1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተተቸው የፓኪስታን ጸረ-ሽብር ዕቅድ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8 2007

በፓኪስታን የታሊባን ታጣቂዎች በጅምላ ከገደላቸው ከገደሏቸው 141 ሰዎች መኻከል አብዛኞቹ ተማሪ ልጆች እንደነበሩ ተዘግቧል። ጥቃቱ የተፈፀመው ማክሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2007 ዓም የኪቤር ፓክቱንክህዋ ግዛት መዲና በሆነችው ፔሻዋር ውስጥ በሚገኝ አንድ የወታደር ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር።

https://p.dw.com/p/1E6AB
ምስል Reuters/K. Parvez

ቴኅሪቅ ኤ ታሊባን በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ TTP የተሰኘ ቡድን ኃላፊነት መውሰዱን ተናግሯል። ቡድኑ ጥቃቱን ያከናወነው የፓኪስታን ጦር በአፍጋኒስታን ድንበር አቅራቢያ በተደጋጋሚ አድርሶታል ያለውን ጥቃት ለመበቀል እንደሆነ አስታውቋል። ጥቃቱን ከዚያው ከፓኪስታንም ከውጪም የተለያዩ ወገኖች አውግዘውታል። የፓኪስታን ታዋቂ የክሪኬት ተጨዋች የነበረው እና አሁን ፖለቲከኛ የሆነው ኢምራን ካሕን አንዱ ነው። ቃል አቀባዩ ሺሪን ሚርዚ።

«ይኽ የአራዊቶች አረመኔያዊ ድርጊት ነው። ቀደም ሲል የሠላም ድርድሩን አንቀበልም ብለው በሽብር ድርጊታቸው የቀጠሉት የታሊባን አሸባሪዎችን ሀገሬው በአንድነት የሚፋለምበት ጊዜ ነው። እነሱ ከተፋላሚዎች ጋር የመዋጋት ድፍረቱ የላቸውም። አሁን ጥቃት የሚሰነዝሩት ሕጻናት ላይ ነው። ይኽ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም። ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል።»

ፓኪስታናዊ አባት ቁስለና ልጁን ሲንከባከብ
ፓኪስታናዊ አባት ቁስለና ልጁን ሲንከባከብምስል Reuters

ተማሪዎችን የጨፈጨፈው ቴኅሪቅ ኤ ታሊባን የተሰኘው ቡድን ከዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን አልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል። ወደ ትምህርት ቤቱ ዘልቀው ተማሪዎች እና አስተማሪዎች ላይ የተኩስ ሩምታ የከፈቱት ታጣቂዎች ነጫጭ ልብሶችን የለበሱ ዓረቢኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ የዶይቸ ቬለዘጋቢ ከኢስላማባድ ጠቅሷል። ከዚህ ቀደም በታሊባኖች ጭንቅላቷን በጥይት ተመትታ ከሞት የተረፈችው የ17 ዓመቷ የኖቤል ተሸላሚ ማላላ ዮሣፍዛይ በስደት ከምትኖርበት ብሪታንያ መልእክቷን አስተላልፋለች።

«ከ100 በላይ የዋሕ ሕጻናት እና አስተማሪዎች ሕይወታቸው የመቀጠፉን ዜና ስንሰማ እኔ እና ቤተሰቤ ልባችን በሐዘን ነው የተሰበረው። እናም አሁን ። የምንተባበርበት ጊዜ ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በፓኪስታን ያሉ መሪዎች፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ እያንዳንዳችን በአንድነት በመነሳት ሽብርተኝነትን መዋጋት አለብን ስል ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። እያንዳንዱ ሕጻን ደኅንነቱ የተጠበቀ ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘቱን ማረጋገጥ መቻል አለብን።»

የፓኪስታን ፔሽዋር በካርታ ላይ
የፓኪስታን ፔሽዋር በካርታ ላይ

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንሥትር ናዋዛ ሻሪፍ ግድያውን ተከትሎ ሀገሪቱ «ብሔራዊ የሐዘን ቀን» ማወጇን ይፋ አድርገዋል። ሐዘኑ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይም ተገልጧል።

«ስለልጆቻችን ሞት በሐዘን ተውጠናል። ሆኖም የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅ ሽብርተኝነትን ድል እስክንነሳው ድረስ ትግላችን እንደሚቀጥል ማንም ሊጠራጠር አይገባውም። ትግላችን ይፋፋማል። ለዚያ አንዳችም ጥርጣሬ የለም።»

ጠቅላይ ሚንሥትሩ በፓኪስታን ሥልጣን በያዙ ሰሞን ከታሊባኖች ጋር ለመነጋገር ሙከራ አድርገው እንደነበር ይነገራል። ሆኖም የፓኪስታን ማዕከላዊ መንግሥት እስልምና አክራሪ ቡድኖችን በቁርጠኝነት እየተዋጋ አይደለም የሚሉ ትችቶች እየተሠነዘሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የፓኪስታን መንግሥት በአፍጋኒስታን ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር አክራሪዎቹን መፈለጉ እንደሆነ ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ