1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተሐዋሲው መነሻ ቦታ እና ተግዳሮቱ

ዓርብ፣ የካቲት 13 2007

የኢቦላ ተሐዋሲ በዓይን የማይታይ ንዑስ ነቁጥ ነው። በአጉሊ መነጽር ሲታይ ግን ጫፉ እንደመቋጠር ያለ ክር አይነት ቅርጽ ያለው ይመስላል።

https://p.dw.com/p/1Eel9
Ebola Virus
ምስል AP

ተሐዋሲው ለመጀመሪያ ጊዜ በተመራማሪዎች የተገኘው እጎአ በ1976 ዓም አሁን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምንለው ሀገር የቀድሞው ዛየር ውስጥ በሚገኝ አንድ መንደር ነው። ተሐዋሲውን ኢቦላ የሚል ስያሜ የሰጡት በአካባቢው ከሚገኘው ኢቦላ ከተባለው ወንዝ ነው። በ1970ዎቹ ውስጥ ብቻ ዛየር እና ሱዳን ውስጥ ተሐዋሲው ለሦስት ጊዜያት ተቀስቅሷል። ሆኖም ከእዛ በኋላ ተሐዋሲው እስከ 1994 ድረስ አልታየም። ያኔ ጋቦን ውስጥ የታየው ይኽ የኢቦላ ስርጭት ተሐዋሲው ወደ ምዕራብ አፍሪቃ ያደረገው የመጀመሪያ ጉዞ ተደርጎ ተመዝግቧል።

በአጠቃላይ የኢቦላ ወረርሽኝ ለ20 ጊዜያት ተከስቷል። በሁሉም ታዲያ በአንፃራዊነት ወረርሽኙ በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሎ ነበር። ከባድ በተባለው ወረርሽኝ እንኳን በተሐዋሲው የተጠቃው ሰው ቁጥር ከ430 የዘለለ አልነበረም። የአሁኑ የኢቦላ ወረርሽኝ የተቀሰቀሰው እጎአ በ2013 ዓም ጊኒ ውስጥ ነው። ከዚያም በሽታው ወረርሽ ደረጃ ላይ በመድረስ ወደ ጎረቤት ሃገራት ሴራሊዮን፣ እና ላይቤሪያ በመስፋፋት ከ9000 በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፣ ከ23,000 በላይ ሰዎች በተሐዋሲው እንዲጠቁ አድርጓል።

ኢቦላ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን
ኢቦላ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን

ተሐዋሲው እንዲህ እንደዋዛ ሊሰራጭ ከቻለባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ሃገራት ተሐዋሲው ይዞ ሊመጣ የሚችለውን ችግር አሳንሰው የመመልከታቸው ነገር ነው።

ኢቦላ «በብሔራዊ ቸልተኝነት፣ ክህደት እና ያለመዘጋጀት ውቅያኖስ ውስጥ እየቀዘፈ» ነበር ሲሉ ናይጄሪያዊው የተሐዋሲ ጥናት ተመራማሪው ኦይዋሌ ቶሞሪ ተናግረዋል።

በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ ቀርተዋል። የሰውነት አካል በኢቦላ ሲጠቃ በትክክል የሚሆነው ምንድን ነው? ለምንድን ነው ወጣቶች በእድሜ ከገፉ ሰዎች በተሻለ መልኩ በሽታውን ሊቋቋሙ የሚችሉት? በቅርቡ ከተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በቀደሙት 40 ዓመታት ውስጥ በኢቦላ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 2500 ነው፤ ይኽ ማለት በየቀኑ በኤች አይ ቪ ወይንም በሣንባ ነቀርሣ ከሚጠቁ ሰዎች ያነሰ ቁጥር ነው። ዓለም ኢቦላን በተመለከተ የልምድ እጥረት ይታይባታል።

የኢቦላ ተሐዋሲ ወረርሽኝ በቅርቡ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ከተቀሰቀሰ በኋላ ግን ክትባቶችን እና መድኃኒቶችን የማግኘቱ ጥረት መሻሻል አሳይቷል። የዓለም የጤና ድርጅት በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ (WHO) በኢቦላ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ በተጠቁ ሃገራት ውስጥ ለሚገኙ በበርካታ መቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በ2015 አጋማሽ ክትባቶችን ለማዳረስ ተስፋ ሰንቋል። በ2015 መገባደጃ ላይ ደግሞ ድርጅቱ አንድ ሚሊዮን የኢቦላ ክትባት አቅርቦት እንደሚኖር ተስፋ ያደርጋል።