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነበር መልዕክት ያስተላለፉት። »
በታንዛንያ አስተናጋጅነት እና የተለያዩ ያካባቢ ሀገራት መሪዎች በተሳተፉበት ድርድር የተገኘው አበረታቺ ርምጃ መሆኑ መሆኑ የሚነገርለት ይኸው ስምምነት ለወደፊቱ በተቀናቃኞቹ አንጃዎች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ የሚቻልበትን ዘዴ ያጠቃለለ ነው። ይህም ካሁን ቀደም ከተደረሱት ሌሎች ስምምነቶች ሁሉ የተለየ እንደሚያደርገው የቀድሞው የሰመድ የሱዳን ልዑክ ፒተር ሹማን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።
« ትልቁ ልዩነት ይኸው ስምምነት «ኤስ ፒ ኤል ኤም» ን እንደገና አንድ ለማድረግ በሚቻልበት ጥረት ላይ ማትኮሩ ይመስለኛል። ስምምነቱ የፓርቲው ተቋማዊ አሰራር እንዲንኮታኮት እና ታህሳስ 15፣ 2013 ዓም የኃይል ተግባር እንዲነሳ ያደረጉትን ሁኔታዎች አንድ ባንድ መርምሮዋል። ይሁንና፣ ለነዚህ ለዘረዘራቸው ችግሮች የመፍትሔ ሀሳብ አላቀረበም። »
ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር፣ ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቸር እና የአንድ ሌላ ተገንጣይ አንጃ መሪ ዴንግ አሎር ኩዎል የአሩሻውን ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ አደራዳሪዎቹ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ባካሄዱት የሥልጣን ሽኩቻ አኳያ ብርቱ ነቀፌታ ሰንዝረዋል። የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የርስበርሱን ጦርነት አላስፈላጊ እና አሳዛኝ ክስተት ሲሉ ገልጸውታል።
« የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ካላንዳች የረባ ምክንያት በጣም ተሰቃይቶዋል። ይህ ባጣም አሳዛኝ ክስተት ነው። »
የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታም ተቀናቃኞቹ ባለሥልጣናት ለሕዝባቸው ፍላጎት እንዲገዙ አሳስበዋል።
« ውጊያው የሚያበቃበት ጊዜ አሁን ነው። እና፣ እንደ ሀገር መሪዎች፣ አሁን፣ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ እንደሚጠብቅባችሁ፣ የጣለባችሁን ኃላፊነት ማሟላት ይኖርባችኋል። ሕዝቡ ከናንተ የተሻለ ኑሮ፣ መረጋጋት፣ ብልፅግና እና ልማት እንድታስገኙለት ጠብቋል። ውጊያ፣ ፍርሀት እና ሞትን አልነበረም የጠበቀው። በመሆኑም፣ የዛሬው ዕለት አዲስ ጅምር እንደሚያስገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። »
ተቀናቃኞቹ የፓርቲ አንጃዎች የሚወዛገቡበትን ዋነኛ ጉዳይ፣ ብሎም፣ ሥልጣን ሊጋሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ስምምነት ግን በዚሁ ረገድ ዝርዝር ሀሳብ አላቀረበም፣ ይህ ተጓድሎ የሚገኝበት ሁኔታም፣ እንደ የቀድሞው የሰመድ የሱዳን ልዑክ ፒተር ሹማን ለዶይቸ ቬለ ግምት፣ የስምምነቱን መሳካት አጠራጣሪ አድርጎታል።
« ስምምነቱ መደረሱ ወሳኝ ርምጃ ይመስለኛል፣ ግን፣ በጣም ንዑስ ርምጃ ነው። ሶስቱ ተፈራራሚ ቡድኖች ወደፊት ዓበይት ውሳኔዎች መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ያለፉ ተሞክሮዎችን መለስ ብየ ስመለከት፣ አንዱም ቡድን ሥልጣኑን በፈቃደኝነት ለመልቀቅ የሚፈልግ አይመስለኝም። በድርድሩ ወቅት ሁሉ ጎልቶ የተሰማው ሀሳብ «ኤስ ፒ ኤል ኤም» የደቡብ ሱዳን ሬፓብሊክ መንግሥት ሆኖ በሥልጣን ይቆያል የሚለው ነበር። ውሉን የፈረሙት የአንጃ ተወካዮች ወደፊትም ከ«ኤስ ፒ ኤል ኤም» ሌላ ቡድን ሥልጣን ይይዛል የሚል እምነት የላቸውም። እና ይህ እኛ በሥልጣን ላይ መቆየት አለብን የሚለውን አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ወይም አስተሳሰብ ነው። »
በሥልጣን መጋራቱ ድርድር ወቅት ፕሬዚደንት ኪርም ሆኑ ሪየክ ማቸር ግልጽ ገላጋይ ሀሳብ አላመላከቱም፣ ፕሬዚደንት ኪር ስምምነቱ ሊፈረም ጥቂት ቀናት ሲቀረው በሰጡት አንድ መግለጫ ከሥልጣን የመውረድ ሀሳብ እንደሌላቸው ሲያስታውቁ፣ አዲሱም ስምምነት ይህንኑ ዕቅዳቸውን አጠናክሮዋል። የሥልጣን መጋራቱ ስምምነት መሳካት እንግዲህ በገዢው ፓርቲ ማዕከላይ ጽሕፈት ቤት አዲስ አወቃቀር እና ወደፊት በሚኖረው ሥልጣን ላይ ጥገኛ ይሆናል።
የአሩሻው ስምምነት የተኩስ አቁም ደንብ ወይም የመጨረሻውን የሰላም ስምምነት በማስገኘቱ ጉዳይ ላይ አለማትኮሩ ቢታወቅም፣ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ በምሕፃሩ በኢጋድ ሸምጋይነት ለተጀመረው እና በዚህ ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ቀጣይ የድርድር ዙር ወደፊት እንደሚያራምድ የታንዛንያ ፕሬዚደንት ኪክዌቴ ቃል አቀባይ ሳልቫቶሪ ርዌዬማሙ ገምተዋል።
« የአሩሻው ስምምነት ለቀጣዩ ድርድር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ይመስለኛል። የመጪዎቹን ድርድሮች መሠረት ይጥላል። »
ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቸር እአአ ባለፈው ህዳር 2014 ዓም በአዲስ አበባ ተገናኝተው የተኩስ አቁም ደንብ ቢፈራረሙም ፣ ድንቡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እንደገና መጣሱ የሚታወስ ነው። የአሩሻው ድርድር እየተካሄደ በነበረበትም ጊዜ ውስጥ በመንግሥት ወታደሮች እና ሪየክ ማቸርን በሚደግፉ ዓማፅያን መካከል ከባድ ውጊያ ተካሂዶዋል።
በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማው,ረድ ቀጣይ ጥረት መደረግ እንደሚኖርበት የሲቭሉን ማህበረሰብ የሚመሩት ቄስ ፒተር ቲቢ አስታውቀዋል።
« ሰላም በሂደት የሚገኝ ነው። ብዙ መሰራት ያለበት ይመስለኛል። የፖለቲካ መሪዎቹ ሊስማሙ ይችሉ ይሆናል፣ ስምምነቱ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የሚወዛገቡትን የተለያዩትን የሲቭል ማህበረሰቦች ማጠቃለል ይኖርበታል። »
የደቡብ ሱዳን ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ሞይጋ ኮሮኮቱ ንዱሩም የሀገራቸው የፖለቲካ መሪዎች ይህንኑ የሰላም ሂደት የማራመድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
« ፖለቲከኞቹ የሰላሙን ሂደት ወደፊት ከማራመድ ያለፈ ሌላ አማራጭ የላቸውም። ምክንያቱም፣ በየተኛውም የደቡብ ሱዳን አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ የሰላም ያለህ እያለ ነው። ሕዝቡ ጦርነቱን ማንም ያልፈለገው እና ትርጉም አልባ አድርጎ ነው የተመለከተው።»
በደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺህ የሚቆጠር ሰው ሲገደል፣ ሁለት ሚልዮን የሚሆን ደግሞ ከመኖሪያ ቀየው ተፈናቅሎዋል ወይም ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰዷል።

Bruch der Waffenruhe im Südsudan 26.01.2014
ምስል Reuters
Südsudan Flüchtlingslager in Bor
ምስል Reuters
Salva Kiir und Riek Machar unterzeichnen Abkommen
ምስል AFP/Getty Images

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ