1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአል ሸባብ ዛቻና የአሜሪካኖች ሥጋት

ማክሰኞ፣ የካቲት 17 2007

ከCNN እስከ FOX የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ትላልቅ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሰሞኑን እየተቀባበሉ ያራገቡት አዲሱ የአሸባብ ዛቻ-ሚኒሶታን ናይሮቢ-ሞል ኦፍ አሜሪካን-ዌስት ጌት ያደርጋቸዋል የሚል ሥጋት አሳዳሯል።የሥልታዊ እና የዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ ሪቻርድ ዶዉኔ ግን ዛቻዉ አያሰጋቸዉም

https://p.dw.com/p/1EgeP
ምስል picture-alliance/dpa7AP Photo/Star Tribune/Jerry Holt

የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ሰሜን አሜሪካ እና አዉሮጳ የሚገኙ የገበያ አዳራሾችን ለማጥቃት መዛቱ የአሜሪካ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ተንታኞችን እያነጋገረ ነዉ።ቡድኑ በቅርቡ ባሠራጨዉ የቪዲዮ መልዕክት ሚኒሶታ-ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉን Mall of America የተሰኘዉንና ካናዳና ብሪታንያ የሚገኙ ሌሎች የገበያ አዳራሾችን እንደሚያጋይ ዝቷል።ዛቻዉ ከተሰማ ወዲሕ ዩናይትድ ስቴትስ ለትላልቅ የገበያ አዳራሾች የሚደረገዉን ጥበቃ አጠናክራለች።አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች ዛቻዉን «ትርጉም የለሽ» በማለት ሲያጣጥሉት ሌሎች ግን «አስፈሪ» ይሉታል።

«ዌስት ጌት የመጀመሪያዉ ነዉ» ብሎ ይጀምራል የአሸባብ የሽብር ዛቻ-የቪዲዮ መግለጫ።በርግጥም አሸባብ ዌስት ጌት በተባለዉ የናይሮቢ-የገበያ አዳራሽ መስከረም 2006 ያደረሰዉ ጥፋት፤ ጥቃትና ጥፋቱን ከተከታተሉ ወገኞች አዕምሮ ገና አልጠፋም።67 ሰዎች ተገድለዋል።መቶዎች ቆስለዋል።ከCNN እስከ FOX የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ትላልቅ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሰሞኑን እየተቀባበሉ ያራገቡት አዲሱ የአሸባብ ዛቻ-ሚኒሶታን ናይሮቢ-ሞል ኦፍ አሜሪካን-ዌስት ጌት ያደርጋቸዋል የሚል ሥጋት አሳዳሯል።የሥልታዊ እና የዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ ሪቻርድ ዶዉኔ ግን ዛቻዉ አያሰጋቸዉም

«አሸባብ ከሚንቀሳቀስበት አካባቢ ያን ያሕል በሚርቅ ሥፍራ አደጋ ለመጠል ከፍተኛ የሆነ የአቅም ጥንክሬ ያስፈልገዋል።የቅርቡ አዉነታ የሚያመለክተዉ ግን አሸባብ ከመጠናከር ይልቅ መዳከሙን የሚያረግግጥ ነዉ።»

al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል picture alliance/AP Photo/Sheikh Nor

የዩናይትድ ስቴትሱ ብሔራዊ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሴሊና ሪልዩዮ ግን ተቃራኒዉን ነዉ የሚሉት።በፕሮፌስሯ እምነት አሸባብ አሜሪካን ለማጥቃት ተዋጊዎቹን አሜሪካ ድረስ ማዝመት አያስፈልገዉም።

«በመሠረቱ ቡድኑ ተዋጊዎቹን ወደ ዩናይትድ ስቴት ማዝመት ባይሳነዉም፤ ማዝመት ግን አያስፈልገዉም። የሚያሰጋን በቪድዮዎችና በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያደርጉት ቅስቀሳ እዚሕ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ እና ወትሮም ልባቸዉ የሚዋልል ሰዎች «ለስላሳ ኢላማ» የሚባሉትን እንዲያጠቁ ማደፋፈር መቻላቸዉ ነዉ።Mall of America ደግሞ ለአሸባብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ላላቸዉ አሸባሪ ቡድናት ትልቅ ኢላማ መሆኑ ግልፅ ነዉ።»

አሸባብ ሊያጋየዉ የዛተዉ ዝነኛዉ የገበያ አዳራሽ በሚገኝበት በሚኖሶታ ፌደራዊ ግዛት በርካታ ሶማሌዎችና የሶማሊያ ዝርያ ያላቸዉ ይኖራሉ።በይፋ የሚታወቀዉ ቁጥር 35 ሺሕ ተብሎ ነዉ።የአካቢዉ ባለሥልጣናትና መገናኛ ዘዴዎች ግን የሶማሌዉ ማሕበረሰብ እስከ ሰማንያ ሺሕ እንደሚደርስ ይናገራሉ።ፕሮፌሰር ሪልዩዮ እንደሚሉት ከነዚሕ የሶማሊያ ማሕበረሰብ አባላት መሐል በአሜሪካዉ ሥርዓት ያልረኩ፤ ወይም የተበሳጩ ከአሸባብ ወጥመድ በቀላሉ ይገባሉ።

«የሚያስፈራዉ ከአሜሪካ የአኗኗር ይትበሐል ጋር በቅጡ ያልተቀየጡ የሁለተኛዉ ትዉልድ አባላት ናቸዉ።እነዚሕ ፤ከአሜሪካ ማሕበራዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊ እና ፖለቲካዊዉ ሥርዓት ጋር ያልተዋሐዱ ወጣቶች በቀላሉ በአሸባብ ሊመለመሉ ይችላሉ።»

የዩናይትድ ስቴትስ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ጄሕ ጆንሰንና የፌደራላዊ የምርመራ ቢሮ (FBI) ባለሥልጣናት ለሞል ኦፍ አሜሪካ የሚደረገዉ ጥበቃ እንዲጠናከር አዘዋል።ይሁንና ሁለቱም መሥሪያ ቤቶች በተጨባጭ አደጋ ይጣላል የሚል ልዩ ማስጠንቀቂያ አልሰጡም።የሥልታዊና የዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ባልደረባ ሪቻርድ ዶዉኔም የአሸባብ ዛቻ ቡድኑ መዳከሙን ከመጠቆም አልፎ አሜሪካን የሚያሰጋ አይደለም ባይ ናቸዉ።

Selbstmordanschlag in Mogadischu
ምስል picture-alliance/dpa

«እንደሚመስለኝ በቅርቡ የተሠራጨዉን ቪዲዮ ብትመለከተዉ መልዕክቱ ተስፋ የመቆረጥ ጥሪ ነዉ።ቪዲዮዩን የሚመለከቱ ሰዎችን ለመመልመል የሚቃጣ ነዉ።ሥለዚሕ የሆነ ነገር ከመጠበቅ ይልቅ እንዲያዉ ተስፋ ነዉ-መልዕከቱ።»

አሸባብ፤ የአፍሪቃ ሕብረት፤ የሶማሊያ መንግሥትና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በጋራና በተከታታይ በከፈቱበት ጥቃት ተዳክሟል።የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ዶሮን በተባለ ሰዉ አልባ አዉሮፕላን በተደጋጋሚ ባደረሰዉ ድብደባ የቀድሞ መሪዉን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናቱን ገድሎበታል።ይሁንና ቡድኑ አሁን አሜሪካካንን ለማጥቃት የመዛቱ አንዱ ምክንያቱም ይኸዉ ነዉ።ያዳከመዉን የመሪዎቹን መገደልና ደም መበቀል።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ